Monday, May 16, 2016

የተዛቡ ምስሎችን በድረገጾቸው ላይ የለጠፉ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴርና ኢቢሲ አንባቢዎችን ይቅርታ ለመጠየቅ ተገደዱ

የመንግስት ኮሚውኒኬሽን ጉዳዮች /ቤትና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን  ከአርበኞች ግንቦት ሰባት የተማረኩ ጦር መሳሪያዎችና የመንገድ ግንባታ ናቸው በሚል በድረገጾች ላይ የተለጠፉ ምስሎች የኢትዮጵያ ያልሆኑ መሆናቸውን በማስመልከት በማህበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚዎች በደረሰባቸው ጫና ምስሎቹን ማንሳታቸው ታወቀ።
የመንግስት ኮሚውኒኬሽን ጉዳዮች /ቤትና በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮሮፖሬሽን በድረገጾቻቸው ላይ ያሰራጯቸው ሁለት ምስሎች በኢትዮጵያ ውስጥ ያልተነሱ መሆናቸውን ማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎች ስለደረሱባቸው መስሪያ ቤቶቹ ይቅርታ ለመጠየቅ ተገደዋል።
አዋሽ ወልዲያ፣ ሃራ ገበያ ተብሎ በኮሚውኒኬሽን /ቤት የተሰራጨው ምስል Devil’s Slide Tunnel ተብሎ የሚጠራው  ፓሲፊካ በሚባል ካሊፎርኒያ አሜሪካ ግዛት የሚገኝ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ኮሚውኒኬሽን /ቤት ይህንን ምስል በወልዲያ አካባቢ በመንግስት ወጪ የተሰራ ነው በማለት ለአንባቢ የተሳሳተ ምስል አቅርቦ እንደነበር ይታወቃል።
ሆኖም የኮሚኔኬሽን ጉዳዮች /ቤት ያሰራጫቸው የምስሎች መረጃ፣ የተሳሳቱና ከጽሁፎቹ ጋር የማይገናኙ በመሆኑ ይቅርታ እንጠይቃለን ሲል የፌስቡክና ትዊተር ድረ-ገጽ ተከታዮችን ይቅርታ ጠይቋል።
በተመሳሳይ መልኩም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በኤርትራ ከሚታገዙ አሸባሪ ድርጅቶች የተማረከ ነው በሚል የጦር መሳሪያ የሚያሳይ ምስል ትክክል እንዳልሆነና፣ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በቀጥታ እንደወሰደው ገልጾ፣ አንባቢዎቹን ይቅርታ ጠይቋል። ለተፈጠረው ስህተት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተጠያቂ ነው ሲልም ክስ አቅርቧል።
ከኤርትራ የሚታገዙ አሸባሪዎች ላይ የተማረከ መሳሪያ ነው በማለት ኢቢሲ ያሳየው ምስል 2004 በኢራቅ ፋሉጃህ ግዛት 82ኛው አየር ወለድ ክፍለጦር የተማረከ መሆኑን የማህበራዊ ድረ-ገጽ ተሳታፊዎች እጅ ከፍንጅ ይዘዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ተቋማት አንባቢዎችን ሲዋሹ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳልሆነና፣ ብዙ ጊዜ የሚያቀርቡት ዘገባ በእውነት ላይ የተመሰረተ እንዳልሆነ የማህበራዊ ድረገጽ ተሳታፊዎች በጻፏቸው አስተያየቶች ተመልክቷል።

Esat News

No comments: