Sunday, April 26, 2015

ደህንነቶች የታሰሩት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ከፓርቲያቸው እንዲለቁ ጫና እያደረጉ ነው

መንግስት አይ ኤስ አይ ኤስ በኢትዮጵያውያውያን ላይ የፈፀመውን የጭካኔ እርምጃ ለመቃውም በጠራው ሰልፍ ላይ ተይዘው የታሰሩት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ከፓርቲው እንዲለቁ ደህንነቶች ጫና እያደረጉ መሆኑ ታወቀ፡፡ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ እስር ቤቶች ታስረው የሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትን ደህንነቶች ከፓርቲያቸው እንዲለቁ ጫና እያደረጉ እንደሆነና ከፓርቲው ከለቀቁ እንደሚፈቷቸው መግለጻቸው ታውቋል፡፡

በተለይ ካሳንቺስ ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙትን ወይንሸት ሞላንና ዳንኤል ተስፋዬን ሌሊት ሌሊት ከታስሩበት በማስወጣት ለረዥም ሰዓት ከታሰሩበት ጉዳይ ጋር የማይገናኝ ከፍተኛ ምርመራ እንደሚያደርጉባቸውና ከፓርቲው ካልለቀቁ በስተቀር እንደማይፈቱ እንደሚያስፈራሩዋቸው ተገልጾአል፡፡ በሰማያዊ ፓርቲ አባላት ላይ የሚደረገው አብዛኛው ምርመራ ፍርድ ቤት ላይ ፖሊስ ካቀረበባቸው ‹‹ሁከትና ብጥብጥ›› ክስ ጋር የማይገናኝና በፓርቲው ውስጣዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል በሰልፉ ወቅት ታፍሰው ከታሰሩት መካከል የሰማያዊ ፓርቲ አባል ያልሆኑትን ‹‹የሰማያዊ ፓርቲ አባል ነኝ፡፡ ፓርቲው ብጥብጥ እንዳስነሳ ልኮኝ ነው ወደ ሰልፉ የመጣሁት›› ብለው እንዲፈርሙ እያስገደዱ መሆኑን ምንጮች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ በርካታ የገዥው ፓርቲ አባላትም በአፈሳው ወቅት ተይዘው የታሰሩ ሲሆን አብዛኛዎቹ ከቀበሌ የምስክር ደብዳቤ አምጥተው መለቀቃቸውን ምንጮች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

No comments: