Wednesday, May 25, 2016

በምዕራብ ሸዋ ጊንጪ ተቃውሞ ተቀሰቀሶ የትራንስፖርትና የትምህርት አገልግሎት ተቋረጠ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ በምትገኘው የጊንጪ ከተማ ዳግም ተቃውሞ መቀስቀሱንና የትራንስፖርትና የትምህርት አገልግሎት ከማክሰኞ ጀምሮ መቋረጡን ነዋሪዎች ለኢሳት አስታወቁ።

ተቃውሞ ጨርሶ አልተቋረጠም ሲሉ የገለፁት ነዋሪዎች የጸጥታ ሃይሎች አሁንም ድረስ በከተማዋ ዙሪያ በመሰማራት በህብረተሰቡ ላይ ፍርሃትን አሳድረው እንደሚገኙ ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው መናገር ያልፈለጉ እማኞች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

በነዋሪዎች ሲነሱ የነበሩ የተለያዩ የአስተዳደርና የመብት ጥያቄዎች በግባቡ ምላሽ አለማግኘታቸው ተቃውሞው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረጉንም ከነዋሪዎቹ ለመረዳት ተችሏል።

ከማክሰኞ ጀምሮ በከተማዋና በዙሪያው ባሉ የገጠር መንደሮች የተቀሰቀሰው ይኸው ተቃውሞ በነዋሪዎቹ ዘንድ የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን እያስነሳ እንደሚገኝም ታውቋል።
በከተማዋ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎም የጸጥታ ሃይሎች በነዋሪዎች ላይ የሃይል እርምጃ መውሰድ መጀመራቸውና በርካታ መኖሪያ ቤቶችንም ብርበራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ እማኞች ገልጸዋል።

በተለያዩ የኦሮሚያ ክልሎች አሁንም ድረስ ግድያና እስራት ቀጥሎ እንደሚገኝ የተናገሩት ነዋሪዎች በፀጥታ ሃይሎች እየተወሰደ ያለው የሃይል እርምጃ በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል።

የገቡበት ያልታወቀ ተማሪዎችና ነዋሪዎች ሁኔታ መጣራት አለበት ሲሉ ቅሬታቸውን በመግለጽ ላይ ያሉት ነዋሪዎች በጊንጪ ከተማ የተቀሰቀሰው ዳግም ተቃውሞ ወደ አምቦ መዛመቱንና የጸጥታ ሃይሎች ወደ አካባቢው እየተሰማሩ መሆኑንንም አስታውቀዋል።
በወታደራዊ አስተዳደር ስር ነው የምንገኘው በማለት በጊንጪና አካባቢዋ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ለኢሳት ያስረዱት እማኞች በባለስልጣናት የተሰጡ መግለጫዎችና ውይይቶች ህብረተሰቡን ሊያሳምኑ እንዳልቻሉም ገልጸዋል።

በተያዘው ሳምንት በሃረማያ ዩኒቨርስቲ ተመሳሳይ ተቃውሞ ዳግም አገርሽቶ የሚገኝ ሲሆን አንድ የዩኒቨርስቲ ተማሪም በዚሁ ተቃውሞ በጸጥታ ሃይሎች መገደሉን ማክሰኞ መዘገባችን ይታወሳል።

በክልሉ ድጋሚ ተቀስቅሶ የሚገኘው ይኸው የነዋሪዎች ተቃውሞ ከምዕራብ ሸዋ በተጨማሪ በወለጋና ምስራቅ ሃረርጌ አካባቢዎች በመዛመት ላይ መሆኑንም ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

ኢሳት



No comments: