Wednesday, May 25, 2016

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የራሱን ማስተር ፕላን ሊያጸድቅ ነው ተባለ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሶስት አመት ያለማስተር ፕላን የቆየበትን ችግር እልባት ለመስጠት የኦሮሚያ ክልል ያልተካተተበትን የራሱን ማስተር ፕላን ሊያፀድቅ መሆኑ ተገለጸ።
10 አመት ሲያገለግል የነበረው የከተማዋ ማስተር ፕላን ከሶስት አመት በፊት የመጠቀሚያ ጊዜው ቢያበቃም ከኦሮሚያ ክልል የመሬት መስፋፋት ጋር በተገናኘ ማስተር ፕላኑ ተግባራዊ ሳይደረግ መቆየቱን አስተዳደሩ አስታውቋል።

በቅርቡ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መስፋፋት ጋር የተፈጠረውን ተቃውሞ ተከትሎ 200 በላይ ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በክልሉ የተፈጠረውን ተቃውሞ ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን ዝግጅት ራሱን ማግለሉ ይፋ ማደረጉ ይታወቃል።

ክልሉ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክልልሉ ያልተካተተበትን የራሱን ማስተር ፕላን በማዘጋጀት በቅርቡ ለህዝብ ውይይት በማቅረብ መወሰኑን ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

አዲስ አበባ ከተማን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለማስፋፋት የተጀመረው እንቅስቃሴ ያስመጣውን ከፍተኛ ተቃውሞ ተከትሎ መንግስት ማስተር ፕላኑ ተግባራዊ አይደረግም ሲል ለህዝብ ይፋ ማድረጉም የሚታወስ ነው።

የከተማው አስተዳደር በተናጠል አዘጋጅቷል የተባለው ማስተር ፕላን በከተማዋ የሚገኙ ክፍለ ከተሞችን ዳግም የመከለስ እቅድ እንዳለው የተገለጸ ሲሆን፣ የከተማዋ ነዋሪዎች በየቀበሌው በቅርቡ በመሰባሰብ ውይይት ያካሄዱበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከአራት ወር በላይ ዘልቆ በነበረው የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ በጸጥታ ሃይሎች ከተገደሉት 200 በላይ ሰዎች በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ የፓርቲ አመራሮችና አባላት እንዲሁም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለእስር ተዳርገው እንደሚገኙ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይገልጻሉ።

አሜሪካን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረትና የተለያዩ አካላት በክልሉ የተፈጸመው ግድያ በገለልተኛ አካል እንዲጣራና ለእስር የተዳረጉም የፖለቲካ አመራሮች እንዲፈቱ ጥያቄን አቅርበዋል።
ኢሳት


No comments: