Wednesday, May 11, 2016

የሚዲያ ብዝኃነት ማጥ የሆነባት አገር

‹‹ዛሬ የፕሬስ ቀን ነው፡፡ እናም ከዛሬ የበለጠ የመናገሪያ ቀን፣ ሐሳብን የመግለጫ ቀን፣ ሰው የሚፈልገውን ብቻ ሳይሆን ሰውም ሊያስቆጣ የሚችል ነገር የመናገሪያ ቀን የለም፡፡››
ይህን የተናገሩት አንጋፋው የሕግ ባለሙያና የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አብዱ ዓሊ ሒጂራ ናቸው፡፡ በዘንድሮው የፕሬስ ቀን ጥናት ካቀረቡት መካከል የተለየ ንግግር ያደረጉት ራሳቸው አቶ አብዱ ብቻ ነበሩ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይሁንና ባለፉት ዓመታት የፕሬስ ቀን ሲከበር ቢያንስ የተለያየ ሐሳብና አመለካከት ያላቸው ሰዎች የበዓሉ ድምቀት ነበሩ፡፡ የግዮን፣ ሒልተን፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና የመሳሰሉት መሰብሰቢያ አዳራሾች በተከበሩ የፕሬስ ቀን በዓላት የምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ተወካዮች፣ የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች፣ የተለያዩ አገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ የሙያ ማኅበራት ተወካዮችና ታዋቂ ግለሰቦች ለመንግሥት ተወካዮች ሞጋች የሆኑ ጥያቄዎችን ማስተናገዳቸውና ሞቅ ያለ ክርክርና ውይይት መደረጉ የፕሬስ ቀን መገለጫ ነበር፡፡ በእነዚህ ሰፋፊ አዳራሾች የተገኙ ተሳታፊዎች ብዛትና ብዝኃነት በእርግጥም በናፍቆት የሚጠበቅ ቀን ያደርገው ነበር፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በዓሉ በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አማካይነት የሚካሄድ ሲሆን፣ የተሳታፊዎች ቁጥር እጅግ የተመናመነ ሆኗል፡፡ ይበልጥ አሳሳቢው ጉዳይ ግን ተሳታፊዎቹ በኢትዮጵያ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ከመቼውም ጊዜ በላይ በስኬት እየተጓዘ እንደሆነ በአንድ ድምፅ የሚናገሩ መሆናቸው ነው፡፡ በዓሉ ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ‹‹መረጃ የማግኘት መብትና መሠረታዊ ነፃነቶች፡- ይህ የእናንተ መብት ነው!›› በሚል መሪ ቃል ሲከበር፣ ሚያዝያ 25 ቀን 2008 .. በፍሬንድሺፕ ኢንተርናሽናል ሆቴል በኢትዮጵያ ደግሞ መሪ ቃሉ ‹‹የሚዲያ ብዝኃነትን ያከበረች አገር - ኢትዮጵያ!!!›› ነበር፡፡ 
መሪ ቃሉ በራሱ በመንግሥትና በሌሎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ አስተያየት በሚሰጡ አካላት መካከል ያለውን ልዩነት የመግለጽ ኃይል አለው፡፡ ገዥው ፓርቲ አሕአዴግ ሌሎች የብዝኃነት መገለጫዎችን ለማክበር እንደተንቀሳቀሰው የሐሳብ ብዝኃነትን ግን ከማክበር ይልቅ የመድፈቅ ባህሪ ተላብሷል ተብሎ ይተቻል፡፡ ኢሕአዴግ በራሱ መሥፈርት ገዥ ሐሳብ ብሎ ካስቀመጠው አቅጣጫ ውጪ በራሳቸው መንገድ ለመጓዝ የመረጡ መገናኛ ብዙኃን ዕጣ ፈንታ መጥፋት እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም የተነሳ በአደጉት አገሮች ያሉት እንደ አሸን የፈሉ የሚዲያ ተቋማትን ለንፅፅር ማቅረቡ ቢቀር፣ እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ባሉት አገሮች ደረጃ እንኳን 90 ሚሊዮን በላይ ለሚገመተው ዥንጉርጉር ሕዝብ የሚመጥን የሚዲያ አቅርቦት እንዳይኖር ያደረገው፣ የመንግሥት አመለካከትና ፖሊሲ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡
በተቃራኒው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በቁጥጥሩ ሥር ከሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን ውጪ ያለው የግል ፕሬስ በነፃነት እንዲንቀሳቀስና የፈለገውን ሐሳብ እንዲያንፀባርቅ የሕግ ማዕቀፍ በማውጣት፣ ፖሊሲ በመቅረፅና አስቻይ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ረጅም ርቀት መጓዙን ያስረዳል፡፡
በዕለቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ / ፍሬሕይወት አያሌውም ይህንኑ አቋም አፅንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ፕሬስ በነፃ የመናገርና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት የተጎናፀፈው እየገነባነው ባለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው፡፡ መንግሥት የፕሬስ ነፃነትን ለማስጠበቅ ባለፉት ሁለት አሥርት በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ መንግሥት ሰፊ የመረጃ ምንጭ በመሆኑ ለመረጃ ነፃነት የሚያግዙ መሠረታዊ ልማቶችን በመዘርጋት፣ የአሠራር ማዕቀፎችን በየጊዜው እየፈተሸ በማሻሻል፣ የዘርፉን የሰው ኃይል በክህሎትና በቴክኖሎጂ የሚደግፍ አሠራር በመዘርጋት ረጅም ርቀት ተጉዟል፤›› ብለዋል፡፡
ይህን የወ/ ፍሬሕይወት ሐሳብ በጽሕፈት ቤቱ የሚሠሩት አቶ ታምራት ደጄኔ፣ ‹‹የግንቦት ሃያ ትሩፋቶች፣ የሐሳብ ብዝኃነትና የፕሬስ ነፃነት በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት በዝርዝር አብራርተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሐሳብ ብዝኃነትን የሚደግፍ የሚዲያ ኢንዱስትሪ እንዳለ ሲከራከሩም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ 30 የግል ጋዜጦች፣ 20 የግል ብሮድካስት ሬዲዮ ጣቢያዎች፣ 28 ማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች፣ እንዲሁም ከሞላ ጎደል ሁሉም ክልሎች ራሳቸው የሕዝብ ሚዲያ ገንብተው በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡
ከእነዚህ መገናኛ ብዙኃን ተቋማት መካከል አብዛኞቹ አንድ ሐሳብ የሚያቀነቅኑ ናቸው፡፡ በአንፃሩ 1984 .. እስከ 1987 .. ድረስ ባሉት ጊዜያት በሥራ ላይ የነበሩት 265 ጋዜጦችና 120 መጽሔቶች የሙያ ሥነ ምግባርና ገለልተኝነታቸው ላይ ጥያቄ የሚቀርብባቸው ቢሆንም በብዝኃነት የሚታሙ አልነበሩም፡፡
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ መሠረት አታላይም በአገሪቱ የሐሳብ ብዝኃነት እየዳበረ እንደሚገኝ፣ የደርግ ባለሥልጣናት እየጻፉ ያሉትን መጻሕፍት በምሳሌነት በመጥቀስ ሞግተዋል፡፡ ‹‹አንዳንድ የነፃነትና የመብት ተከራካሪ ነን የሚሉ ምዕራባዊ ድርጅቶች ሰሞኑን በአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ባሠራጩት መግለጫ ኢትዮጵያ ውስጥ የቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) ፕሬሱን አስሮና ጠፍንጎ ይዞታል በማለት መኮነናቸው፣ በየትኛውም አተያይ ተቀባይነት አለው ብለን አናምንም፡፡ ሳንሱር ቢኖር ኖሮ ዛሬ በየመንገዱ የምናያቸውን በርካታ መጻሕፍት አናይም ነበር፡፡ ሌላው ቢቀር አንዳንድ የደርግ የቀድሞ ባለሥልጣናት ከእስር ቤት መልስ ምን ይዘት ያላቸው መጻሕፍት እያስነበቡ እንደሆነ ዓይቶ የፕሬስ ነፃነት ምን ዓይነት ገጽታ እንዳለው መናገር ይቻላል፡፡ ሌሎች በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙ የሕግ ታራሚዎች በተለይም ካለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ወዲህ እየጻፉ የሚያስነብቡን መጻሕፍት ምን ዓይነት እንደሆኑ በመመልከት ስለአገሪቱ የፕሬስ ነፃነት ገጽታ መረዳት ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡
የአቶ አብዱ ዓሊ ሒጂራ ሐሳብ ለየት ብሎ የቀረበው በእነዚህ ተመሳሳይነት አቋሞች መሀል ነው፡፡ ‹‹ፕሬስ በገዛ ራሱ የሚያዝ፣ ነፃና ዥንጉርጉር የሆነ መሆን አለበት፡፡ በገዛ ራሱ የሚያዝ ማለት በቁሳቁስም፣ በመሠረተ ልማትም (ታህታይ መዋቅር) ማለት በማተሚያ ቤት፣ ማሠራጫው በማንም ቁጥጥር ሥር ያልሆነ፣ በኢኮኖሚም ቁጥጥር የማይደረግበት ነው፡፡ ዥንጉርጉርነቱ ደግሞ ሐሳብንና እውነትን በሞኖፖል ያልያዘ ፕሬስ ይኑር ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡ በእርግጥም በእነዚህ መሥፈርቶች በባለቤትነትና ተቋማዊ ይዘት ልዩነት ቢኖርም የሐሳብ ብዝኃነት ግን ለአገሪቱ ብርቅ የሆነ ይመስላል፡፡ 
መረጃ የማግኘት መብት እንደ ማሳያ
መረጃ የማግኘት መብት ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 29 ላይ ካሰፈራቸው ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽ አስፈላጊ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29(3) () የፕሬስ ነፃነት የሕዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት ዕድልን እንደሚያካትት ይደነግጋል፡፡ ‹‹መረጃ የማግኘት መብት መሠረታዊ መብት እንደመሆኑ ዕድል ተብሎ መቀመጡ አግባብ አይመስለኝም፡፡ ደግነቱ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ቀራጮች ይህ መብትና ነፃነት የሚተረጎመው ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር በተስማማ ሁኔታ እንደሆነ በማስቀመጣቸው ዓውዱን ለመሳት የሚያፈናፍን አይደለም፤›› ያሉት አቶ አብዱ፣ኢንፎርሜሽንየሚለውን ቃልመረጃብሎ መተርጎሙ የሚገልጸው እንዳልሆነም አስገንዝበዋል፡፡
አቶ አብዱ የኢንፎርሜሽን ነፃነት ማለት በመንግሥት ወይም በመንግሥት አካላት እጅ የሚገኝ ኢንፎርሜሽንንና እሱን ማግኘት በሚገዛው የሕዝብ ማዕቀፍ ውስጥ ያለውን ኢንፎርሜሽን የማግኘት ነፃነት ነው ሲሉ ተርጉመውታል፡፡ ‹‹በመንግሥት እጅ ያለ ኢንፎርሜሽን ማለት መንግሥት ባለአደራ ሆኖ ይያዘው እንጂ የሕዝቡ ነው፡፡ በውክልና ሥልጣኑ ምክንያት ሥራውን ሲያካሂድ አመነጨው፣ አጠራቀመው፣ አስቀመጠው እንጂ ባለቤትነቱ የሕዝብ ነው፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡
ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ማንም ሰው በማንኛውም መገናኛ ሥርዓት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ድንበር ሳይወስነው ኢንፎርሜሽን በመሻት፣ በመቀበልና በማሠራጨት ነፃነት እንደሚገለጽ ያስታወሱት አቶ አብዱ፣ ‹‹አንዱ ደግሞ ያለ ሌላው አይኖርም፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው በፕሬስ አማካይነት ነው፤›› ብለዋል፡፡
ሰኔ 24 ቀን 2000 .. የፀደቀው የመረጃ ነፃነት ሕግ ሦስት የዝግጅት ዓመታትን ከወሰደ በኋላ ባሉት ዓመታት ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡ አቶ አብዱ፣ ‹‹እውነት ተፈጻሚነቱ ተጀምሯል? ያመነጨነውን ኢንፎርሜሽን የማሰባሰብ፣ ያሰባሰብነውን የማስቀመጥ፣ ያስቀመጥነውን ኢንፎርሜሽን ስንፈልግ የማግኘት ሥርዓት አለን ወይ?›› ሲሉ ምላሹን ለተሳታፊዎቹ ትተዋል፡፡
ይሁንና የሚስጥራዊነት ባህል በሰፈነበት ማኅበረሰብና ይህም የተቋማቱ መገለጫ በሆነበት ዓውድ የመረጃ ነፃነት ሕጉን ተግባራዊ ማድረግ ትልቅ ተግዳሮት እንደሆነ አቶ አብዱ ይቀበላሉ፡፡ ‹‹ሚስጥራዊነትን ከመንግሥት አሠራር ለማስወገድ አብዮት ማድረግ አለብን፡፡ የሚስጥር ሕጎቻችንም ሥራ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ የመንግሥት ሠራተኛ መጀመሪያ ትኩረት የሚሰጠው ሚስጥር የመጠበቅ ጉዳይን ነው፡፡ አሁንም ድረስ እውነት በመናገርና በታማኝነት በመሥራትና ሚስጥር በመያዝ መካከል ያለው ልዩነት ግልጽ ሆኖ አናይም፤›› ሲሉም ምልከታቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ ታምራት የሚስጥራዊነት ባህልን ጨምሮ በርካታ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፣ የመረጃ ነፃነት ሕጉ 2002 .. ጀምሮ በሥራ ላይ እንደዋለና እየተሠራበት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የመረጃ ነፃነት ሕጉ አፈጻጸም ያለበትን ደረጃ ለመገምገም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ያስቀመጣቸውን ዘጠኝ መሥፈርቶች ተጠቅመዋል፡፡ መሥፈርቶቹ የግልጽነት መርህ፣ የማተም ግዴታ፣ የመንግሥትን ግልጽ አሠራር ማስፋፋት፣ የመረጃ ገደብን በልዩ ሁኔታ መፈጸም፣ መረጃ ለማግኘት የሚወጣ ወጪን የተመጣጠነ ማድረግ፣ ስብሰባዎችን ክፍት ማድረግ፣ ለመረጃ ተደራሽነትና ክፍትነት ቅድሚያ መስጠትና ለመረጃ አፈትላኪዎች ጥበቃ ማድረግ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ እነዚህን መሥፈርቶች ከሞላ ጎደል እንደሚያሟላ ያስረዱት አቶ ታምራት፣ በተግባር በሕጉ መሠረት እየተሠራ ስለመሆኑ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በተመድ ውሳኔ መሠረት ... 1993 ጀምሮ በመላው ዓለም ይከበራል፡፡ በዓሉ ሲከበር አራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር ተመድ ያሳስባል፡፡ እነዚህም የፕሬስ ነፃነት መርሆዎች፣ የፕሬስ ነፃነት ወቅታዊ ሁኔታ፣ የሚዲያ ተቋማት ነፃነትና በሚዲያ ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ናቸው፡፡ በዓሉ በኢትዮጵያ ሲከበር የመንግሥት ተቋማትን የሚወክሉ ተሳታፊዎች ግን በመርሆዎችና በሕግ ማዕቀፍ ላይ በማተኮር ተግባራዊ ግምገማን ወደኋላ ሲገፉ ይታያሉ፡፡
ከዚህ አኳያ አቶ ታምራት የፕሬስ ነፃነትን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ የሚታዩ ክፍተቶችን መንግሥት በአግባቡ ለይቶ ለመፍታት አንዳንድ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ መንግሥት የፕሬስ ነፃነት አተገባበር ተግዳሮቶች ብሎ ከለያቸው መካከል የተጠናከረ የጋዜጠኞች ማኅበር፣ የአሳታሚዎች ማኅበርና የፕሬስ ካውንስል አለመኖር፣ በኩባንያ ባለቤትነት ይዞታ ላይ የተጣለው 15 በመቶ ቁጥጥር ገደብ መሻሻል አለማሳየቱ፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለቤትነት በኢትዮጵያዊያን ሊሆን እንደሚገባ ማስቀመጡና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ያላካተተ መሆኑ፣ የሚዲያ ኢንዱስትሪው በተለይ የብሮድካስት ከዲጂታላይዜሽን ፕሮግራሙ በፊት ቀድሞ መስፋፋት መጀመሩ፣ ለሚዲያውና በዘርፉ ለተሰማሩ ተዋንያን የማበረታቻ ማዕቀፍ አለመኖሩና ይልቁንም የሚያቀጭጭ የግብር አሠራር መኖሩ፣ የመንግሥት ማስታወቂያ በጀት አጠቃቀም ሚዲያውን ሊያለማ በሚያስችል ቅኝት አለመመራቱና በመንግሥት ተቋማት መረጃ ተደራሽ ለማድረግ ዝርዝር አሠራር አለመዘርጋቱ ተጠቃሽ እንደሆኑም አቶ ታምራት ዘርዝረዋል፡፡
መንግሥት እነዚህን ተግዳሮቶች ለይቶ መፍትሔ ለመስጠት ከልብ እየሠራ ከሆነ ሊበረታታ የሚገባውና ለውጥ የሚያመጣም እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይሁንና በቀረቡት ጥናታዊ ወረቀቶች ላይ አስተያየታቸውን የገለጹ ተሳታፊዎች የተወሰኑትን ተግዳሮቶች እንደማይቀበሉ መግለጻቸው፣ ምናልባትም በመንግሥት አካላት ዘንድ ሙሉ ስምምነት እንደሌለ አመላካች ነው፡፡ በሌላ በኩል የሐሳብ ብዝኃነትን እንደ ማጥ ለሚያይ መንግሥትና አገር ከሙገሳ ባሻገር ያሉ ትችቶችና ለየት ያሉ አስተያየቶችን ያለመቀበል አባዜ መገለጫ ይሆናል፡፡     

 Source: Ethiopian Reporter

No comments: