Thursday, September 12, 2013

የፓርቲ አባልነት ከዜግነትና ብቃት አይብለጥ

የፓርቲ አባልነት ከዜግነትና ብቃት አይብለጥ

12 September 2013 at 21:59
በኢትዮጵያ በመንግስትነት ወንበር የተቀመጡ የነገስታቱን፣የወታደራዊው አስተዳደርንና የኢህአዴግን ተመሳስሎ ከሚያሰፉ ሁነቶች አንዱ ሁሉም ለተጠጋቸው ታማኝነቱን ላሳያቸውና የሚሰጡትን የመታወቂያ ደብተር እንደ ጸሎት መጽሀፍ ከኪሱ ለማይነጥል  ከተራው ዜጋ በተለየ የሚያደርጉለት ውለታ ነው፡፡
አጼው ከእንግሊዝ አገር ስደት መልስ መንበራቸውን በብዙ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ደም ካገኙ በኋላ ሹመት የሰጡት ለቅርብ ሰዎቻቸው እንደነበር ታሪክ መዝግቦታል፡፡ንጉሱ አርበኞችን አስከፍተው ታማኞቻቸውን በሹመት በማንበሽበሻቸው
             አገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ
             የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ፡፡
የሚል ስንኝ መደርደሩ የነበረውን እውነታ ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡የንጉሱን የቤተሰብ ስርዓት በመገርሰስ በህዝባዊ መፈክር ወደ ስልጣን የወጣው ደርግ የአጼውን የቅርብ ሰዎች በማጥፋት የራሱን ሰዎች በማሰባሰብ ካድሬነት ከኢትዮጵያዊነት በላይ እንዲታይ አድርጓል፡፡አለም የወዛደሮች ትሆናለች ይል የነበረው ደርግ ከወዛደር ውጪ የማየት ፍላጎት ስላልነበረው ወዛደር ያልሆነ ኢትዮጵያዊ ‹‹ኢምፔሪያሊስት››በመባል ይፈረጅ ነበር፡፡
በደርግ አብዮታዊነት ያልተጠመቀ ኢትዮጵያዊ ስራ የማግኘት ሌላው ቀርቶ ከቀበሌ ይታደል የነበረን  የማግኘት መብት አልነበረውም፡፡የደሃው ልጆች ለጦርነት ሲማገዱ የደርግ ሰዎች በኪሳቸው የያዟት ቀይ መታወቂያ ልጆቻቸውን  ከእሳት የመጠበቅ ጉልበት ነበራት፡፡
ደርግ ከሄደ 22 ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ዛሬስ?የህዝብ ብሶት ለስልጣን እንዳበቃው የሚናገረው ኢህአዴግ በተለይም አውራ ፓርቲነቱን ካወጀበት ቅጽበት አንስቶ በአገሪቱ የእርሱን ይሁንታ ሳያገኙ ስራ ማግኘት ነግዶ ማትረፍ ተደራጅቶ መብትን መጠየቅ የማይታሰብ እየሆነ ነው፡፡ተማሪዎች ተመርቀው በተመረቁበት ሞያ ስራ እንዲያገኙ አባል የሚያደርጋቸውን ፎርም እንዲሞሉ ይደረጋሉ፡፡ለስራ ከተመረቁበት ሞያ በላይ አባልነት ዋጋ እንደተሰጠው ማየት የቀደመው ስርዓት ግልባጭ መሆን ነው፡፡
በነጻ ገበያ እንደሚያምን ይናገር የነበረው ገዢው ፓርቲ ነጋዴዎችን በነጋዴዎች ፎረም እንዲደራጁ ማድረጉም በዚህች አገር ‹‹ያልተደራጀ››ከስርዓቱ ምንም እንደማያገኝ አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት እንዲደራጁ የተደረጉ ወጣቶች ወደ መደራጀት የገፋቸው ስራ ማጣት ቢሆንም ኢህአዴግ ለስራ የተደራጁ ወጣቶችን በፓርቲ ስብሰባ፣በሰላማዊ ሰልፍ፣በመዋጮ ጠፍንጎ መያዙ ስራን ለአላማው ማራመጂያነት እየተጠቀመበት እንደሆነ መናገር ይቻላል፡፡
በአንጻሩ የዜጎች በነጻ የመደራጀት መብት አጣብቂኝ ውስጥ ለመግባቱ ባለ ራዕይ ወጣቶች ማህበርን መመልከት ይቻላል፡፡ማህበሩ ለስበሰባ የሚሆኑ አዳራሾችን ከመነፈጉ በላይ አባላቶቹ ላይ ማሳደድ እየተፈጸመ ለመሆኑ ዘወትር ከመግለጽ ተቆጥቦ አያውቅም፡፡ነጻ ማህበራት በህግ መሆናቸው በህግ ታውጆ በገቢር ግን የገዢው ፓርቲ ክንፍ የሆኑ ማህበራት እንደ ባለ ራዕይ ማህበር የአዳራሽ ችግር አያጋጥማቸውም፣አባላቶቻቸው አይሳደዱም፡፡እነዚህ ሁለት ታቃርኖዎች በፓርቲ አባልነትና በነጻ ዜግነት መካከል የሰማይና የምድር ያህል ርቀት እንዳለ የሚያሳዮ ናቸው፡፡
አገሪቱ የካድሬውም፣የተቃዋሚውም፣የደጋፊውም፣የነቃፊውም፣በነጻ የተደራጀውም፣ሊግ የሆነውም የምትሆነው በተደራጁና ባልተደራጁ ዜጎች መካከል ምንም አይነት ልዮነት ሳይደረግ ነው፡፡አንዱ በችሎታው ሳይሆን ለድርጅቱ ያለው ታማኝነት ተሰፍሮለት ከሌላው የሚበልጥ ከሆነ የዜግነት መብት ይደፈጠጣል፡፡በዚህ ሁኔታ ውስጥ የምትፈጠር አገር የጥቂቶች እንጂ የሁሉም አትሆንም፡፡ኢህአዴግ አሁንም ቆም ብሎ ምን አይነት አገር እየፈጠረ እንደሆነ ማሰብ አለበት፡፡በየትኛውም መለኪያ የፓርቲ አባልነት ከዜግነትና ችሎታ መብለጥ አይገባውምና፡፡
     በቅርቡ ማን እንደሆናችሁ ደርሰንባችኋል ተብለው ከአየር መንገድ ለተባረሩ 75 ኢትዮጵያዊያን መታሰቢያ ይሁንልኝ፡፡

No comments: