Friday, April 3, 2015

ኢሜግሬሽን በኢ/ር ይልቃል ጌትነት ጉዳይ ላይ መልስ መስጠት አልቻለም



• ‹‹ይህ ሁሉ ከአቅመ ቢስነታቸው የመነጨ ነው›› ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
የኢሜግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ጉዳይ ላይ መልስ መስጠት አለመቻሉንና ይህም ሆን ተብሎ ጉዟቸውን ለማጓተትና እንቅስቃሴያቸው ለመግታት የተደረገ ነው ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ የኢሜግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ በትናንትናው ዕለት ቀጠሮ ሰጥቷቸው የነበር ቢሆንም ምንም አይነት ምክንያትና መፍትሄ ሳይሰጥ ለዛሬም ሌላ ቀጠሮ ተሰቷቸው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ይሁንና በዛሬው ዕለትም የኢሜግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ሲሄዱ ‹‹ፓስፖርቱ እኛ ጋር አልደረሰም፡፡ ቆይተው ደውለው ይጠይቁ›› ብለው ስልክ እንደሰጧቸው ገልጸዋል፡፡ ይህም ሆን ተብሎ ጉዞውን ለማጓተት የተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ሊቀመንበሩ አክለውም ‹‹ይህን ሁሉ የሚያደርጉት አገር የማስተዳደር ብቃት ስለሌላቸው፣ የፖለቲከኛን እንቅስቃሴ በማጓተትና በማገድ የተፈጠረባቸው ስጋት የሚቀርፉ ስለሚመስላቸው ነው፡፡ እንደ አጠቃላይ ከአቅመ ቢስነታቸው የመነጨ ነው›› ብለዋል፡፡ በምርጫ ክርክር ወቅት ኢህአዴግ ሰማያዊ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ጋር ያለውን ግንኙነት አሉታዊ አድርጎ እንዳቀረበ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ የኢህአዴግ ሚዲያዎችም ይህን አቋም እየተደጋገመ እንደሆነ የገለጹት ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ሰማያዊ ፓርቲ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያለው ተቀባይነት፣ እነዚን ኢትዮጵያውያን እያንቀሳቀሰ መሆኑና አቅማቸውን ለመጠቀም ዝግጁ መሆኑ በጣም አስፈርቶታል ብለዋል፡፡

No comments: