መንግሥት በአዲስ አበባ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችና የሥራ ማቆም አድማ ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋቱ አይሎበታል። ይህን ተከትሎ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞች ስብሰባ እየተጠሩ ነው። የመንግሥት ተቀጣሪ ያልሆነውን የከተማ ነዋሪ ደግሞ በኢሕአዴግ እና በመንግሥት መዋቅሮች በተከታታይ ለመሰብሰብ መታቀዱ ተሰምቷል።
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው በተለያዩ የመንግስት መዋቅሮች ውስጥ የሚሰሩ ተቀጣሪዎች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት እንደሚኖር የተነገራቸው ሲሆን ከዚህ ቀደም የተገፉ አጀንዳዎችና የሰራተኛው ጥያቄዎች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ስምቻለሁ ይላል የአዲስ አበባ መስተዳድር ስራተኛ።
“ሰለመኖሪያ ቤትና የሰራተኞች የደመወዝ ጉዳይ ውይይት እንደሚደረግ ወሬው ተናፍሷል ይሁንና በይፋ የተባለ ነገር አልሰማሁም” ትላለች በላፍቶ ክፍለከተማ የጤና ቢሮ ሰራተኛ ።
የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ሰኞ ለተለያዩ መዋቅሮች ይፋ ባደረጉት መርሀ ግብር መሰረት በመላ ሀገሪቱ ገዥውን ፓርቲ የሚደግፉ ስብሰባዎችና እንደአመቺነቱ ሰልፎች ይደረጋሉ። የጠባብነትና የትምክህት አደጋዎችን መከላከል በሚል በወጣው ዕቅድ መሰረት አናሳ ክልሎችንና የገዥውን ፓርቲ መዋቅር በመጠቀም በሀገሪቱ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ አነስተኛ መሆኑን ለማሳየት መታቀዱንም ለመንግስት ቅርብ የሆኑ ምንጮች ነግረውናል። ኢህአዴግ መገናኛ ብዙሀን በተገቢው ስራቸውን አልሰሩም ሲል የወቀሰ ሲሆን በአስቸኳይ ሰፊ የፕሮፓጋንዳ ሰራ ለማካሄድ በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደረጃ የሚመራ ቡድን ተቋቁሟል።
በአዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች ተቃውሞና አድማ ሊከሰት ይችላል በሚል ስጋትም የታክሲ ማህበራትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ላሉ ፓርቲ ዘመም መዋቅሮች ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። ከሰሞኑ በነበረው አመፅ በተለያዩ ክፍለ ሀገራት የተፈጠረውን የትራንስፖርትና የመሰረታዊ አቅርቦት ችግር ለመፍታትም የፀጥታ ሀይሎች፣ የክልል መሰሪያቤቶችና የሚንስቴር ተቋማት በጋራ እየተመካከሩ ነው።
“መንግስት እንዲህ ሲሰጋ አይቼ አላውቅም፣ ኮሽ ባለው ሁሉ እየደነገጡ እኛንም እያሳቀቁን ነው። እኔ ለምሳሌ ዛሬ ቢያንስ አራት ጊዜ ስብሰባ ተብሎ ተጠርቻለሁ። መመሪያ በመጣ ቁጥር ይጠሩናል። ነገሩ ወይ ቢለይለት ይሻላል” ሲል የማክሰኞ ውሎውን የነገረን የንግድ ባንክ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ሰራተኛ ነው።
የሀገሪቱ የፀጥታ መስሪያቤትም አመፅ ሊስፋፋ ይችላል በሚል ያሉትን ስውር ሰራተኞች በሙሉ በሰራ ያሰማራ ሲሆን፣ በመደበኛ የደህንነት ሰራተኞች መሸፈን ሰለማይቻል ጠቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞችን ለማሰማራት ተገዷል።የደህንነት መስሪያቤቱ ለአዳዲስ ምልምሎቹና ስውር ጠቋሚዎች የአስቸኳይ ጊዜ ስልክ ቁጥሮች ማደሉንም ተረድተናል።
ከመደበኛ የደህንነት ሰራተኞች ምስጢር የሚያወጡ አሉ በሚል ጥብቅ ማሳሰቢያ የተሰጠ ሲሆን ምስጢር ሲያሳልፍ የተገኘ የሞት ቅጣት ይጠብቀዋል በሚል መነገሩንም ስምተናል። የደህንነት መስሪያቤቱ በሙስና ተዘፍቀዋል የተባሉና በአማራና በኦሮሚያ ክልል አመፅ ተባብረዋል የተባሉ የፓርቲው ባለስልጣናትን የተቃዋሚ መሪዎችንና በእስር ላይ ያሉ ወጣቶችን ምስክርነት ያካተተ ዶሴ እያደራጀ መሆኑንም ስምተናል።
የደህንነት መስሪያ ቤቱ አመፁ የውጪ ሀይሎች እጅ እንዳለበት ለማጋለጥ ያለመ ተራኪ ፊልም ከመንግስት ሚዲያ ጋር በጋራ እያዘጋጀ ነው። ይህን የፕሮፓጋንዳ ስራ ከደህንነት መስሪያቤቱ የተመደቡ ሶስት ሰዎችና አንድ የመንግስት ጋዜጠኛ ብቻ የሚሰናዱት ነው።
ዋዜማ ራዲዮ
No comments:
Post a Comment