Wednesday, August 24, 2016

አሜሪካ በኢትዮጵያ አዲስ አምባሳደር ለመመደብ ዝግጁ አይደለችም


·         Outgoing US Ambassador Patricia H.

  በኢህአዴግ ግትር አቋም አሜሪካ ደስተኛ አይደለችም
የስራ ዘመናቸውን አጠናቅቀው ከትናንት ወዲያ በኦፊሴል በተሰናበቱት የአሜሪካ አምባሳደር ምትክ ለኢትዮጵያ የሚሾም ዲፕሎማት ገና በዕጩነት እንኳ እንዳልቀረበ ምንጮች ገለፁ።
ላለፉት ሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ የቆዩት አምባሳደር ፓትሪሽያ ሀስላክ በነሐሴ 24 (ኦገስት 30) ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንደሚመለሱ ምንጮች ለዋዜማ አስረድተዋል። በጊዜያዊነት እርሳቸውን የሚተኩት አሁን በምክትል አምባሳደርነት ማዕረግ እያገለገሉ የሚገኙት ፒተር ቨርማን ናቸው።
የተተኪ አምባሳደር ጉዳይ ውስጥ ውስጡን ቢወራም የአሜሪካ ምርጫ እስኪጠናቀቅ ድረስ እና ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ቦታውን እስኪረከብ ድረስ ሊዘገይ እንደሚችል ምንጮች ይናገራሉ። እስከዚያው ድረስ አሜሪካ የኢትዮጵያን ጉዳይ የምትከታተለው ቻርዥ አፌርደረጃ እንደሚሆን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ያብራራሉ።
ለጊዜያዊ የአምባሳደርነት ቦታው አዲስ ዲፕሎማት ከሚመደብ ይልቅ ምክትል አምባሳደር ፒተር ቻርዥ አፌርነት የመቀጠላቸው ዕድል ከፍተኛ እንደሆነ ጨምረው ይገልጻሉ። አሜሪካ ኢትዮጵያ የምትገኝበት የፖለቲካ ቀውስ በጥልቅ እንዳሳሰባት እየገለፀች ቢሆንም በጉዳዩ ክብደት ልክ የዲፕሎማት ምደባውን ማፋጠን አለመቻሏ እንቆቆልሽ ሆኗል።
ዩናይትድ ስቴትስ እንዲህ አይነት አካሄድ ስትከትል ግን የመጀመሪያዋ አይደለም። ምርጫ 97 ተከትሎ የተከሰተውን የፖለቲካ ቀውስ እና የተቃዋሚ ፖርቲ አመራሮች እስር ስትከታተል የነበረው ቻርዥ አፌርደረጃ በነበሩ ዲፕሎማቷ ነበር። በወቅቱ የስራ ጊዜያቸውን ያገባደዱትን አምባሳደር ኦሪሊያ ብራዚልን ተክተውቻርዥ አፌርየነበሩት ቪኪ ሃድልስተን ነበሩ።
አሜሪካለኢህአዴግ ባለስልጣናት ስሱ ልብ ነበራቸውበሚል ይተቹ ከነበሩት ቪኪ በተጨማሪ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከፍተኛ ስልጣን ላይ የነበሩትን ዶናልድ ያማማቶን በተደደጋሚ በመላክ (ሸትል ዲፕሎማሲ) ቀውሱን ለመፍታት ስትጥር ቆይታለች።
የዲፕሎማሲ ጥረታቸው ተሳክቶላቸዋልተብለው የሚሞገሱት ያማማቶ በስተኃላ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ተሹመዋል። አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን የፖለቲካ ችግር ለመፍታት አሜሪካ እንደ ያማማቶ አይነት ልዩ መልዕክተኛ ትመድብ እንደው የታወቀ ነገር የለም።
በሀገሪቱ የተከሰተውን ህዝባዊ አመፅ ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስ ያቀረበችውን ምክረ ሀሳብ ገዥው ፓርቲ ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኑና በሀይል እርምጃ ችግሩን ለመፍታት በመምረጡ ዋሽንግተን ቀጣይ እርምጃዋን እንድታጤን እንዳስገደዳት ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮቻችን ይናገራሉ።
የኢትዮጵያን መንግስት ሳያስቆጡ መፍትሄ ማምጣት ይቻላል የሚለው አማራጭ ውጤት እንዳላመጣ የተገነዘቡት የአሜሪካ ሹማምንት በጉዳዩ ላይ ከተለያዩ ተቋማትና ባለሙያዎች ጋር መመካከር ጀምረዋል። አሜሪካ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን የፀጥታ ጉዳይ ትብብርንም ሆነ ኢትዮጵያን ካልተፈለገ ቀውስ መታደግ እንዴት ይቻላል በሚለው ሀሳብ ዙሪያ ከተለያዩ የፖሊሲ አማካሪዎች በተሰበሰበ ምክረ ሀሳብ መሰረት ገዥው ፓርቲ አፋጣኝ የፖለቲካ ማሻሻያ እንዲያደርግ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የሚገዳደሩ ችግሮችንም በድርድር ለመፍታት የቀረበውን ሀሳብ ኢህአዴግአስብበታለሁካለ በኋላ ሀሳቡን ቀይሮ ችግሮችን በራሴ እወጣለሁ፣ የተቃውሞ ሀይሉንም በሀይል አንበረክካለሁ ብሏል።

ዋዜማ ራዲዮ

No comments: