Monday, September 9, 2013

ከጸረ ሽብር አዋጁ ሰለባ ላለመሆን መፍትሄው ‹‹አለመወለድ›› ብቻ ነው!!


ከጸረ ሽብር አዋጁ ሰለባ ላለመሆን መፍትሄው ‹‹አለመወለድ›› ብቻ ነው!!


ሙሉቀን ተስፋው (ባህር ዳር)

በጥንት ዘመን ከዓለም ታላላቅ አገሮች ተርታ የምትመደብ በጨለማው አህጉር በስተምስራቅ በኩል ባለችው አንዲት ስሟም 

ኢትዮጵያ የምትባል፣ ህዝቦቿም ልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪ፣በመልክም ቀይ፣ የቀይ ደማና ጥቁር አይነት፣ በቁመትም አጭር፣ 

መካከለኛ እና በጣም ረዣዥም ሰዎች የሚኖሩባት አገር ነበረች፡፡ ህዝቦቿ ልዩ ልዩ አምልኮም ያካሂዳሉ፡፡ በዓለም ያሉትን 

ታላላቅ ሀይማኖቶች ፈጥነው እንደዚች አገር ሰዎች የተቀበለ የለም፡፡ የዓለም ስልጣኔም የጀመረ በዚህችው አገር ነበር፡፡ የሰው 

ልጅም መጀመሪያ የኖረባት በዚችው አገር ነበር፡፡ አክሱምና ላሊበላ የሚባሉ ይኸው ትውልድ እንዴት እንደተሰሩ ሊያውቃቸው 

የማይችሉ ኪነ ኅንጻ ጥበብም በዚያችው አገር አለ፡፡

በዚህች አገር የሚኖሩ ሰዎች ጥበብ አዋቂዎችና በሳሎች ነበሩ፡፡ በአውሮጳና በእስያ ያሉ በህብረት መስራት እና በጋራ መብላት፣ 

የጋራ ሀብት ማካበት ‹‹ኮሚዩኒዝምና ሶሻሊዝም›› እያሉ የሚጠሩት ርዕዮተ ዓለም ከመኖሩ በፊት የዚህች አገር ጠቢባን 

ማህበራት ነበሯቸው፡፡ በማህበራቸውም ከመካከላቸው በእድሜ ባለጸጋ የሆኑትና የሀይማኖት አባቶቻቸው ስለ ሀገራቸው 

ሰላምነት፣ ስለ ህዝባቸው ደህንነት ይጸልዩም፣ አምላከቸውንም አመስግነው የሚፈልጉትንም ይለምኑ ነበር፡፡ ከእለታት አንድ 

ቀን ግን መራቂ በስህተት መረቀና መርገም በህዝቡ ላይ ወረደ፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው የአባቶቻቸው ምርቃት ‹‹ኢትዮጵያን 

ሀገራችን ማህሏን ገነት ዳሯን ግን እሳት ያድርግልን›› በማለት ነበር፡፡ መራቂው በስህተት ‹‹አገራችን መሀሏን እሳት 

አድርግልን›› ብሎ በመመረቁ ምክንያት አንድ ሀይለኛ ንጉስ በህዝቡ ጫንቃ ላይ አረፈ፡፡ 

የንጉሱም የወል ስም ‹‹ኢህአዴግ›› ተባለ፡፡ ስሙንም የሰጠው ለራሱ ነው፡፡ እነዚህ ህዝቦች ኢህአዴግ ከመንገሱ በፊት 

ጨዋታው ሁሉ በነፍጥ የሆነ ደርግ የሚባል ጫማዎቹ ባለመሎጊያ የሆኑ፣ አመክንዮና በሀሳብ የመወያየት ባህል በሀይልና 

በማስፈራራት የተተኩበት ጊዜም በመሆኑ የአገሪቱ ህዝቦች ኢህአዴግ ሲመጣባቸው በደስታ ተቀበሉት፡፡

ኢህአዴግም የኢትዮጵያን ሰዎች እንዲህ ሲል አሞኛቸው፡፡ ወደ እኔ የተጠጋ ይድናል፡፡ ሽክማችሁ የከበደ ወደ እኔ ኑ፡፡ እኔ 

ሸክሜም ቀሊል ቀንበሬም ልዝብ ነውና አላቸው፡፡ ሰዎቹም አመኑት፡፡ የሽማግሌውን የእርግማን ምርቃት በዚህች ሰዓት 

ያስተዋለ የለምና፡፡

የዚህ ንጉስ ሀይለኛነት ቀስ በቀስ እየተገለጠም ሄደ፡፡ በሳል የተባሉ በአገሪቱ የነበሩ በዘመናቸው የመጠቀ አስተሳሰብ የነበራቸውን 

ሰዎች ከአካባቢው እንዲርቁ አደረጋቸው፡፡ ደፍረው የተጠጉተን ግን ‹‹ከእናንተ ጋ ምን ህብረት አለኝ›› ብሎ ለብቻቸው 

በተከለለ ቦታ አስቀመጣቸው፡፡ በመካከልም ከአለሙ ሁሉ የሚለይ ጋራ አበጀባቸው፡፡ እነዚያ ሰዎችም በተከከለ ቦታ ከጋራው 

ማዶ ‹‹ህብረትንማ እንደማታውቅ በግብርህ እያየን አይደለምን! ባይሆን መለየያየቱን በወጉ አድርገው እንጅ›› ሲሉ ከአጥር 

ውስጥ ሆነው ተናገሩት፡፡ አጥብቀው የተናገሩትን አይቀጡ ቅጣት ቀጣቸው፡፡ ሌሎቹም ቢሆን ባሉበት ቦታ እርጅና ተጫናቸው፡፡ 
ንጉሱ ግን አንድነታቸውን በጎሳ ጠበብቶችና መሰል ልሂቃን ድንበር አበጀላቸው፡፡ ‹‹ከኦሮሞው ግዛት አማራው ምን አለው! 

ከሲዳማው ግዛት ኦሮሞው ምን አለው! ከዚህ ወዲያ የእናንተ ከዚያም በኋላ የእነርሱ ነው ብየ አልነገርኳችሁምን! ስለምን 

ከማይመሰላችሁ ጋር ህብረት መፍጠር አሰባችሁ! የሚያምን ከማያምን፣ ወገንህ ከዚያ ማዶ ካለው ሰው ጋር ምን ህብረት 

አለው!›› የሚል መልዕክትም በአገሪቱ ባሉ አውራጃዎችና ቦታዎች ሁሉ ተዳረሰ፡፡ ከባድ ጥፋትም ተከሰተ፡፡ የህዝቡ ማህበራዊ 

አንድነትም ታወከ፡፡ በዚሁ መልዕከት የተነሳ ጋብቻቸውን ሁሉ ያፈረሱም ቀላል አልነበሩም፡፡ 

ንጉሱም በተለያዩ ጊዘያት የተለያዩ አዋጆችን እያወጣ በአገሪቱ ሁሉ ላይ ተገበረ፡፡ አንዳንዶቹ ግን በተለዬ ሁኔታ የህዝቡን 

እንቅስቃሴ የሚገድቡ ሆኑ፡፡ አንዳንዴም ቀደም ብለው የወጡትን ህጎች የሚጣረሱም ሆኑ፡፡

ኢህአዴግ በነገሰ በ19ኛ ዓመት፣ በአመቱም በ12ኛው ወር፣ ከወሩም በ22ኛው ቀን የንጉሱን ረቂቅነት ሊያስረዳ የሚችል አዋጅ 

አወጀ፡፡ ስሙንም ጸረ ሽብር ብሎ ጠራው፡፡ እንደ 666 የአውሬው ቁጥር ሁሉ ኢህአዴግም ለአዋጁ ቁጥር አበጀለት፡፡ 

652/2001 የሚለው የአውሬው አዋጅ መለያ ቁጥርም ሆነ፡፡ በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ የተባለችው ሀገር በዋና ከተማዋ አዲስ 

አበባ እና በሁሉም ስፍራዎቿ የሚኖሩ ህዝቦች ሁሉ ‹‹ንጉስ ሆይ ምን አጠፋን! እንዲህ አይነት መቅሰፍት በላያችን ላይ 

ተጫነ›› እያሉ ኡኡታቸውን አቀለጡት፡፡ ንጉሰም መለሰላቸው ‹‹ሰማይ እንደማይታረስ ንግስናዬም እንደማይከሰስ ስለምን 

አላስተዋላችሁም›› አላቸው፡፡ 

ንጉሱም ለህዝቡ ሁላ እንዲህ ሲል በንፋስ ምስል መስኮቱ አስተላለፈ፡፡ ‹‹አዋጅ አዋጅ ስማ ያልሰማን አሰማ፣ ይህን አዋጅ 

ለተላለፉ ሁሉ ወዮላቸው፤ መጽናናትን አያገኙምና፤ በስልክ መንግስትን ያማ ወዮለት፤ ልማታዊ መንግስቴ አያስጠጋውምና፤ 

በማህበራዊ ድረ ገጾች ሸክሙ ከበደኝ ያለ ወዮለት- ከእይታዬ አይሰወርምና፤ ወዮ ለዚያ ሰው እኔን አያድርገኝ፡፡ ጽድቄን 

ለሚተላለፍ ለዚያ ሰው ከአንገቱ ላይ በገመድ ወፍጮ ድንጋይ ታስሮ ወደ ጥልቅ ጉድጓድ ቢወድቅ ይሻለው ነበር፡፡››

በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ የተባለችው ሀገር ሰዎች ባልተወለዱ ህጻናት ይቀናሉ፡፡ በህይወት ያሉትም፣ የሞቱትም በስጋ ፈቃድ 

ምክንያት ሰይጣን ቢያሳስታቸው በልጅ ልጆቻቸው ላይ ሊተላለፍ የሚችል ቅጣት ይጠብቃቸዋልና፡፡

ንጉሱም ከቀን ወደ ቀን በሀጢያታቸው ምክንያት ስለተፈረደባቸው ሰዎች በንፋስ ምስሉ ሁሌ ሳይሰለች ይናገር ነበር፡፡ በዚያች 

ምስኪን ሀገርም ልክ እንደፈጣሪ ያክል ሆነባቸው፡፡ የሰዎቹን እንቅስቃሴ የሚከታተል ሰውም ለእያንዳንዱ ሰው መደበላቸው፡፡ 

እንዲህም አላቸው ‹‹በእያንዳንዱ ሰው መካከል እኔ አለሁኝ፤ እናንተ ግብዞች ምሉዕ በኩልሄ (omnipotent) መሆኔን 

እንዴት መገንዘብ አቃታችሁ!! ለእያንዳንዱ ሰው ጠባቂ መላክ እንደላክሁላችሁ ዘነጋችሁኝን!!››፡፡ 

በዚያም ጊዜ አንዳንዶች ከዚህ በፊት በዚሁ ንጉሱ የታወጁትን ህጎች በማስታዎስ ‹‹ይህች ቃልህ ስለምን ከፊተኛይቱ ጋር አንድ 

አልሆነችም! በቀደመው ህግህ አንድ ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ አንድን ሰው መያዝ ቀርቶ ቤቱ እንኳ እንዲበረበር 

አልፈቅድም ብለህ ነበር፡፡ አሁን ግን ክቡር ዘበኛህ በአንድ በተወሰነ ቦታ ላይ ሽብርተኛነት እየተፈጸመ መሆኑን ካመነ፣ ሊፈጸም 

እንደሚችል በቂ ምክንያት ካለው እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል፣ በድንገት ለሚደረግ ብርበራም ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወረቀት 

አስፈላጊ ከሆነም በስልክም በሚገኝ ፈቃድ ሊሆን እንደሚችል ትነግረናለህ!! በቀደመው ህግህ ስለግለሰብ መብት ነገርከን አሁን 

ደግሞ ያይኑ ቀለም ያላማረኝን ሰው ስልኩን ሊጠልፍ፣ የሚናገረውን በሚስጥር ሊቀዳ የሚችል፣ የመልዕክት ሳጥኑን ሊበረብር 

የሚችል መልዓክ እልክበታለው ትላለህ!! በቀደመው በወንጀል የተጠረጠረ ሰው ፍርድ ቤት ቀርቦም ያለመናገር መብት 

እንዳለው ታወጀ፡፡ አሁን ግን አይደለም ቃሉን ደሙንና ምራቁን እንኳን ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነን ተጠርጣሪ ጉልቤዎች 

‹‹ተመጣጣኝ ሀይል›› መውሰድ እንደሚችሉ ትነገረናለህ፡፡ በቀደመው አዋጅህ አንድ ሰው በፍርድ ቤት ጥፋተኛነቱ 

ካልተረጋገጠ ወንጀለኛ እንደማይባል አስተማርከን አሁን ግን አስቀድመህ በግል ንብረትህ በሆነው የንፋስ ምስል መስኮትህ 

‹‹አሸባሪ›› ናቸው ትለናለህ!! የኦሪት ጊዜ አልቆ አዲስ ዘመን ታወጀ እንዳንል ወይም ዘመን መቁጠሩን ዙሮ ወደ ኋላ ከሀዲስ 

ወደ ብሉይ ተጓዘምን እንዳንል ነበያቶቹ አልተቀየሩም፤ የንጉሳችን መገለጥ ሂደት እንዴት ነው! አንድ ሰው ከዚህ በድንገት 

ሊሰጥ ከሚችል ታርጋ ይድን ዘንድ ንጉስ ሆይ በእውኑ መፍትሄው ምንድነው! የትኛይቱን ህግስ እንከተል! ጠባቂ 

መላዕክቶቻችንስ ቢሆን የሚጠብቋቸውን ዜጎች ስለምን ያሳቅቃሉ! የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ባልከፋም ነበር ግን 

በተቃራነው መሆኑ ይህ ምስጥሩ ምንድን ነው! ይህ በእውነት በንጉሱ ካልሆነ በእኛ የአዕምሮ ምጥቀት ሊተረጎም 

አልተቻለንም›› ሲሉም ተገዳደሩት፡፡

አንዳንድ ባለ ብሩህ አዕምሮ ነን የሚሉ ሰዎችም ከእነርሱ እድሜ በፊት ከወደ ምዕራብ ጆርጅ ኦሮይል የሚባል ሰው የእንስሳት 

አቢዮት ብሎ በሰየመው መጽሀፍ ውስጥ ያለው ትንቢት እንደዚህ ነበር ሲሉም አዲሱን የንጉሱን አዋጅ አጣጣሉት፡፡ ከእለታት 

በአንድ ቀን እንስሳቱ ሁሉ በጌታቸው ላይ አምጸው የእንስሳት መንግስት መሰረቱ፡፡ ሰባት አንቀጽ ያለው ህግም አወጡ፡፡ 

ከህጉም የመጀመሪያው አንቀጽ ‹‹ሁለት እግር ያለው ሁሉ ጠላት ነው›› የሚለው ነው፡፡ ሌሎችም ‹‹በአራት እግሩ የሚሄድ 

አሊያም ክንፍ ያለው ሁሉ ወዳጅ፣ እንስሳት የሰው ልጆችን ልብስ መልበስ፣ በሰው ልጆች በተሰራ አልጋ ላይ መተኛትና የሰው 

ልጅ ያዘጋጀውን አልኮል መጠጣት ፍጹም ክልክል መሆኑን፣ እንስሳ እንስሳን መግደል እንደማችልና ሁሉም እንስሳት እኩል 

ናቸው፡፡›› የሚሉ አዋጆች ይገኙበት ነበር፡፡ 

እንስሳቱም ለተወሰነ ጊዜ በድሎት እና በምቾት ኖረው ያመረቱትን ምርት ለራሳቸው ሲያውሉ እና የሰው ልጅ የተባለው 

ጠላትም በአካባቢያቸው ሲያርቁት ደስታቸው ወደር አልነበራቸውም፡፡

ሆኖም እየዋለ እያደረ አስተባባሪው እንስሳ (አንዱ አሳማ) በግሉ ባሳደጋቸው ውሾች የተነሳ የእርሻ ቦታውን ለመቆጣጠር ቻለ፡፡ 

ውሾቹም የደህንነት አስጠባቂዎች ሆኑ፡፡ ለምን ብሎም መጠየቅ አልተቻለም፡፡ ህጎቹም በየቀኑ ይስተካከሉ ዠመር፡፡ ለምሳሌ 

ከህገ አራዊታቸው አንደኛው አንቀጽ ‹‹በሰው ልጆች አልጋ ላይ መተኛት ወንጀል ነው›› የሚል ነበር፡፡ ይህ ህግ በንጉሰ አራዊቱ 

አማካሪዎች ‹‹በሰው ልጆች አልጋ ላይ መተኛት ክልክል ነው - አንሶላ ለብሶ!›› ተብሎ ተስተካከለና ነጉሰ አራዊቱም ምቹው 

አልጋ ላይ ተኛ፡፡ አንዳንድ አራዊቶች በሰው ልጆች አልጋ ላይ መተኛት ‹‹ነውር›› እንደሆነ ያላቸውን መጠነኛ አዕምሮ 

ተጠቅመው አስታውሰው ህጉ ወደ ተጻፈበት አቅጣጫ ሲሄዱ ‹‹አንሶላ ለብሶ›› የሚል ሀረግ እያዩ ‹‹ በቃ ጌቶች አልጋ ላይ 

ብርድ ልብስ እንጅ አንሶላ ስላልበሱ ትክክል ናቸው›› አሉ፡፡ እርግጥ ነው የተጠራጠሩም ነበሩበት፡፡

ንጉሰ አራዊቱ በክብክብ ውሾቹ አማካይነት አንድ ቀን በርካታ እንስሳትን በተለይም ለእንስሳት እርሻው በጣም አስተዋጽኦ 

የነበራቸውን አስረሸናቸው፡፡ ያች ማሳ ደም በደም ሆነች፡፡ ያመለጡትን አንድ አሳማና አንዲት በቅሎም ሊሰልሉ የሚችሉ 

እርግቦች አሰማራ፡፡ ይህም ለእርሻቸው እና ለእነርሱ ደህንነት እንደሆነ በአፈ ጉባኤው በኩል ተነገራቸው፡፡ እንስሳቱም ከዚህ 

በፊት ‹‹እንስሳ እንስሳን መግደል የለበትም›› የሚለውን ህግ አስታውሰው ኪታቡ የነበረበትን ቦታ ፈለገው አነበቡት፡፡ መጨረሻ 

ላይ ‹‹ያለ በቂ ምክንያት›› ምትል ሀረግ ተጨምራ ‹‹እንስሳ እንስሳን መግደል የለበትም - ያለ በቂ ምክንያት›› በማለት 

አነበቡና ንጉሱ ወንጀል አልሰራም ሲሉ አሰቡ፤ ሰርቷል ብለው ያሰቡም በውስጣቸው ያዙት፡፡

በአራዊቱ መንደር የጌታ እና የሎሌ አይነት ስርዓት ነግሶ ሲመለከቱ ‹‹ሁሉም እንስሳት እኩል ናቸው›› የሚለውን ወርቃማ 

አንቀጽ አስታወሱት፡፡ እንደልማዳቸው ሂደው ሲያነቡት ‹‹ሁሉም እንስሳት እኩል ናቸው - አንዳንዶች ደግሞ የበለጠ እኩል 

ናቸው›› የሚል ሆኖ ያገኙታል፡፡ በአጠቃላይ በእንስሳቱ ያሉት ሁሉም አናቅጾች የንጉሰ አራዊቱን እድሜ በሚያራዝም መልኩ 

ተስተካከሉ፡፡ የተፈጥሮ የሆኑትን እንኳ በንጉሱ ቸርነት እንደሆነ እንዲናሩ ይደረግ ነበር፡፡ ‹‹እኔ በጌቶች አመራር በስድስት ቀን 

አምስት እንቁላል ለመጣል ቻልኩ›› ስትል ዶሮ አንዱ ደግሞ ‹‹እኔ በጌቶች ቸርነት 11 አመት ለመኖር ቻልኩ›› ይላል 

ሌላው፡፡ 


እናም እነዚህ ባለ ብሩህ አዕምሮ የቀደመችውን የንጉሱን አዋጅ ያስታወሱ ሰዎች የዚህን ሀይለኛ ንጉስ አዋጆች ከዚህ ምሳሌ ጋር 

እያያዙ ያወጉ ዠመር፡፡ በመጀመሪያው አዋጅ ‹‹በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ መያዝ አይችሉም›› 

በአሁኑ ደግሞ ‹‹በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ መያዝ አይችሉም - አስቸኳይ ካልሆነ በስተቀር›› በሚል 

ተስተካክሎ አገኙት፡፡ የቀደመው ‹‹በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች በፍርድ ቤት ጥፋተኛነታቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ ወንጀለኛ 

አይባሉም›› በሚለው ሀሳብ ላይ ‹‹አሸባሪ ካልሆኑ በስተቀር›› የሚል ሀረግ ተጨምሮ ‹‹‹‹በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች 

በፍርድ ቤት ጥፋተኛነታቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ ወንጀለኛ አይባሉም - አሸባሪ ካልሆኑ በስተቀር›› በሚል ተስተካክሎ 

እንዲነበብ ተደረገ፡፡ 

ይህን አስታወስን በሚሉ ሰዎች የሚነገርን መገዳደር እና አሉቧልታ በሰማ ጊዜ ኢህአዴግ የተባለው ንጉስም አስረግጦ እንዲህ 

አለ ‹‹በቀደመው ግለሰቦች መረጃቸውን የመጠበቅ፣ ያለማስፈተሸ መብት እንዳለቸው ሰምታችኋል እኔ ግን እላኋለው ግለሰቦች 

መረጃቸውን ማስፈተሸ አይችሉም- ግን ፈታሽ መልዓክና መልክዕከተ ሳጥን ሰባሪ ክብክብ እልካለው፡፡ በቀደመው 

ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበውም ያለ መናገር መብት አላቸው- አሁን ግን እላኋለው አስፈላጊ ከሆነ ክብክቦቹ ተመጣጣኝ 

ሀይል ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ እኔ የቀደመችውን የራሴን ህግ አጸናው እንጅ አልሻርኩም፡፡ ክብክቦቼም የሰዎቼን ደህንነት 

ይጠብቃሉ››፡፡ 

ሰላም!!


(ማስታዎሻ፡-ይህን ጽሁፍ እንድጽፍ የተነሳሳሁት ከአሸባሪነት ጋር በተያያዘ በደቡብ ጎንደር ደብረ ታቦር፣ ፋርጣ፣ ስማዳ እና 

ጋይንት በልዩ ልዩ ሙያ ተሰማርተው የነበረ 13 ግለሰቦች በግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. ተይዘው በአዲስ ዘመን፣ ወረታ እና 

ባህር ዳር ባሉ ፖሊስ ጣቢያዎች በተለያዩ ዳኛዎች እና መርማሪዎች ጉዳያቸው ሲታይ ቆይቶ አንድም መፍትሄ ሳያገኙ 

ቤተሰቦቻቸው ጭምር እየተንገላቱ በመጨረሻም አዲስ አበባ ማዕከላዊ ለወራት እንዲቆዩ ተደረገ፡፡ ግለሰቦቹ በምን ሁኔታ ላይ 

እንዳሉ እና የፍርድ ሂደታቸውን የሚከታተል ሰው አልነበራቸውም፤ የላቸውም፡፡ በኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ መታሰራቸውን 

ከማንበባችን የዘለለ የትኛውም ሚዲያ እነዚህን ወጣቶች አያውቅም፡፡ እናም ስንት ያልታወቁ ሰዎች በዚህ አይነት ችግር በዚህ 

ህግ ምክንያት ሊጎዱ እንደሚችሉ ሳስብ ይህን ጽሁፍ ጻፍኩ፡፡)

No comments: