Tuesday, May 31, 2016

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ የሚደረገው ጫና ተጠናክሮ ቀጥሏል


በቃሊቲ ወህኒ ቤት በሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ በእስር ቤቱ ሃላፊዎች የሚደረገው ጫና ተጠናክሮ መቀጠሉ ታወቀ።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት 18 አመት እስራት ተፈርዶበት በወህኒ ቤት የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ከቤተሰብ እንዳይገናኝ ተከልክሏል፣ ስንቅ እንዳይገባለትም ዕገዳ ተጥሎበታል።
መስከረም 2003 ዓም ጀምሮ ላለፉት 5 አመታት ያህል በአሸባሪነት ተከሶና ተፈርዶበት በወህኒ ቤት የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ቀደም ሲል መጽሃፍ እንዳይገባለት የተደረገ ሲሆን፣ ማናቸውም ጽሁፍ እንዳይጽፍ ባዶ ወረቀቶችን እንዲሁም ወንበርን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጽህፈት ማሳሪያዎችን እንደተወሰደበት መረዳት ተችሏል።
1985 ዓም ጀምሮ በኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ውስጥ ግንባት ቀደም ከነበሩት ጋዜጠኞችና የፕሬስ ባለቤቶች አንዱ ሆኖ የዘለቀው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ቀደም ሲል ለሰባት ጊዜያት ያህል የታሰረ ሲሆን፣ የአሁኑን ጨምሮ ሁሉም ክሶች ሃሳቡን በፁሁፍ ከመግልጹ ጋር የተያየዘ መሆኑን መረዳት ተችሏል።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከቤተሰብ እንዳይገናኝ፣ ወይንም በቤተሰብ እንዳይጠየቅ ስለተከለከለበት ምክንያት የታወቀ ነገር የለም።


ኢሳት

No comments: