Saturday, March 14, 2015

“አሻንጉሊቶች ናችሁ!”

በስድስት ኪሎ የዩኒቨርሲትው ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው የበዕደ ማርያም ትምህርት ቤት ተማሪ ልሆን ወደ አዲስ አበባ ሳመራ፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ትልቁ የግቢው አሽከርካሪ እምብርት ነበር። ባለፈው ዓመት የታሠሩት ተማሪዎች ሲፈረድባቸው፤ ከታሣሪዎቹ አንዱ፤ “እናንተ ጉልቻዎች፤ ንጉሡ የሚያዛችሁን ማድረግ እንጂ ሌላ ምን ታውቃላችሁ!” ማለቱንና ቅጣቱን ከሶስት ዓመት ወደ አምስት ዓመት እንዳዛወሩበት ሰምቻለሁ። በኋላ ሲፈታ ጉዳዩን እንደ ቲያትር አድርጎ ገልፆልኛል። እውነቱንም ነበር። ዳኞቹ ወንበራቸውን ጠባቂዎች እንጂ ነፃነት አልነበራቸውም። ይህ ጉዳይ አልተለወጠም። በደርግም ይሁን በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ቀጥሏል። እናም ዛሬ ደግሞ አብረሃ ደስታ፤ “እኛ የደፈርነው ችሎት አሻንጉሊት ችሎት ነው። ድሮውንም የተፈረደ ችሎት ነው።” በማለት ፍርዱ ተሠጥቷቸው የመጡና ያንን ለማብሰር ብቻ የተጎለቱ መሆናቸውን ገለጸ።
እዚህ ላይ ችግሩ የተከሳሾቹ ሳይሆን የዳኞቹ ነው። አብረሃ ደስታ የተናገረውን ይረዱታል የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም፤ ያንን መረዳት ቢችሉ ኖሮ፤ በዳኝነት የተሰየሙት በዚያ የፍርድ ወንበር አይቀመጡም ነበርና! የታሠሩት ዳኞቹ ናቸው። መብት የሌላቸው ዳኞቹ ናቸው። አብረሃማ የልቡን ተናገረ እኮ! ነገራቸውኮ! ለሚሠጡት መልስ አሁንም መጠበቅ ያለባቸው ዳኞቹ ናቸው። “የምትናገረው ነገር እንደገና ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ የሚወስድህ ጉዳይ ነው፤ ምርመራ ይደረግበታል” ሲሉ መለሱለት። ይህ የሚያሳየው፤ የታዘዙትን ፈጻሚ እንጂ፤ በቀጥታ በቦታው መወሰን የማይችሉ አሻንጉሊቶች መሆናቸውን ነው። በሕገ ደንቡ የሰፈረ ካለ፤ ምርመራ ለምን ያስፈልጋል?
አብረሃ ይኼን ሊያስረዳቸው፤ “አሁንስ ቢሆን የምናገረውን ፖሊስ እየሰማ አይደለምን?” ሲል መለሰላቸው። አሁንም አልገባቸውም። አብረሃ፤ “የምን ምርመራ አስፈለጋችሁ? ይኼው በግልጽ ባደባባይ ተናገርኩ። የተናገርኩት ትክክል ካልሆነና የሚያስቀጣ ከሆነ፤ ሕጉን ጠቅሳችሁ ልትቀጡኝ ትችላላችሁ። የምን ምርመራ ነው?” ነበር ያላቸው። አልገባቸውም። ሊገባቸውም አይችልም። በገቡበት ትምህርት ቤት፤ የፍርድ ትምህርትና ዳኝነት ሳይሆን፤ ካድሬነት ተምረው የወጡ ናቸውና! አሁንም መልሳቸው፤ “ፖሊስ የሚነግረንና የታዘዝነውን ፈጻሚዎች ነን።” ነበር። እናም ስለማይችሉ፤ “ትዕዛዝ እስክናገኝ ጠብቅ!” ብለውት ወጡ። አይገርማችሁም? ዳኝነት እኮ፤ አንድ ክስ ተመስርቶ ከዳኛው ፊት ሲቀርብ፤ የክሱን መሠረት በማዳመጥ፤ በተከሳሹ ላይ የቀረበው ትክክል ነው፤ ወይንስ አይደለም? የሚለውን አውጥቶ በማውረድ መዝኖ፤ ከተከላካዩ ወገንም ለመከላከያ የቀረበውን ወስዶ በማመዛዘን፤ ሁሉን በደንብ በመመርመር፤ በሕገ መንግሥቱና በመተዳደሪያ ደንቡ የሰፈረውን ትናኔና ቅጣት ተከትሎ፤ ውሳኔ መሥጠት ነው። ይኼ ግን በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የሚታሰብ አይደለም።
በመሠረቱ፤ የዳኞች ሁኔታና የፍርድ ቤቱ ችሎት፤ ከሌላው በሀገራችን ካለው ሥርዓት የተለዬ አይደለም። ፍርድ ቤቱ ነፃነት ኖሮት ሊሠራ የሚችል አካል አይሆንም። የፖሊሱም ክፍል እንዲሁ። በትምህርት ክፍሉ፣ በጤና ክፍሉ፣ በወታደራዊ አካሉ፣ የተለየ ነገር መጠበቅ፤ ሥርዓቱን አለማወቅ ነው። አብዮታዊ ዴሚክራሲን አለመረዳት ነው። ይህን በትክክል የተገነዘቡት እስረኞቹ እነአብረሃ ደስታ ናቸው። በመታሠራቸው እያሰተማሩ ናቸው። መታሰራቸው እራሱ ትምህርት ሆኖ፤ ሂደቱንም ትምህርት ቤት አድርገውታል። ተማሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ታጥቦ ጭቃ ቢሆንም፤ ሌሎቻችን ትምህርቱን በሚገባ በሥራ ላይ ማዋል አለብን።
Source: nigatu

No comments: