Wednesday, May 11, 2016

የመከላከያ ሠራዊትን አደረጃጀትና የሚገኝበትን አድራሻ አሳልፎ በመስጠት የተጠረጠሩ ወታደሮች ተከሰሱ

የተጣለባቸውን አገራዊ አደራ ወደ ጎን በመተው፣ ራሱን አግአዴን (አርበኞች ግንቦት ሰባት) ለሚባለው ድርጅት፣ የኢፌዴሪ የመከላከያ ሠራዊትን አደረጃጀትና የሚገኝበትን አድራሻ አሳልፈው በመስጠት የተጠረጠሩ ሁለት ወታደሮች የሽብር ተግባር ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 14 ወንጀል ችሎት በተከሳሾቹ ምክትል አሥር አለቃ አጃናው ታደሰና ምክትል አሥር አለቃ ቻሌ ነጋ ላይ ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ የአርበኞች ግንቦት ሰባት የዘመቻ መምርያ ኃላፊ ለሆነው ክፈተው አሰፋ ወይም ዶክተር ከኤርትራ ኦማጆር አካባቢ ስልክ እየተደወለላቸው መረጃዎችን ማቀበላቸውን ገልጿል፡፡
ተከሳሾቹ የመከላከያ ሠራዊት 6 እና 25 ክፍለ ጦር የሚገኙ ሬጅመንቶችን ብዛትና የት እንደሚገኙ፣ የራሳቸው የተከሳሾቹ ክፍለ ጦር ስንተኛ እንደሆነ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሲጠየቁ፣ እያንዳንዱ ክፍለ ጦር የት እንደሚገኝ አካባቢውንና የክፍለ ጦሩን አድራሻና ምድብ ቦታ ማሳወቃቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ከአንደኛው ዕዝ ወደ ሌላኛው ሠራዊት እየተቀላቀለ ወደ ሌላኛው ዕዝ እንደሚዘዋወር፣ በስልክና በቫይበር ግልጽ ማስረጃዎችን ተከሳሾቹ ለድርጅቱ ማሳወቃቸውን አስታውቋል፡፡
በአጠቃላይ ተጠርጣሪዎቹ በተለይ የአገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር የገቡትን ቃል ኪዳን ወደ ኋላ በመተውና የአግአዴን/አርበኞች ግንቦት ሰባት ድርጅትን ተልዕኮ በመቀበል፣ የመከላከያ ሠራዊትን አደረጃጀትና የሚገኝበትን አድራሻ መረጃ አሳልፈው ለመስጠት፣ ከድርጅቱ ታጣቂዎች ጋር ለመቀላቀልና የድርጅቱ ተስፋ በመሆን በፈጸሙት በሽብር ቡድን በማንኛውም መልክ መሳተፍ ወንጀል እንደተከሰሱ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ አቅም እንዳላቸውና እንደሌላቸው ሲጠይቃቸው አቅም እንደሌላቸው ስለገለጹ፣ ተከላካይ ጠበቆች ጽሕፈት ቤት እንዲያቆምላቸው ትዕዛዝ ሰጥቶ ክስ ለመስማት ለግንቦት 15 ቀን 2008 .. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Source: Ethiopian Reporter

No comments: