Sunday, September 22, 2013

የኔ ሐሳብ ... የኔ ጉዳይ!


የኔ ሐሳብ ... የኔ ጉዳይ!
---------------------------

ለውጥ የማይቀር ሂደት ነው። ስለ ሀገር ለውጥ ስናስብ ስለ ማህበረ-ፖለቲካዊ ለውጥ መሆኑ አይቀርም። ስለ ማህበረ ፖለቲካ 
ስናወራ ስለ ሕብረተሰብ እየተናገርን ነን። ስለ ሕብረተሰብ ስንናገር ስለ አብዛኛው ዜጋ መሆኑ ነው፤ ምክንያቱም እያንዳንዱን 
ዜጋ አንድ ዓይነት አመለካከትና ዝግጁነት ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ ስለ አብዛኛው ሰው ፍላጎትና ዝግጁነት ስናወራ 
ዴሞክራሲያዊ ነው።


እኔ እንደ ሐሳብ የማነሳው ጉዳይ ሀገራዊ የሆነ የፖለቲካ ለውጥ ያስፈልጋል የሚል ነው። ግን ሰው ሁሉ የየራሱ ፍላጎትና 
አስተያየት አለው። ይህንን የሰዎች ፍላጎት ማክበር አለብኝ። እኔ ለውጥ ስለፈለኩ ብቻ ሌሎች ሰዎችም ለለውጥ እንዲነሱ 
አላስገድድም። ለነገሩ ማስገደድም አልችልም፤ ምክንያቱም ጠብመንጃና በጠመንጃ ሰዎች የማስገደድ ፍላጎት የለኝም።


ግን እኔ ለውጥ ፈላጊ ነው። ምን ዓይነት ለውጥ? ስልጣን በጠብመንጃ ከመያዝ ስልጣን ከህዝብ (በሰለማዊና ዴሞክራሲያዊ 
ምርጫ) ወደ መቀበል መሸጋገር አለብን። ስልጣን መያዝ በራሱ ግብ ስላልሆነ ስልጣን የምንይዝበት መንገድ የሐሳብ ክርክር 
መሰረት ያድረገ እንጂ በጠመንጃ ሃይል መሆን የለበትም።


እኔ የፖለቲካ ለውጥ እፈልጋለሁ። ሌሎችም የኔ ፍላጎት የሚጋሩ ዜጎች ይኖራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ለውጥ እንዲመጣ 
የማይፈልጉ ይኖራሉ። ለውጥ የሚፈልጉ ሃይሎች "ይህን የፖለቲካ ስርዓት አልተመቸንም፤ ሌላ ስርዓት ማየት እንፈልጋለን" 
እያሉ ነው። ለውጥ የማይፈልጉ ደግሞ "አሁን ስልጣን ላይ ባለው ስርዓት ተመችቶናል፣ ለኛ በቂ የሆነ ለውጥ አለ፣ ተጨማሪ 
የፖለቲካ ለውጥ አንፈልግም" የሚሉ ናቸው። ስለዚህ ክርክሩ ያለው ለውጥ በሚፈልጉና በማይፈልጉ፣ በተመቻቸውና 
ባልተመቻቸው መካከል ነው። የተመቸው ለውጥ ያለመፈለግ፣ ያልተመቸው ደግሞ ለውጥ የመፈለግ ጉዳይ ባህርያዊ ነው።


ጉዳዩ መሆን ያለበት የሁለቱም ወገኖች (በዚህ ስርዓት የተመቸውና ያልተመቸው) ፍላጎት ማስታረቅ መሞከር ነው። 
ለማስታረቅ 
የምንጠቀመው መስፈርት ምንድነው? መስፈርቱ ለመለየት ግባችን መለየት አስፈላጊ ነው። ግባችን ልማት ነው። 
የልማት ዓላማ ደግሞ የሰው ልጆች ነፃነት ነው። ስለዚህ ዓላማችን ልማት/ነፃነት ከሆነ መንገዱ ምን መሆን አለበት? ሁለገብ 
ልማትና ነፃነት ለማስፈን የሁሉም ሰው (የአብዛኛው ሰው) ፍላጎት መሰረት ያደረገ ተሳትፎ ያስፈልጋል። ይህ አሰራር ደግሞ 
ዴሞክራሲ ይባላል።


ስለዚህ የሁለቱም ወገኖች ፍላጎት ለማስታረቅ ዴሞክራሲያዊ መንገድ መከተል አለብን (መስፈርቱ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ 
ነው)። 
በአንድ ሀገር ለውጥ የሚፈልጉና የማይፈልጉ ዜጎች ቢኖሩም በአንድ ሀገርና በአንድ አስተዳደር ለመቀጠል እስከወሰንን 
ድረስ አንድ ላይ መጓዝ ይኖርብናል። ስለዚህ 'የየትኛው ፍላጎት ገዢ ሁኖ መቀጠል አለበት' በሚል ሐሳብ ላይ ውሳኔ 
ያስፈልገናል ማለት ነው።


ዉሳኔያችን ዴሞክራሲያዊ ይሁን። በዚህ መሰረት የአብዛኃዎቹ ፍላጎት ገዢ ይሆናል፣ የጥቂቶቹ ደግሞ ይከበራል። (አብዛሃና 
ጥቂት የሚወሰነው ለለውጥ ባላቸው ፍላጎት እንጂ በብሄር ወይ በቋንቋ ወይ በሃይማኖት አይደለም)። እናም አብዛሃ 
ኢትዮዽያውያን ለውጥ ያልተመቻቸውና የፖለቲካ ለውጥ የሚፈልጉ ከሆነ እንደፍላጎታቸው ለውጥ መምጣት አለበት፤ የህዝብ 
ፍላጎት ነውና። አብዛኛው ኢትዮዽያዊ በዚህ ስርዓት የተመቸውና ለውጥ የማይፈልግ ከሆነ ይህ ስርዓት ይቀጥል፤ የህዝቦች 
ፍላጎት እናክብር።


አብዛኛው ህዝብ እንደተመቸው ወይ እንዳልተመቸው እንዴት እንወቅ? ቢያንስ ለውጥ የሚፈልጉና የማይፈልጉ የተወሰኑ 
ግለሰቦች አሉ። እነዚህ ግለሰቦች ለምን ለውጥ እንደሚያስፈልግ ወይ እንደማያስፈልግ ምክንያታቸውን ለህዝብ ያቅርቡ፤ 
ለማሳመን ይሞክሩ። የግለሰቦቹ ሐሳብ ህዝቡ ጋ እንዲደርስ ነፃ ሚድያ ይፈቀድ። በዚህ ሂደት መንግስት ገለልተኛ ይሁን (ገዢው 
ፓርቲ አላልኩም)። ህዝቡ የራሱ ፍላጎት መሰረት አድርጎ ዉሳኔ ይስጥ።


ህዝቡ ዉሳኔውን የሚያሳውቀው በምርጫ ይሁን። ህዝቡ የፈለገውን አቋም እንዲያንፀባርቅ ነፃነቱ ይሰጠው። ፍላጎቱ በምርጫ 
በማንፀባረቁ ምንም ዓይነት አድልዎ ሊደርሰው አይገባም። በመጨረሻ የህዝቡ ውሳኔ ወይ ምርጫ ይከበር። አብዛኛው ህዝብ 
ለውጥ ከፈለገ ለውጥ ይኑር፤ ለውጥ ካልፈለገ ደግሞ ባለንበት እንቀጥል።


ጨዋታው መሆን ያለበት ይሄ ነው፤ለውጥ የሚፈልግ ሰው ይበዛል ወይስ የማይፈልግ??? የኔ ሐሳብ የኔ ጉዳይም ይሄ ነው።


It is so!!!

No comments: