Wednesday, April 15, 2015

ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ!

(የትነበርክ ታደለ)
ሀገራችን ኢትዮጵያ ለደቡብ አፍሪካ ያደረገችውን ያህል ለሌሎች አፍሪካ አገራት አላደረገችም ብንል ማጋነን አይሆንም። በአፓርታይድ ጡንቻ ስትደቆስ ቆይታ ከሌሎች አገራት ሁሉ መጨረሻ ነጻነቷን የተጎናጸፈችውና ለ27 አመታት በእስር የቆየው ኔልሰን ማንዴላ አገር ደቡብ አፍሪካ ፊትዋን ወደ ምስራቋ ጸሀይ የጥቁሮች ተስፋና መነቃቂያ ወደ ሆነችው የያኔዋ ልእልት አገራችን እያየች ነበር የስልጣን ቁልፉን ከነጭ ገዢዎቿ እጅ የተቀበለችው።
ሌሎች አፍሪካ አገራት እንኳንስና ለመረዳዳት ለራሳቸውም በሁለት እግር መቆም ባልቻሉበት በዚያ ጨለማ ጊዜ ኢትዮጵያን ብሎ አገር አቆራርጦ የመጣውን የነጻነት ጥም የተጠማውን ማንዴላን በክብር ተቀብላ፤ አሰልጥናና አስታጥቃ ልካለች።
ከዚያም አልፎ ደቡብ አፍሪካ ነጻነትዋን ካገኘች በሁዋላም ቢሆን፤ ሁላችንም በየትምህርት ቤታችን ዘምረንላታል። እነዚያ ትላንት በነጭ ፖሊሶች እየተሳደዱ በዉሾቻቸው ሲበሉ የነበሩ ደቡብ አፍሪካውያን፤ ትላንት እዚህ ትምህርት ቤት አትማሩም፣ እዚህ ሆስፒታል አትታከሙም ሲባሉ የነበሩ የአህጉራችን ልጆች ዛሬ በሀገራቸው ሰውነታቸው ተመለሰላቸው ስንል እልልል ብለንላቸዋል።
ትናንትና እንኳ ያ እድሜ ጠገብ የነጻነት አባት ማንዴላ ከዚህ አለም በሞት ሲለይ አብረን አልቅሰናል፣ አዝነናል። ደቡብ አፍሪካ ለኛ የተለየች ናት ብለን ነው የምናስበው።
ዛሬ ግን ደቡብ አፍሪካውያኑ ቅስማችንን ሰብረውታል። በዚያ በአስከፊ የባርነት ጊዜያቸው የዘረጋንላቸውን እጆቻችንን ዛሬ በአደባባይ ቆርጠውታል፣ በላስቲክ ጎማ አቃጥለውታል። ዛሬ ሶስት ሬሳ ልከውልናል። ክፉ ሟርት አይሁንና ቁጥሩ ነገ ከነገ ወዲያ ከዚህም በላይ ሊሆን ይችላል። አንድስ ነፍስ ቢሆን? ያውም ኢትዮጵያዊ እንዴት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በአደባባይ ይገደል? ለምን?
እሺ ምክኒያታቸው ምንም ይሁን ምን...ውለታችንም ይረሳ። ብድራችንም አይመለስ። የጃኮብ ዙማ መንግስት ለዚህ ዘመናችንን የማይመጥን የእንስሳት ፍርድ የሚሰጡን ምላሽ የለም? የአገራችንስ መንግስት ቢሆን በየአገሩ የተበተነውን ህዝብ መሰብሰብ ቢያቅተው እንዲህ ያለ ለሰው ልጅ ክብር በማይመጥን ሁናቴ ወንድሞቻችን በሞት ሲቀጡ ሬሳቸውን ለወላጆቻቸው ሲሰጥ ምን አይነት ምክኒያት እያቀረበ ይሆን? በአለም አቀፍ የአገራት ጉድኝት ህግ መሰረት የፕሪቶሪያን መንግስት ይጠይቅልን ይሆን? ወይስ እንደተለመደው ወገን እያለቀ ነገሩ ሁሉ እንዲሁ ይቀጥል ይሆን? ግን እኛ ማነን? ምንድነን?
ያም ሆነ ይህ ህዝብ ሲጠቃ ሀገር ተጠቃ ማለት መሆኑን ለመገንዘብ ብዙ እውቀት አይፈልግም።

No comments: