Monday, April 6, 2015

የታዳጊዋ ብሶት – እየሩሳሌም አርአያ


የታዳጊዋ ብሶት – እየሩሳሌም አርአያ

ትላንት አመሻሽ ላይ በዲሲ 16ኛው መንገድ “የእኛ እድር” የተሰኘ ድራማ ይታይ ነበር። ዝግጅቱን ለመታደም ከኢየሩስና አብራት ከምትማረው ታዳጊ ኤልሳ ጋር በስፍራው ተገኘን። ድራማው ይጀመራል ከተባለበት ጊዜ ለ1 ሰዓት ተኩል ዘግይቶ ነበር። (ሃበሻና ቀጠሮ መቼ እንደሚታረቁ አይታወቅም)…ዝግጅቱ እስኪጀምር ወግ ቀጠልን። ታዳጊ ኤልሳ አሜሪካ ከአባቷ ጋር የመጣችው ከ5 አመት በፊት ነበር።
የ16 አመቷ ኤልሳ በገፅታዋ ብሶትና መከፋት በሚታይበት መልኩ « አባቴ በተለይም አጐቴ በጣም ይረብሹኛል። “አንቺ ኦሮሞ ነሽ” ይሉኛል። አጐቴ ካርታ እያሳየኝ ኢትዮጵያዊነቴን እንድክድ ይወተውተኛል። በጣም ስለመረረኝ ዳግም እንዲህ እንዲህ አይነት ነገር እንዳያነሱብኝ ነገርኳቸው። ኢትዮጵያዊ ነኝ! አለቀ ደቀቀ! ኢትዮጵያ እያለሁ ያልነገራችሁኝን ለምን እዚህ እየነገራችሁ አገሬን ኢትዮጵያ እንድክድ እንደምትወተውቱኝ አላውቅም፤ አልኳቸው» ካለች በኋላ በሃዘን ስሜት ተውጣ « እናትና አባቴ ተለያይተዋል። አጐቴና አባቴ ፍላጐታቸው እኔ ኢትዮጵያዊነቴን እንድክድ ብሎም በፊት የማላውቀውንና አሁን የገባኝን የእናቴ አማራ መሆን እንዳልቀብል ወይም እንድቆራረጥ ነው እቅዳቸው።
እናቴና ኢትዮጵያ ለእኔ አንድ ናቸው! ሁለቱንም አልክድም! ከዚህ በኋላ ቢያስጨንቁኝ እከሳቸዋለሁ። አዎ እከሳቸዋለሁ! አይረብሹኝ» አለች በቁጣ። በውስጤ ክፉኛ አዘንኩ። በታዳጊዋ አቋም ስለተደነቅኩ ግንባሯን ሳም አደረኩና « ወደ ክስ አትሂጂ።


አሁን በያዝሽው የፍቅር ፅናት አቋም እያስተማርሽ – አሸንፊያቸው!» አልኳት። “እሺ” አለች በሙሉ ፈገግታ።.. አባቶቻችን ያላስተማሩንን ለልጆቻችን የምንሰብከው የጥላቻ መርዝ ፋይዳው ምንድነው?…በየአቅጣጫው የጥላቻና ዘረኛ መርዝ የሚያሰራጩ ወገኖች ከዚህ ድርጊታቸው ቢቆጠቡ ይበጃል! ምናልባት “ወያኔ ያመጣው ነው” ሊባል ይችላል። ነገር ግን ለልጅህ ያንን መንገድ ማሳየት አለበህ?..አንተ ለምታራግበው ጥላቻ ተጠያቂው አንተ ነህ!!…በነገራችን ላይ በተመስገን መላኩና ሰብለ እንዲሁም ሌሎች የተዘጋጀው ድራማ ድንቅ ነበር! “24 አመት የታመመችው ኢትዮጵያ” ነው ያላችሁት በድራማው!?
Source: Satenaw

No comments: