Tuesday, April 21, 2015

ሰማያዊ ፓርቲ የነገውን ሰልፍ እንደሚደግፍ አስታወቀ

ሰማያዊ ፓርቲ ሊቢያ ውስጥ አይ ኤስ አይ ኤስ የተባለው አሸባሪ ቡድን በኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን አረመኔያዊ እርምጃ ለመቃወም የተጠራውን ሰልፍ እንደሚደግፍ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታወቀ፡፡ ኢትዮጵያውያን ሰልፉን እንዲቀላቀሉም ጥሪ አቅርቧል፡፡ ሙሉውን የመግለጫው አካል ከስር ይመልከቱ!
ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ!
ኢትዮጵያውያን አደባባይ ወጥተው ሀዘናቸውን እና ተቃውሟቸውን እንዲገልጹ የተጠራውን ሰልፍ እንደግፋለን!
ሊቢያ ውስጥ በወገኖቻችን ላይ የተፈፀመውን አረመኔያዊና አሰቃቂ ግድያ ዜጎች አደባባይ ወጥተው እንዲያወግዙ የተጠራውን የተቃውሞ ሰልፍ ሰማያዊ ፓርቲ እንደሚደግፈው እንገልፃለን፡፡
ዛሬ ማክሰኞ 13/2007 ዓ.ም በርከት ያሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መንግስት በዜጎቻችን ላይ የተፈፀመውን አረመኔያዊ ግድያ ትኩረት እንዲሰጠው ለማሳሰብና ቸልተኝነቱን ለመቃወም ወደ ቤተ መንግስት በማቅናት ላይ እያሉ ፖሊስ በኃይል እንዲመለሱ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ለሚገኘው በደል እስካሁን ይህ ነው የሚባል ጥረት አለማድረጉ ሳይበቃ የሟች ቤተሰቦችና ሌሎች ወገኖቻችን መንግስት አለን ብለው ወደ ቤተ መንግስት ሲያመሩ በኃይል ማስመለሱ ለዜጎች በደል ትኩረት እንደሌለው ዳግመኛ ያስመሰከረበት ነው፡፡ ይህን የተገነዘቡት ሰልፈኞችም ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስት የለም›› ብለው ተቃውሟቸውንና ቁጣቸውን ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ ሰልፈኞች ላይ ወከባ ከመፍጠር አልፎ ሀዘን ላይ የሚገኙ የሟች ቤተሰቦችን ጨምሮ ሰልፈኞችን ደብድቦ በኃይል በትኗል፡፡ ይህ የመንግስት እርምጃ በዜጎች ላይ ተጨማሪ ምሬትን ፈጥሯል፡፡ አሳዝኗል፡፡ በሰልፉ ወቅት በርካታ ኢትዮጵያውያን በቁጭት ተቃውሟቸውን ከመግለጽ ባሻገር ከየአካባቢው ሰልፈኛውን እየተቀላቀለ እንደነበር ለመረዳት ችለናል፡፡ በመሆኑም ፖሊስ ሰልፍ ብቻ ሳይሆን ለቅሶም ጭምር እንደበተነ ተረድተናል፡፡ ሰማያዊ ይህ ከባህላችን ያፈነገጠ፣ ለዜጎች ምንም አይነት ርህራሄ ያልታየበትን የመንግስት እርምጃ በጽኑ ይቃወማል፡፡
በሌላ በኩል መንግስት ለነገ ሚያዝያ 14/2007 ዓም የተቃውሞ ሰልፍ በመስቀል አደባባይ መጥራቱ ተገልጾአል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ዜጎቻችን አደባባይ ወጥተው የአሸበሪ ቡድኑን አረመኔያዊ ድርጊት እንዲያወግዙ ካለው ጽኑ እምነት የተነሳ ዜጎች መስቀል አደባባይ ወጥተው የተቃውሞ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ዜጎቻችን በስደት ባሉበት ሀገር የሚደርስባቸው ግድያና መከራ ሀገር ውስጥ ባለው የዴሞክራሲያና መልካም አስተዳደር እጦት መሆኑንም አስረግጦ ይገልፃል፡፡ በመጨረሻም ሰማያዊ ፓርቲ ህይወታቸውን ያጡ ወገኖቻችንን ፈጣሪ በቀኙ እንዲያስባቸው በሀዘን ለተጎዱም ቤተሰቦቻቸው መፅናናትን እንዲሰጥልን ይመኛል! ከዚህ ባሻገርም መንግስት አሁንም በሊቢያ እና በየመን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎቻንች አፋጣኝ ድጋፍ እና ጥበቃ እንዲያደርግ ብሎም ተገቢውን እርምጃና ዲፕሎማሲያዊ ስራ እንዲሰራ እናሳስባለን፡፡
ሚያዝያ 13/2007 ዓም
አዲስ አበባ

No comments: