Monday, March 2, 2015

የፀረ-ኢትዮጵያዊው ገዥ ሥጦታዎች አያባሩም!

(ልንጠቀምባቸው ይገባል፤ ካወቅንበት)
አንዱዓለም ተፈራ
የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በተደጋጋሚ ለታጋዩ ክፍል የሚያደርገው ልገሣ፤ ማብቂያ ዲካ የለውም። አሁን ደግሞ እልል የሚያስብል ስጦታ ፊታችን ላይ ዘርግፎልናል። በሰላም የሚታገሉትን ድርጅቶች፤ ለማፈራረስና ለመጪው ውድድር እንዳይሳተፉ ለማድረግ፤ ባለ በሌለ ጉልበቱ ዘምቶባቸዋል። ይህ የሚጠበቅ ነው። በርግጥ ሁሉንም ታጋይ ድርጅቶች በአንድ ጠፍር አንቆ ለማጥፍት መጣሩን የሚሳየው ድርጊቱ፤ ሳያውቀው የታጋይ ድርጅቶቹን በአንድነት እንዲሰልፉ በሩን በርግዶ ከፍቶላቸዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ታጋይ ድርጅቶች፤ ከገዥው ድርጅት አንጻር አንድ በመሆን፤ አማራጭ ሆነው እንዲቀርቡ ከመጎትጎት ቦዝኖ አያውቅም። አሁን፤ ከመቼውም በላይ ይህ ጉትጎታ በሀገር ውስጥ በሰላም እየታገሉ ያሉትን ሀገራዊ ድርጅቶች፤ እንዲተባበሩ እየገፋቸው ነው። ለዚህም የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ከፍተኛ ድጋፍ ታክሎበታል። ይህ እልል ያሰኛል። ልንጠቀምበት ይገባል፤ ካወቅንበት! ድርጅቶችም እየሰሙና እየተቀበሉት ነው። ለረጅም ጊዜ ስጠብቀው የነበረው ደስ የሚያሰኘው ዜና እልል አሰኝቶኛል።
የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ከመድረክ ጋር በትብብር፤ ከሰማያዊና ከመኢአድ ጋር ደግሞ ውህደት ፈጥሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ስሰማ፤ አሁን የድሉ መንገድ በደንብ ተጠረገ አልኩ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ድርጅቶቻችሁን መታገያ አድርጉ እንጂ አታምልኳቸው ሲል የነበረውን አዳመጡ። “ትግሉ ትግል የሆነው፤ በዚህ ወይንም በዚያ ስም በሚጠራ ድርጅት በመካሄዱ አይደለም። ትግሉ የሚቀጥለው ድርጅታችንን ስለከለከላችሁን ወይንም ስለፈቀዳችሁልን አይደለም። የምንታገለው በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ሀቅ፤ ትግሉን ግድ ስላደረገው ነው።” በማለት ተነሱ። ከመሰሎቻችን ሀገር አቀፍ ድርጅቶች ጋር አንድ ሆነን እንታገላለን አሉ። ስሙን ውሰዱት አሉ። ከዚህ በላይ ለትግል ሕይወትን መሥጠት የት አለ? ቆራጥነት የት አለ። ለዚህ እኮ ነው አንዱዓለም አራጌ፣ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዩት ዓለሙ፣ በቀለ ገርባ እና ሌሎች እስር ቤት የሚማቅቁት። እናም አሁን ትግሉ የሀገር ሆነ። ትግሉ ለሀገር ሆነ። አንድነት፣ መኢአድና ሰላማዊ ተቀላቅለው ሲሰለፉ፤ ማንም ሳይቀድመኝ የመጀመሪያው አባል ለመሆን ለሩጫዬ ተዘጋጅቻለሁ። ያንዳቸውም አባል አልነበርኩም። አሁን የሁሉም ልሆን ነው። ይህን ጥሩ ሥጦታ ከንቱ ላባክነው አልፈልግም።
ድሮውንም ሥልጣን በምንም ዓይነት መንገድ እንደማይለቅ ያሳወቀው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ በሰላም እየታገልን፤ አቤቱታችንን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እናሰማለን ያሉትን ሰላምተኞች፤ መፈናፈኛ አሳጥቶ አፍኗቸዋል። አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ፤ በራሱ የዕለት ተዕለት ሕግ ማውጣትና ማፈረስ ባህርይ፤ ሕጋዊ አይደላችሁም ብሎ አንዳንዶቹን እንዳይወዳደሩ፤ ሌሎችን ደግሞ ሰርጎ በመግባት የሱ ተቀጥላዎች እንዲሆኑ እየኮለኮላቸው ነው። ይህ ሁሉ ድካሙ የሚያሳየው፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ ምን ያህል የኢትዮጵያን ሕዝብና ምርጫውን እንደሚፈራ ነው። ባለፈው ጊዜ ምርጫውን 99.6% አቸነፍኩ ያለ ፓርቲ፣ የሀገሪቱን ገንዘብ፣ መንግሥታዊ መዋቅርና የሰው ኃይል በሙሉ ለራሱ ምርጫ ያዋለ ፓርቲ፣ የምርጫ ቦርዱን በቁጥጥሩ ሥር ያደረገ ፓርቲ፣ ለምን ተወዳዳሪዎቹን እና ምርጫውን ይፈራዋል። ግልጽ ነው። በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እምነት የለውም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ታጋዮች ደግሞ፤ አሁንም በሰላም መንገድ፤ ከመቼውም የበለጠ በመጠናከር፤ በገዥው ፓርቲ ፍላጎትና ሕገ-ደንብ ሳይሆን፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ቆራጥነት ትግላቸውን ወደፊት ይገፉታል።
በሰላማዊ ትግል የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ሥልጣኑን ወዶ አይለቅምና በትጥቅ ትግል እንዝመትበት ለሚሉት፤ ይሄ በር አይከፍትም። የትጥቅ ትግል የራሱ የሆነ ሁኔታዎች አሉት። ይልቁንም ያሁኑ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መደናበር፤ ምን ያህል የሰላማዊውን ትግል እንደሚፈራውና እንዳይካሄድ ያለ የሌለ ጉልበቱን እንደሚያፈስበት ያስረዳናል። ለምን ብንል፤ የሕዝብ ድጋፍ የሌለው ስለሆነ ነው። የሕዝቡ ድጋፍ ከታጋዮች ጋር ነው። የሕዝቡ ድጋፍ ከሰላማዊ ታጋዮች በሆነበት ቦታ፤ ሰላማዊ ትግሉ ያብባል። ያድጋል። ይጎለብታል። የይስሙላ ግደባዎች አያቆሙትም። ጊዜያዊ አጥሮች የሚያዘገዩት አጥሮቹን እስኪያፈርሳቸው ድረስ ብቻ ነው። ሰላማዊ ታጋይ ድርጅቶች በምርጫዎች መሳተፍ አለባቸው። የሚሳተፉት ምርጫውን በመጠቀም ለሕዝቡ መልዕክታቸውን ለማስተላለፍ፣ ምርጫው ምን ያህል ውሸት እንደሆነ ለማሳየት፣ ለሕዝቡ የትግል ተሳትፎ በር ለማስፋትና ለማሳደግ እንጂ፣ የፓርላማ ወንበር አሟቂዎችን ቁጥር ለማብዛት አይደለም። ይህ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የሚመራው በፓርላማው ሳይሆን፤ በጀርባው ባስቀመጠው የጉልበት መዋቅሩ ነው።
በዚህ አሁን በሙሉ ኃይሉ እየተካሄደ ባለው ሰላማዊ ትግል ያገኘነው ዋናው ትምህርት፤ ይህ ትግል፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሥልጣኑ ባለቤት በማድረግ በኩል፤ የሚሳካው፤ መላ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት፤ በአንድ የትግል ማዕከል በሚመራ ትግል እንጂ፤ በተናጠል በሚደረግ ትግል አለመሆኑን ነው። መፍትሔ ለማምጣት በአንድነት መሰባሰብ፣ በአንድ ራዕይ መነሳትና መታገል ግድ መሆኑ ተስመረበት። ይህ እልል ያስብላል፤ ልንጠቀምበት ከቻልን።
በዚህ እየተደረገ ባለው ሰላማዊ ትግል፤ አንድ ዋና የኢትዮጵያዊያን ጠላት መኖሩን ተማርንበት። ትግሉ የሚያተኩረው የኢትዮጵያን ሕዝብ የሥልጣኑ ባለቤት ለማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ ዋናው ጠላት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ብቻ ነው። ሥልጣኑ በኢትዮጵያ ሕዝብ እጅ እንዲሆን፤ መላ ታጋዮች ባንድነት መታገል ያለባቸው መሆኑን ሁላችን እናውቃለን። እንዳይሰባሰቡ እስካሁን ያገዳቸው ምንም ሆን ምንም፤ አሁን ካሉበት ወጥተው ወደ ስብስቡ እንዲቀርቡ መንገዱ ግልጽ፣ በሩ ክፍት ሆኗል።
የታጋዮች ወደ አንድ መጠቃለልና ከድርጅቶች ሕልውና ይልቅ የሀገር ጉዳይ ቅድሚያ ማግኘቱ፤ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊት ልብ እንደሚያንኳኳ ጥያቄ አያስፈልገውም። በሩጫ የመጀመሪያው አባል ለመሆን ግን የሚቀድመኝ እንዳይኖር ተዘጋጅቻለሁ። በርግጥ ብዙ እጅግ ብዙ ከኔ በፊት አባል ለመሆን እንደሚሽቀዳደሙ ጥርጥር የለኝም። ሁላችንም እልል እንበልና ለሩጫው እንዘጋጅ። እኔ ጫማዬን አጥልቄያለሁ። eske.meche@yahoo.com በሉ የዚህ ስብስብ ድርጅት አባል አብረን እንሁን።

No comments: