Thursday, August 4, 2016

አዲስ አበባን ጨምሮ በኦሮምያ፣ ባህርዳርና ደብረታቦር የሚደረገውን የተቃውሞ ሰልፍ የተሳካ ለማድረግ ዝግጅቶች እየተካሄዱ ነው



ሐምሌ  ፳፰ ( ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፰ / ኢሳት ዜና :-የፊታችን ቅዳሜ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ኦሮምያ፣ በባህርዳር ከተማ እና በደብረታቦር ከተማ የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን የሚያቀነቅኑ የተቃውሞ ሰልፎች ይደረጋሉ። በእነዚህ ሰልፎች ላይ የህወሃት አገዛዝ እንዲያበቃ ጥሪ ይቀርባል።

 ሰልፉ በኦሮምያ የደረሰውን ጭፍጨፋ እንዲሁም የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ምንነት የኮሚቴ አባላት መታሰራቸውን ያወግዛል።

በኦሮምያና በባህርዳር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሰልፉን ቀን በጉጉት እየጠበቁት መሆኑን ይናገራሉ። አንድ  በባህርዳር ከተማ የሚኖር  ህዝቡ ብሶታል፣ ድምጹን የሚገልጽበት መድረክ አጥቶ ቆይቷል፤ አሁን አጋጣሚው ጥሩ በመሆኑ አንቀርምብሎአል።

በምእራብ አርሲ ነዋሪ የሆነው ግለሰብም ህዝቡ ሰልፉ ቢከለከልም ቢፈቀድም ድምጹን ለማሰማት ዝግጁ ነው ይላል። ህዝቡ የሚያጣው ነገር የለም የሚለው ግለሰቡ ኢትዮጵያ አንድነቷ ይፈራርሳል በማለት ገዢው ፓርቲ ተቃውሞ እንዳይደረግ የሚያደርገው ቅስቀሳ ባዶ መሆኗን፣ ኢትዮጵያ እነሱ እንደሚሉት አትፈርስም፣ ይህን ለመናገርም ጠንቋይ መሆን አያስፍልግም ብሎአል።

ከደቡብ ክልል አስተያየታቸውን የሰጡ አባት ደግሞ ተቃውሞው በመላው አገሪቱ አለመጠራቱ እንዳስቆጫው ገልጸው፣ በተለይ በባህርዳርና ደብረታቦር በሚካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ የመከላከያ ሰራዊቱ ከእናት እና አባቱ ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል።

በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑትና ቤታቸው በቅርብ የፈረሰባቸው ግለሰብ በአዲስ አበባ በሚደረገው ሰልፍ ለመሳተፍ መረጃ በስፋት እንዲሰጣቸው ጠይቀው፣ በባህርዳርና ደብረታቦር በሚደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ህዝቡ ድርጊቱን እንዲያወግዝላቸው ጠይቀዋል።


No comments: