Friday, May 20, 2016

ህገወጥ በተባሉ የመኖሪያ ቤቶች መፍረስ ጋር ተያይዞ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ኢሳት (ግንቦት 12 2008)
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ አየር ማረፊያ ዙሪያ ህገወጥ በተባሉ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ የሚወስደው እርምጃ አርብ መቀጠሉንና በርካታ ሰዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እማኞች አስታወቁ።
ወረገኑ እየተባለ በሚጠራው መንደር ከፍተኛ የጸጥታ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ የተናገሩት ነዋሪዎች የጸጥታ ሃይሎች የቤት ለቤት ፍተሻን በማካሄድ ሁከትን ፈጥረዋል የተባሉ ሰዎችን አሳልፈው እንዲሰጡ ዘመቻ በማካሄድ ላይ መሆናቸውም ታውቋል።
ህገወጥ ናቸው በተባሉ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ መንደር ጋዜጠኞች ጉብኝት እንዲያደርጉ እገዳ ተጥሎ የሚገኝ ሲሆን፣ በሶስት ቀን የጸጥታ ሃይሎች ዘመቻ የደረሰው ጉዳት በትክክል ማወቅ አንዳልተቻለም የአይን እማኞች ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ ቁጥራቸው መግለጽ ያልፈለገው ተጠርጣሪዎች በጸጥታ ሃይሎች ላይ ህገወጥ እርምጃም ወስዳችኋል ተብለው ለእስር መዳረጋቸው አረጋግጧል።
ያለመጠለያ መቅረታቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች በበኩላቸው የጸጥታ ሃይሎችና አፍራሽ ግብረሃይል ለአስር አመታት ያፈሩትን ንብረት እንደወደሙባቸውም አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ 2 የሚበልጡ መኖሪያ ቤቶች በህገወጥ የተገቡ ናቸው በማለት የማፍረስ ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
ይሁንና ነዋሪዎቹ ለአመታት የቆየውን የመኖሪያ ቤት ግንባታቸው የከተማ አስተዳደሩ በሰጠው ልዩ እድል ውስጥ መካተት እንደነበረባቸው ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
የተለያዩ አካላት ለሶስት ቀን በዘለቀው የጸጥታ ሃይሎችና የነዋሪዎች ግጭት 10 የሚበልጡ ሰዎች መሞታቸውን ቢገልጹም ፖሊስ ስለሞቱ ሰዎች የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።
አርብ በአካባቢው ውጥረቱ ቀጥሎ መዋሉን የሚናገሩት ነዋሪዎች የከተማው አስተዳደር ያለምንም አማራጭ የወሰደውን የሃይል እርምጃ በነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞንና ቁጣን ቀስቅሶ እንደሚገኝም አክለው አስረደዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ህገወጥ የተባሉትን ግንባታዎች የማፍረሱ ዘመቻ በቀጣዩ ቀናትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስነብቧል።


No comments: