Monday, August 8, 2016

የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በፅኑ እስራት እንዲቀጡ ተፈረደባቸው

-  የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ተከላከል ተባለ
የሽብር ተግባር ወንጀል ፈጽመዋል በሚል በተሠረተባቸው ክስ ጥፋተኛ ተብለው የነበሩት፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሦስት አባላትና አንድ ተባባሪያቸው፣ በጽኑ እስራት እንዲቀጡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎት ሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ፍርድ ሰጠ፡፡
በጽኑ እስራት እንዲቀጡና ከማንኛውም ሕዝባዊ መብቶቻቸው ለአምስት ዓመታት የታገዱት ፍርደኞች፣ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ እየሩሳሌም ተስፋውና ፍቅረ ማርያም አስማማው ሲሆኑ፣ በአምስት ዓመታት፣ አራት ዓመት ከአምስት ወራትና በአራት ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተፈርዶባቸዋል፡፡ በተባባሪነት የተከሰሰው ደሴ ካሕሳይ አራት ዓመት ከአምስት ወራት ተፈርዶበታል፡፡
ፍርደኞቹ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ እየሩሳሌም ተስፋውና ፍቅረማርያም አስማማው፣ ከኢሕአዴግ ጋር በሰላማዊ መንገድ መታገል አዋጭ እንዳልሆነ ወይም መፍትሔ አይገኝም በሚል፣ የግንቦት ሰባት አባል በመሆን ወደ ኤርትራ ሲሄዱ ድንበር ላይ መያዛቸው ይታወሳል፡፡ በፍርደኛ ደሴ ካሕሳይ አማካይነት ወደ ኤርትራ ሊሻገሩ ሲሉ፣ ድንበር ላይ የተያዙት ሁሉም ፍርደኞች፣ ፍርድ ቤት ቀርበው በሰጡት የእምነት ክህደት ቃል ‹‹የግንቦት ሰባት አባል ነን፡፡ ጥፋተኛ ግን አይደለንም›› በማለት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ድርጊቱን ክደው በመከራከራቸው ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን እንዲያሰማ በማድረግ፣ ተከላከሉ ብሏቸዋል፡፡ እነሱም በመከላከያ ምስክርነት ነባር የኢሕአዴግ ታጋዮችን ማለትም፣ አቶ አዲሱ ለገሰ፣ አቶ ተፈራ ዋልዋ፣ አቶ በረከት ስምኦን፣ ጄነራል ሳምራ የኑስና ሌሎችንም፣ እንዲሁም ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ዶ/ር መረራ ጉዲናን፣ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፣ አቶ ገብሩ አስራትና ሌሎች በርካታ ሰዎችን የቆጠሩ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ባስያዙት ጭብጥ፣ መከላከያ ምስክሮቹ የሚያስረዱላቸው፣ የፈጸሙት ድርጊት ወንጀል ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን መሆኑን ጠቁሞ፣ ‹‹ይህ ደግሞ የሚረጋገጠው በመከላከያ ምስክሮች ሳይሆን በፍርድ ቤት ነው፤›› በማለት የቆጠሯቸውን መከላከያ ምስክሮች ውድቅ አድርጐባቸዋል፡፡ የቅጣት ውሳኔው ከተነበበላቸው በኋላ፣ ብርሃኑና ፍቅረማርያም በተለይ ከይግባኝ ጋር በተያያዘ ለፍርድ ቤቱ የሚያስረዱት ነገር እንዳላቸው ለመግለጽ የፈለጉ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ‹‹መዝገቡ ስለተዘጋ ምንም ዓይነት አስተያየትም ሆነ አቤቱታ አልቀበልም፤›› በማለት ጥያቄያቸውን አልፎታል፡፡ ነገር ግን ማንኛውንም ነገር በማረሚያ ቤት በኩል አቤቱታ ማቅረብ አንደሚችሉ ገልጾ አጠናቋል፡፡
በሌላ መዝገብ በሽብር ድርጊት ወንጀል ተጠርጥሮ ክስ የተመሠረተበት የሰማያዊ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው አቶ ዮናታን ተስፋዬ ሲሆን፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት፣ ሐምሌ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. የተመሠረተበትን ክስ እንዲከላከል ብይን ሰጥቷል፡፡
አቶ ዮናታን ተጠርጥሮ የተከሰሰበት የሽብር ድርጊት ወንጀል፣ ከህዳር ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተደጋጋሚ ጊዜያት በግሉ ፌስቡክ አድራሻ፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን ማለትም አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4ን ተላልፏል የሚል ነበር፡፡
አዋጁን በመተላለፍ የአዲስ አበባና ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላንን ሽፋን በማድረግ፣ በኦሮሚያ በተለያዩ አካባቢዎች ተነስተው የነበሩ አመፆችን የሚያባብሱ መልዕክቶችን በፌስቡክ አድራሻው ማስተላለፉን፣ ዓቃቤ ሕግ ካቀረበው ክስ መረዳት መቻሉን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ አቶ ዮናታን ሐሳቡን በነፃነት የመግለጽ፣ የመጻፍና የማስተላለፍ ሕገ መንግሥታዊ መብቱን ተጠቅሞ መሆን አለመሆኑን መመርመሩን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ላይ ሐሳቡን በነፃነት እንዲገልጽ የተፈቀደለት ቢሆንም፣ ገደብ መጣሉንም ተናግሯል፡፡ አቶ ዮናታን በአንቀጽ 29 (6) ላይ የተጣለው ገደብ በማለፍና በአዋጅ ቁጥር 652/2001ን በመተላለፍ፣ ድርጊቱን መፈጸሙን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ማስረዳት መቻሉን ገልጿል፡፡ በመሆኑም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 113 (2) መሠረት በዓቃቤ ሕግ ያጠቀሰበትን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4ን ወደ አንቀጽ 6 በመለወጥ እንዲከላከል ብይን ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም የመከላከያ ምስክሮች ካሉት ለመስማት ለጥቅምት 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  
Source: ethiopianreporter

No comments: