Friday, April 3, 2015

በነሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ በ19ኛው ወንጀል ችሎት እየታየ ያለው የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች የክስ ጉዳይ



በነሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ በ19ኛው ወንጀል ችሎት እየታየ ያለው የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች የክስ ጉዳይ ለሁለተኛ ቀን ምስክሮችን አሰምቶ በአወዛጋቢ መልኩ ለሚቀጥለው መጋቢት 30 ቀጠሮ ይዞ ተጠናቋል፡፡
ከእለቱ ዋዜማ ቃለ መሃላ ፈጽመው ሳይሰሙ የቀሩት ምስክሮች የተሰሙ ሲሆን ቃለ መሃላ በቀደመው ቀን በመግባታቸው ቀጥታ ወደ ምስክርነት ቃላቸው ተገብቷል፡፡ በሃያ ስድስተኛው የፍርድ ቤት ውሎ ተሰሙት ምስክሮች
7ተኛ ምስክር -ተስፋዬ መንግስቴ የመሰከሩት አቤል ዋበላ ላይ ሲሆን ከመንገድ ላይ ፓሊስ ሲፈትሹ አንዲታዘቡ ጠይቋቸው ቤቱ እና መስሪያ ቤቱ የተገኘው ሲዲ መጽሄቶች እና መጸሃፍት ላይ ሲገኙ አይቼ ፈርሜያለው አቤልም ፈርሟል ብለዋል፡፡
8ተኛ ምስክር- አቶ በረከት ጌታቸው በተመሳሳይ መንገድ ላይ ፓሊስ ታዘቡልኝ ብሎ የበፍቃዱ ሃይሉ ቤት ሲፈተሽ መታዘባቸውን በፍቃዱ የፈረመባቸው ነገሮች ላይም መፈረማቸውን ተናግረዋል፡፡ ጽሁፎቹ አማርኛ እና አንግሊዘኛ ከመሆናቸው ውጪ የሚያስታውሱት ይዘት አንደሌለ ተናግረዋል፡፡
9ኛ ምስክር - አቶ አንድነት ስሜ ይባለሉ አጥናፍ ብርሃኔ ላይ የመሰከሩ ሲሆን ቤቱ የተገኙ ወረቀቶች ላይ እሱም ፈርሟል አኔም ፈርሜያለው ብለዋል፡፡ የተገኙት ወረቀቶች አማርኛ እና እንግሊዘኛ ሲሆኑ ሴኩሪቲ ኢን ኤቦክስ የሚል መጽሃፍ አለበት ብለዋል፡፡ በይዘቱ ላይ አቃቤ ህግ አንዲመሰክሩ ቢጠይቅም ጠበቆች በይዘቱ ላይ ለመመስከር ስላልተመዘገቡ አንዳይመሰክሩ ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ እንዲመሰክሩ ቢፈቅድም ምስክሩ ምንም ይዘት አንደማያስታውሱ ተናግረዋል፡፡
10ኛ ምስክር -አቶ ታምራት ዓለሙ የሚባሉ ሲሆን አቤል ዋበላ ቤት ሲፈተሽ እንደነበሩ በመግለጽ ምስክርነታቸውን አሰምተዋል፡፡ አቤል የፈረመባቸው ነገሮች ላይ ፈርመናል ያሉ ሲሆን የነጻነት ጎህ ሲቀድ መጽሃፍ እስልምና በኢትዬጲያ የሚል መጽሃፍ አዲስ ጉዳይ መጽኄቶች አና እምነት እና ተስፋ በኢትዬጲያ የሚሊ ጽሁፎች ተገኝተዋል፡፡ ሲዲም ተገኝቷል ብለዋል፡፡ የፍተሻውን ቀን ሚያዝያ 11 ነው ብለዋል፡፡ ( ጦማሪ አቤል የታሰረው ሚያዝያ 17 አንደሆነ ይታወቃል)
11ኛ ምስክር አቶ ፋሲል ግርማ ሲሆኑ በፍቃዱ ሃይሉ ቤት ሲፈተሽ ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ቤት ውስጥ ተገኙት እቃዎች እና ሰነዶች ላይ ተከሳሹ ሲፈርም እኛም ፈርመናል ብለዋል፡፡ የተገኙትን ሰነዶች ብዛትና ይዘት እንደማያሰታውሱም ተናግረዋል፡፡
12ኛ ምስክር አቶ ደረጀ አበበ የኮንስትራክሽን እና ቢዝነስ ባንክ ባልደረባ ሲሆኑ ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ ቢሮ ሲፈተሽ ፓሊስ ታዘቡ ብሏቸው አንደነበሩ እና ተገኙት ወረቀቶች ላይ ፈርመው ቢሮውን ዘግተው መውጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ የፈረሙበትን ወረቀት ይዘት የማያስታውሱት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
13ኛ ምስክር አቶ አክሊሉ ሃይለማርያም ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ ላይ የመሰከሩ ሲሆን ስሙን ብቻ ነው የማስታውሰው በማለት ያዬትን ተናግረዋል፡፡ ፈረንሳይ ለጋሲዬን አካባቢ ያለው ቤቱ ሲፈተሽ የተገኙ አማርኛ እና እንግሊዘኛ ጽሁፎች የግል ማስታወሻዎች ሲም ካርድ እና መጽሃፍት የተገኙ ሲሆን ሁሉም ላይ በፍቃዱም ሲፈርም እኔም ፈርሜያለሁ ብለዋል፡፡
በ14ኛ ምስክርነት አቶ የማነ ብርሃኔ የተባሉ ግለሰብ ቀርበው የነበር ቢሆንም አቃቤ ህግ ‹የተለየ ነገር አያስረዱልኝም› በሚል ምስክሩ ሳይደመጡ እንዲመለሱ ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ምስክርነታቸው ሳይሰማ ቀርቷል፡፡ አቃቤ ህግ አጠቃላይ 41 ምስክሮችን እንዳስመዘገበ በመጥቀስ ትናንት ካስመዘገባቸው 17 ምስክሮች ውጭ ሌሎቹን ፖሊስ በአድራሻቸው ፈልጎ እንዳጣቸው በመግለጽ ማቅረብ አለመቻሉን አስረድቷል፡፡ በሌላ በኩል ግን 8ኛ፣ 9ኛ እና 27ኛ ላይ አቃቤ ህግ ያስመዘገባቸው ምስክሮች መጥሪያ ደብዳቤ ደርሷቸው እንዳልተገኙለት ገልጹዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የጠበቆችን (የተከሳሾችን) አስተያየት ጠይቆ ነበር፡፡ በዚህም ጠበቆቹ አሉ የተባሉትን ምስክሮች ፌደራል ፖሊስ ሌሎችን በአድራሻቸው ፈልጎ ማቅረብ ይገባው እንደነበር፣ እግዚቢት ላይ የተመሰከሩት ቃሎችን ፍ/ቤቱ እንዳይመዘግባቸው ማመልከት፣ እንዲሁም ያልተካዱ ዶክሜንቶች ላይ ምስክር መስማቱ ተገቢ እንዳልሆነ በአስተያየታቸው አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም አቃቤ ህግ ቀሪ ምስክሮችን ማሰማት ካለበትም ምስክሮቹን በተሰጠው ቀን ( የማስረጃ መስማት ለሶሰት ተከታታይ ቀናት አንደተቀጠረ ይታወሳል) እንዲያቀርብ በማሳሰብ የደንበኞቻቸው የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት በፍርድ ቤቱና በአቃቤ ህግ በኩል እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡ በተለይ ባልተካዱ ዶክሜንቶች ላይ ይህን ያህል ጊዜ መውሰዱ ተገቢ አይደለም ብለዋል ጠንካራ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ ጦማሪ ናትናኤል በበኩሉ ‹‹አቃቤ ህግ ያቀረበውን ሰምተናል፤ እኛ ብቻችንን አይደለም የታሰርነው፤ ቤተሰቦቻችንና ጓደኞቻችንም አብረውን ታስረዋል፡፡ በህሊና እና በኢኮኖሚ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰብን ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ሁሉ ‹ውሳኔው ላይ አብሮ እንዲታይልን እናመለክታለን ብሏል፡፡
ፍርድ ቤቱ የጠዋት ምስክር መስማቱን ሂደት አጠናቆ ለከሰአት ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ከሰጠ በኋላ ከሰአት በኋላ ሁለት ጉዳዬች ብይን ሰጥቷል፡፡ የመጀመሪያው የምስክሮች ቃል ከመዝገቡ ጋር አንዲያያዝ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቀሩ የተባሉት ሶስት ምስክሮች ታስረው ለመጋቢት 30 አንዲቀርቡ እና አቃቤ ህግ ተጨማሪ ምስክሮች አሉኝ ካለም አንዲያቀርብ ነው፡፡በዚህም መሰረት ለሶስት ቀን የታቀደው ምስክሮችን መስማት በአንድ ቀን ከግማሽ ተጠናቋል፡፡ ጠበቆች አቃቤ ህግ ቀድሞ በተወሰነው ቀን ምስክሮችን ሊያቀርብ ሲገባ ሌላ ቀነ ቀጠሮ መሰጠት የለበትም በማለት ያቀረቡትን ተቃውሞ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ አቃቤ ህግ በበኩሉ ምስክሮቹን በፌደራል ፓሊስ እያስፈለኩ ስለሆነ ተከሳሾ ማረሚያ ቤት እንዳሉ ለፍለጋው ጊዜ ይሰጠኝ ብሎ ነበር ፡፡
ጠበቆቹ አቃቤ ህግ የእግዚቢት ሰነዶችን በተመለከተ የመዝገብ ቁጥሩን ገልጾ እንዲቀርብ በጠየቁት መሰረት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ በትዕዛዙ መሰረት አቃቤ ህግ ዛሬ የመዝገብ ቁጥሩን ይዞ መቅረብ የነበረበት ቢሆንም፣ ጠበቆቹ ይህንኑ ጉዳይ በማንሳት ሲጠይቁ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አልሰጠንም በሚል ክዷል፡፡
የዞን9 ማስታወሻ
አቃቤ ህግ የሌሉትን ምስክሮች ፍለጋ በማለት ለሚያባክነው ጊዜ ፍርድ ቤቱ አንደተለመደው ተባባሪ መሆኑ የፍትህ ስርአቱን በአጠቃላይ እና ይህንን መዝገብ ሂደት ይበልጥ አሳፋሪ አድርጎታል፡፡ አሁንም ቢሆን የተከሳሾች አፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብት ተጠብቆ ሁሉም ተከሳሾች ነጻ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ አጥብቀን እንጠይቃለን ፡፡ ያልተሰራ ወንጀል ምስክር አይገኝለትም ፡፡
ዞን9

No comments: