Tuesday, May 24, 2016

ከሰሃራ በታች ባሉት አገራት የፖለትካ ነጻነት ችግር ውስጥ እንደወደቀ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የፖለቲካ ነጻነት ከሰሃራ በታች ባሉት አገራት ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገለጸ። መንገስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በዚሁ የአፍሪካ ክፍል ከፍተኛ ጫና እንደሚደረግባቸው የገለጸው የአምነስቲ ኢንተናሽናል ዘገባ፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማርያንና ሌሎች መንግስታትን የሚነቅፉ ድምጾች በፍርሃት ዝም እንዲሉ ወይም አገር ጥለው እንዲሰደዱ ተደርገዋል ብሏል።
እንደ ኡጋንዳይ፣ ቡሩንዲና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በመሳሰሉት አገራት መሪዎች የስልጣን ዘመናቸውን የሚገድባቸውን ህገመንግስት በማስወገድ፣ አዲስ ህገመንግስት እንደሚያረቁ፣ ተቃዋሚዎችንና የሲቪል ማህበረሰብን ደግሞ በሃይል በመደፍጠጥ ቁጥጥር እንደሚያደርጉባቸው ሪፖርቱ አያይዞ ገልጿል። እንደ አንጎላ ባሉ ሌሎች አገራት መንግስት ፍርድ ቤትን በመጠቀም ተቃዋሚዎችን እንደሚያስፈራሩ፣ እንዲሁም ተቃዋሚዎች በገንዘብ እጦት በማድከም ወይም ማለቂያ የለሽ በሆነው የፍርድ ሂደት በማጉላላት ተቃውሞውን እንደሚያፍኑ ሪፖርቱ ተብራርቷል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃገራት ደግሞ በብሄራዊ ጸጥታንና ደህንነት ሰበብ አለም አቀፍ የመሰብሰብና የመናገር ነጻነትን በሚጻረር መልኩ በተቃዋሚዎች ላይ ከባድ ቅጣት እንደሚፈረድባቸው ሪፖርት አትቷል።
ኬንያን በመሳሰሉ ሃገራት መንግስታት ሰላማዊ የሆኑ ተቃውሞዎችን ሃይል በመጠቀም ለመበተን እንደሚሞክሩ በዘገባው ተመልክቷል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ በኡጋንዳ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ፕሬዚደንታዊ እጩ ኪዛ በስግዬ አገር በመክዳት ወንጀል የሞት ቅጣት ይፈረድባቸዋል በመባላቸው ሰላማዊ ተቃውሞ ያሰሙ ሰልፈኞችን ፖሊስ በመደብደብ በትኗል ሲል የመንግስታቱን ጸረ-ሰላም አካሄድ በማስረጃ አስደግፎ አውጥቷል።
ኢትዮጵያ ሰላማዊ ሰልፎችን በሃይል በመበተን ከሰሃራ በታች ካሉት ሃገራት ቀዳሚዋ አገር መሆኗን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገልጿል። በዚሁ አመት ታህሳስ ጀምሮ ከአዲስ አበባ ከማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በተነሳው ሰላማዊ ህዝባዊ ተቃውሞ እስከ 400 የሚሆኑትን ሰላማዊ ዜጎችን መንግስት እንደገደለና በሺዎች የሚቆጠሩ እንዳሰረ፣ እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ቤታቸውና የንግድ ድርጅታቸው እንደወደመ ለዚሁ ጥፍፋት ተጠያቂው ህወሃት የሚመራው መንግስት እንደሆነ በሪፖርቱ አስፍሯል። ኦሮሚያ እንደሆነው ሁሉ፣ በኮንሶምና በሌሎች አካባቢዎች መንግስት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሃይል እርምጃ መውሰድ መቀጥሉን በማስረጃ በማስደገፍ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስነብቧል።

ኢሳት

No comments: