Monday, September 23, 2013

የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን ለማስፈፀም የሚያስችል መመሪያ ተዘጋጀ

የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን ለማስፈፀም 

የሚያስችል መመሪያ ተዘጋጀ


አዲስ አበባ ፣ መስከረም 13 ፣ 2006 (ኤፍ ቢ ሲ)
በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 30 መሰረት መሰብሰብ ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ ማቅረብ ለዜጎች የተሰጠ መብት ነው።

በዚሁ አንቀፅ ንዑስ ቁጥር 1 ላይ የሰፈረው ድንጋጌ ደግሞ ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሳሪያ ሳይዝ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ እንዳለበት ያስቀምጣል።

ከቤት ውጪ የሚደረጉ ስብሰባዎችና ሰለማዊ ስልፎች በህዝብ እንቅስቃሴ ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ ለማድረግና ሰላምን ፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶችንና የህዝብን የሞራል ሁኔታ እንዳይጥሱ አግባብነት ያላቸው ስርአቶች ሊደነገጉ እንደሚችሉ በህገ መንግስቱ ላይ ተቀምጧል።

ከዚህ በተጨማሪ ጥቅል ሀሳብ ያላቸው ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግና በመሰብሰብ መብት ላይ ያተኮሩ ድንጋጌዎችም የህገ መንግስቱ አካል ናቸው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ህግ መንግስቱ ላይ የሰፈሩትንና ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግና በመሰብሰብ መብት ላይ ያተኮሩትን ጥቅል ሀሳቦች በዝርዘር ማየቱ አስፈላጊ በመሆኑ ፥ ህገ መንግስቱን በአግባቡ ለመተግበር የሚያስችል መመሪያ ማዘጋጀቱን ገልጿል።

የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው እንደሚሉት ፥ መመሪያው በህገ መንግስቱ ላይ የተመሰረተና ዜጎች ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና የመሰብሰብ መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ያስችላል።

በውስጡም ህጉን በዝርዝር ለማስፈፀም የሚያስችሉ መመሪያዎችን ያካተተ መሆኑንም ነው የሚያነሱት።

መመሪያው ሰላማዊ ሰልፍ የማይደረግባቸው አካባቢዎችንና ጊዜያትን ለይቶ የሚያስቀምጥ ሲሆን ፥ በሃይማኖት ተቋማት ፣ ሰፊ ህዝብ በሚገበያይባቸው የገበያ ቦታዎችና ህብረተሰቡ በብዛትና በስፋት በሚንቀሳቅስባቸው የስራ ቀናት እንዲሁም የስራ መግቢያና መውጫ ስዓታት ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን አይፈቀድም ።

ሰላማዊ ሰልፉን የጠራው አካል ያሉበትን ሃላፊነቶችና የፀጥታ አካላትን ሚና ግልፅ አድርጓል።

የመመሪያው ተልዕኮ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 30 ላይ የተቀመጠውን ድንጋጌ ማስፈፀም እንደመሆኑ ሁሉም ዜጋ በቅርቡ እንዲያውቅ ይደረጋል ብለዋል ።

ዜጎች ህገ መንግስቱንና መመሪያውን እስከ ጠበቁ ድረስ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብታቸው የተጠበቀ መሆኑንም ነው ምክትል ከንቲባው ያረጋገጡት ።
በዳዊት መስፍን

No comments: