Monday, August 29, 2016

ኢህአዴግ ለዲሞክራሲ ጨዋታ ድንጉጥ ነው

ከዛሬ አርባ አመት በፊት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች፤ የህዝቦች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን፣ እኩልነትና ነፃነት እንዲረጋገጥ፣ የሀይማኖት እኩልነትና ነፃነት እውን እንዲሆን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ጥያቄአቸውን አሰምተው ነበር፡፡ 

ከእነዚህ ወጣቶች ከፊሎቹ ያቀረቧቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ ያገኙ ዘንድ መጮህ ብቻውን ፋይዳ የለውም በሚል ብረት አንስተው፣ በወቅቱ የነበረውን አገዛዝ በትጥቅ ትግል በመፋለም፣ ይህ ነው የማይባል የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ከፍለዋል። በመስዋዕትነት ከተሞላ እጅግ መራራ ትግል በኋላ በህይወት የመኖር ፀጋና የድል በለስ የቀናቸው ከፊሎቹ ወጣቶች፤ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በሚል ባቋቋሙት ድርጅት እየተመሩ፣የዛሬ 25 ዓመት የሀገሪቱን ብሔራዊ ስልጣን ለመቆናጠጥ በቅተዋል፡፡

በርካታ ኢትዮጵያውያን፤ መልካም ዘር መልካም ምርት ያስገኛል እንደሚባለው የዛሬ 25 ዓመት በፀደቀው ህገመንግስትና ኢህአዴግ በገባላቸው የዲሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የነፃነትና የእኩልነት ቃል ተማምነው የድህረ-ደርግ የህይወት ዘመናቸው መልካም እንደሚሆን በእጅጉ ተስፋ አደርገው ነበር፡፡ 1992 . በተካሄደው ብሄራዊ ምርጫና ከምርጫው በኋላ በሀገሪቱ የፖለቲካ፣ኢኮኖሚና፣ ማህበራዊ ኑሮ መድረክ ላይ ኢህአዴግ የተወነው ድራማና አተዋወኑ፣ ቃል ከገባው ብቻ ሳይሆን ያለ አንዳች ገደብ እንዲያከብርና እንዲተገብረው ህግ ግድ ከሚለው ከህገ መንግስቱም ውጭ በመሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ ደንግጠውና፤ ‹‹ከቁርስ በፊት የሚዘፍን ከእራት በፊት ያለቅሳል›› የሚለው የኢራናውያን ተረት የተተረተባቸው ያህል ተከፍተው ነበር፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ኢህአዴግ ይዞት የተነሳውና እልፍ ታጋዮቹ በሙሉ ፈቃደኝነትና በማያወላውል ቁርጠኝነት፣ ክቡር ህይወታቸውንና አካላቸውን የተሰውለት የነፃነት፣ የእኩልነት፣ የፍትህና የመብት አላማዎች ከአፉ እንጂ ከልቡ አውጥቶ የጣላቸውና በስልጣን መንበር የለወጣቸው፣ አራት ኪሎ የምኒልክን ቤተ መንግስት በተቆጣጠረ በማግስቱ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኢህአዴግ ዋነኛ የትግል አላማና ግብ፣ ስልጣንና ስልጣን ብቻ ሆነ፡፡ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት ኢህአዴግ ሲፈፅማቸውና ያለ አበሳችን እዳውን ሲያስከፍለን የኖርን በመሆኑ፣ ይህንን እውነትም ትክክልም የሆነን ጉዳይ ተከራክሮ መቀየርም ሆነ ማስተባበል አይቻልም፡፡

ኢህአዴግ ቀድሞ ይዞት የተነሳውንና ለዘመናት የታገለለትን ዋነኛ የትግል አላማ አጥፎ፣ ሁሉም ነገር ለስልጣኔና ለስልጣኔ ብቻ የሚል አዲስ የትግል አላማና ግብ አንግቦ እንዲነሳ፣ ‹‹ከእኔ በቀር ሌሎቹ ይህቺን አገር ያጠፏታል›› የሚለው ስር ሰደድ አመለካከቱ፣ ከፍተኛ ምናልባትም ዋነኛውን አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህ አይነቱ አድሀሪ፣ ኋላቀርና ፀረ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰቡ ደግሞ በተራው፣ ኢህአዴግን ባለበት ቆሞ እንዲረግጥና ለመበስበስ አደጋ እንዲጋለጥ አድርጎታል፡፡ ይህ ጠንቀኛ ክፉ ደዌም ነባራዊውን እውነታ እንደወረደ መርምሮ መረዳት እንዳይችል፣ ጨለማ ውስጥ እንዲገባና ‹‹ንጉስ አይሳሳትም›› በሚል ሮማዊ አመለካከት ባለበት እንዲዳክር ምክንያት ሆኖታል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝቦች ግን በየአቅጣጫው እልፍ አዕላፍ ታጋይ ልጆቻቸውን፣ የህይወትና የአካል መስዋዕትነት የከፈሉበትና ህገ-መንግስታዊ እውቅናና ጥበቃ ያገኘው ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩ፣ የፍትህ ነፃነት ተከብሮ በህግ ፊት እኩል መሆናቸው እንዲታወቅ፣ የዘር፣ የሃይማኖት ነፃነትና እኩልነት እንዲረጋገጥና ያላንዳች ገደብ እንዲከበርላቸው ላለፉት 20 አመታት ለአፍታም እንኳ ሳይሰለቹ ገዢውን ፓርቲ ኢህአዴግን አቤት ሲሉ ኖረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝቦች በህገ-መንግስቱ የተረጋገጠውን ራስን የማስተዳደርና የራሳቸውን ጉዳይ ራሳቸው የመወሰን የማይገሰስ መብታቸው በእውነት እንዲከበርላቸው፣ የአንድ ኢህአዴጋዊ ቡድን የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነትና የዚህ ቡድን ግልጽና ስውር የሞግዚት አስተዳደር እንዲቀርላቸው፣ ሀገሪቱ ከምትጋግረው ብሄራዊ ኬክ የበይ ተመልካች መሆናቸው ቀርቶ፣ ህጋዊና ፍትሀዊ ድርሻቸውን እንዲያገኙ፣ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት ኢህአዴግንና መንግስቱን አበክረው ሲያሳስቡት ኖረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች ላለፉት 20 አመታት የተፈራረቁባቸውን የመብት ረገጣ፣ የነፃነት መታፈን፣ የፍትህ እጦትና፣ የአድሏዊ አሰራር ግፍና በደል የፈጠረባቸውን ሰዋዊ ስሜት የሚተነፍሱበት ትንሽዬየማርያም መንገድየሚያገኙበት፣ እንዲያው ሌላው ቢቀር ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ እንኳ እንዲችሉ ኢህአዴግን ኤሎሄ እያሉ ሲማጠኑ ኖረዋል፡፡

ጣሊያኖች ‹‹ውሀ ጥም ሳይደፋህ በፊት የውሀ ጉድጓድህን በደንብ ቆፍር›› የሚል አሪፍ አባባል አላቸው። እንደ ኢህአዴግ ላለ በስልጣን ላይ ያለ ድርጅት፤ ይህ የጣሊያኖች አባባል ወቅታዊም አስፈላጊም ምክር ነበር። ይሁን እንጂ ባለበት የቸከለውና እየበሰበሰ ያለው ኢህአዴግ፤ በብረት እጁ አጥብቆ በያዘው ስልጣን ላይ አንዳች አይነት አደጋ እስካልደቀነ ወይም በስልጣኑ ላይ አቧራ እስካላስነሳ ድረስ ይህን ረዥም ዘመን ያስቆጠረ፣ የህዝብ እግዚኦታና ተማጥኖ በሚገባ አዳምጦ ተገቢውን መልስ ለመስጠት ጊዜውም ፍላጎቱም እንደሌለው በተግባር አሳይቶናል፡፡
ይልቁንስ ለኢህአዴግ ቀላል የሆነለት ዘዴ፣የኢትዮጵያ ህዝቦች ለመጀመሪያ ጊዜ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩ፣ የራሳቸውን እድል በራሳቸው እንዲወስኑ፣ የግልም ሆነ የቡድን መብቶቻቸው እንዲከበሩ አድርጌአለሁ፣ የፌደራል ስርአት ፈጥሬ ብሄር ብሄረሰቦች በነፃነትና በእኩልነት የሚኖሩበት ምቹ ሁኔታ ፈጥሬአለሁ በማለት ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እሽክሜ ማለት ነው፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ኢህአዴግ የመብት የፍትህ፣ የነፃነትና የእኩልነት ጥያቄ ለዘመናት ያለአንዳች መታከት ለሚያቀርብ ህዝብ፤ እንዲህ አይነት መልስ በመስጠት ህዝቡን ሳይሆን ራሱን ለማታለል ዘወትር መትጋቱ በእጅጉ የሚያስገርም ነገር ነው፡፡ ኢህአዴግ ራሱን የሚያታልልበት ሌላው አብይ ጉዳይ ተሀድሶ ነው። ኢህአዴግ ለራሱ ለድርጅቱ ሆነ ለገነባው የፖለቲካ ስርአት አደጋ ናቸው የሚላቸውን ጉዳዮች፣ ዘወትር በተሀድሶ እያጠራ እንደሚጓዝ ሳይነግረን ያለፈበት ጊዜ መኖሩ ያጠራጥራል፡፡
በዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርአት መንግስታት በየጊዜው የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች በአግባቡና በወቅቱ መልስ በመስጠት የህዝባቸውን ፈተናና ሸክም ማቅለል ለአፍታም እንኳ ቸል ብለው አይናቸውን ለእንቅልፍ የማይከድኑበት ዋነኛ ተግባርና ኃላፊነታቸው ነው፡፡ የዚህ ጉዳይ ዋናው ምክንያት ሌላ ነገር ሳይሆን የሉአላዊ ስልጣን ባለቤትና መንግስታትን በምርጫ ሻሚና ሻሪው ህዝቡና ህዝቡ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡

ኢህአዴግ ስለ ዲሞክራሲ ስርአት የታገለለትን አላማና የገባውን ቃልኪዳን ያጠፋው ገና ከጀምሩ ነው። እናም አሁን ገነባሁት እያለ የሚሸልልበት ዲሞክራሲ፤ የይስሙላ ዲሞክራሲ መሆኑን ድፍን አለሙ አውቆት ፀሐይ ሞቆቷል፡፡ ስለዚህም የዲሞክራሲ ስርአት ወሳኝ የሆኑ የዲሞክራሲ ተቋማትም የስርአቱና የኢህአዴግ አምሳያዎች ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ ኢህአዴግ ሲፈልግ 99.6 በመቶ፣ አለበለዚያ ደግሞ መቶ በመቶ ምርጫ ድምጽበማግኘት ስልጣን እንዴት መቆጣጠር እንደሚችል በሚገባ ያውቃል፡፡

ኡህአዴግ ተወልዶ ያደገው ተፎካካሪዎቹን በኃይል በማስወገድና የሱን ፊት አይቶ አዳሪ ገባር በማድረግ ስለሆነ፣ ለዲሞክራሲ ጨዋታ እንግዳና ድንጉጥ ድርጅት ነው፡፡ ይህንን እውነት የቁጥጥርና የአፈና እጁን ለአመል ታክል ላላ ባደረገባት 97 ብህሄራዊ ምርጫ ወቅት በደንብ አሳይቶናል፡፡ ከዚህ ምርጫ አይረሴ ትምህርት በመውሰዱ፤ በቀጣዮቹ ሁለት ብሄራዊ ምርጫዎች በሚያስደንቅ ትጋትና ብቃት የተንቀሳቀሰው፤ የህዝቡን አንገብጋቢ የመብት፣ የነፃነት፣ የእኩልነትና የፍትህ ጥያቄዎች በአግባቡ በመመለስ ሳይሆን ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችን እግር መትከያ በማሳጣትና የቁጥጥርና የአፈና ሸምቀቆውን ይበልጥ በማጥበቅ ነው፡፡

የህዝብን ጥያቄ በተመለከተ ከሁሉም የከፋው የኢህአዴግ ድርጊት፤ ጥያቄዎቹን መመለስ አለመፈለጉና አለመቻሉ ሳይሆን ፍፃሜው የማይታወቅ ቧልታይ ተውኔት እየተወነ፣ በህዝብ ስቃይና መከራ ላይ ማላገጡ ነው፡፡

ራቅ ያለውን ጊዜ እንተወውና ከወራቶች በፊት ህዝቡ ጠንከር ባለ ሁኔታ የመብት፣ የነፃነት፣ የእኩልነትና የፍትህ ጥያቄዎችን አቅርቦ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ለእነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት በሚል ማሾፍ የጀመረው፤ የጥያቄዎቹ ዋነኛ መንስኤ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው በማለት ነው፡፡

ይህን የኢህአዴግ የመልካም አስተዳደር ፌዝና ቧልት እጅግ መራራ የሚያደርገው ህዝቡ ያነሳቸው መሰረታዊ የመብትና ነፃነት ጥያቄዎች ከኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ ከውሃ አቅርቦት መጓደልና የመንግስትና ህዝባዊ ተቋማት ካለው የተንዛዛ የቢሮክራሲ መጉላትና ሙስና ጋር አንድ አይነት አድርጎ መቁጠሩ ነው፡፡

እንዲህም ሆኖ ይህንኑ የመልካም አስተዳደር ችግር ለማስወገድ ጀመርኩት ያለው ዘመቻ፤ ከአጉል ዘገር ንቅነቃና ከጉሮ ወሸባዬ ግርግር አልፎ እንዲው ላመል ታህል እንኳ ወደፊት ፈቅ ማለት አለመቻሉ የኢህአዴግ መበስበስ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ አመላካች ነው፡፡

የሆኖ ሆኖ ከአሁን በኋላ ኢህአዴግ በህዝብ የነፃነት፣ የእኩልነት፣ የመብትና የፍትህ ጥያቄ ላይ እንዲህ እያሾፈ የሚቀጥልበት ጊዜ ያለው አይመስልም፡፡ እናም ያለው እድል አንድና አንድ ብቻ ነው፡- አለመጠን የሚፈራውን ዲሞክራሲ ፊት ለፊት መጋፈጥና የህዝቦችን የነፃነትና የመብት ጥያቄዎች ያለአንዳች ማመንታት መመለስ!!

addisadmassnews.com

No comments: