Thursday, April 16, 2015

በውጪ ዜጎች ላይ የተከፈተ አመጽ መባባሱ ተነገረ


ኢትዮጵያዊያን የድረሱልን ጩኸታቸውን አሰምተዋል
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሰሞኑን የጀመረው የውጪ ዜጎችን ኢላማ ያደረገው ጥቃት ተባብሶ መቀጠሉ ተነገረ፡፡ የበርካታ ሀገራት ዜጎች በስለት እታረዱ፣ በእሳት እየተቃጠሉ፣ ንብረታቸው እየተዘረፈና እየወደመ እንዲሁም እየተገደሉ እንደሚገኝ በርካታ የአለም ሚዲያዎች ዜናውን በመቀባበል ላይ ይገኛሉ፡፡
እዛው ደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በስልክ ደውለው እንደነገሩን ከሆነ እነሱን ራሳቸውን ጨምሮ የሌሎች አፍሪካ ሀገራት መጤ ዜጎች እየታደኑ በመደብደብ፣ በስለት በመጨፍጨፍና በመገደል ላይ እንደሚገኙ ነው የገለጹልን፡፡ በጆሀንስበርግና ደርባንን በመሳሰሉ ከተሞች በተለይ አመጹ ተፋፍሞ እንደቀጠለ የገለጹልን ኢትዮጵያዊያኑ በእስከአሁን ሂደት ሁለት ኢትዮጵያውያን ለሞት እንደበቁ ነው የነገሩን፡፡
አሁን የምንገኘው ቤታችንን ዘግተን ነው ሲሉ የሚናገሩት ኢትዮጵያዊያኑ ቤት ለቤት በዘመቻ የውጪ ዜጎችን እያደኑ ማጥቃት እንደሚካሄድና ያሉበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ነው ፍራቻቸውን ጨምረው የተናገሩት፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያዊያን እንደተናገሩት ከሆነ ደቡብ አፍሪካዊያኑ እያጠቁ ሉት እነሱንና የአንዳንድ አፍሪካ ዜጎችን እንጂ በሀገሪቱ በብዛት የሚኖሩትን ነጮችን፣ ህንዶችንና እስያውያንን እንዳልሆነ ሁኔታውን በሀዘን ስሜት ገልጸውልናል፡፡
የዚምባብዌ፣ የናይጄሪያ፣ የናሚቢያና የበርካታ ሀገራት ኤምባሲዎችና መንግስታት ተወካዮች ሌላው ቀርቶ የሶማሊያ ኤምባሲ እንኳን ዜጎቻቸውን መሰብሰብና ከጥቃት ጠብቀው ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ፈጣን ርብርብ እያደረጉ እንደሚገኙ በቁጭት የተናገሩት እኒሁ አስተያየታቸውን የሰጡን ኢትዮጵያዊያኑ በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ግን አንዳችም እርምጃ ሲወስድ እንዳላዩ ትዝብታቸውን ገልጸው የሚመለከተው ሁሉ በቶሎ ይድረስልን ሲሉ ነው አቤቱታቸውን የነገሩን፡፡
ይህን የኢትዮጵያዊያኑን አቤቱታ በተመለከተ ከትናንት ጀምሮ አዲስ አበባ ለሚገኘው የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ስልክ በመደወል መንግስት ምን አይነት ምላሽ በመስጠት ላይ እንዳለ ለመጠየቅ ስናደረግ የቆየነው ተደጋጋሚ ሙከራ እስከአሁን አልተሳካልንም፡፡ በዚህ ጉዳይ አለሁ የሚሉ የመንግስት አካላት የሚሰጡትን ምላሽ እንዳገኘን ይዘን የምንቀርብ ነው የሚሆነው፡፡ የዘገባውን ዝርዝር ይዘነዋል፡፡

No comments: