Sunday, March 8, 2015

በሽብርተኝነት ተጠርጥረው የተከሰሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ቅጣት ሊወሰንባቸው ነው

በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸውና በእስር ላይ የሚገኙት የአንድነት፣ የሰማያዊና የዓረና አመራሮች ችሎት በማወክ፣ በማንጓጠጥ፣ የችሎቱን ስም በማጥፋትና የችሎት ሒደትን በማስተጓጎል የቅጣት ውሳኔ ሊሰጥባቸው ነው፡፡
የአንድነት ፓርቲ አመራር አቶ ዳንኤል ሽበሺ፣ የዓረና ፓርቲ አመራር አቶ አብርሃ ደስታና የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ የሺዋስ አሰፋ ላይ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀጠሮ የሰጠው፣ ተከሳሾቹ የካቲት 26 ቀን 2007 ዓ.ም. በችሎት ውስጥ ፈጽመዋል በተባለው ድርጊት ነው፡፡
ችሎቱ ተከሳሾቹን (ከሌሎቹም ተከሳሾቹ ጋር) ለየካቲት 26 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀጥሮ የነበረው፣ ተከሳሾቹ በእስር ላይ በሚገኙበት ማረሚያ ቤት ታኅሳስ 12 ቀን 2007 ዓ.ም ለ13 አጥቢያ፣ ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት እስከ ረፋዱ አምስት ሰዓት ድረስ ከማረሚያ ቤቱ ውጪ ባሉ የደኅንነትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ፍተሻ በማድረግ፣ ሰነዶች ገንዘብ እንደተወሰዱባቸው ባመለከቱትና ማረሚያ ቤቱ በሰጠው ምላሽ ላይ ብይን ለመስጠት ነበር፡፡
ፍርድ ቤቱ በዕለቱ በሰጠው ብይን ተከሳሾቹ በጠበቃቸው አቶ ተማም አባቡልጉ አማካይነት፣ ከማረሚያ ቤቱ ባልደረቦች ውጪ ፍተሻ ተደርጎባቸው እንደተዘረፉ አቤቱታ ያቀረቡ ቢሆንም፣ ስለመዘረፋቸው የሚያስረዳ ነገር አለማቅረባቸውንና ፍተሻ አደረጉ የተባሉት አካላትም ከማረሚያ ቤት ውጪ የመጡ ስለመሆናቸው ያቀረቡት ማስረጃ እንደሌለ ገልጾ፣ አቤቱታቸውን ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
የፍርድ ቤቱን ብይን ተከትሎ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የሆኑት ተከሳሽ አቶ የሺዋስ አሰፋ በማጨብጨባቸው ለምን እንዳጨበጨቡ እንዲያስረዱ ፍርድ ቤቱ ሲጠይቅ፣ የተሰጠው ብይን ጥሩ ስለሆነ ተደስተው እንዳጨበጨቡ ይናገራሉ፡፡ በመቀጠልም የዓረና አመራር ተከሳሽ አቶ አብረሃ ደስታ ሐሳብ እንዳላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀው ሲፈቀድላቸው፣ ፍርድ ቤቱ የሰጠው ውሳኔ ትክክል አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እነሱ ማስረጃ እንዳላቸውና እንደሌላቸው ሳይጠየቁ ብይን መሰጠቱ ተገቢ ካለመሆኑም በተጨማሪ፣ ፍርድ ቤቱ (ችሎቱ) ከዚህ በኋላ ትክክለኛ ፍትሕ ይሰጣል ብለው ስለማያምኑ ከዚያን ቀን ጀምሮ ጠበቃቸውን ማስናበታቸውንና እንደማይከራከር ያስረዳሉ፡፡ ፍርድ ቤቱም ሐሳባቸውን እንደማይሰማቸውና እንደሚያሸማቅቃቸውም አስረድተዋል፡፡ 
የአንድነት ፓርቲ አመራር አቶ ዳንኤል ሺበሺም ጠበቃቸውን አለማስናበታቸውን ከመናገራቸው ውጪ አቶ አብርሃ ያቀረቡትን አስተያየት ደግመዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ በሰጡት አስተያየት ላይ ተመካክሮ፣ ችሎቱን በማወክና በማንጓጠጥ አቶ የሺዋስን ጥፋተኛ ካለ በኋላ፣ የቅጣት ውሳኔ በዕለቱ ለመስጠት ከሰዓት የቀጠረ ቢሆንም፣ ውሳኔው ሳይሰጥ ለየካቲት 27  ቀን 2007 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
የካቲት 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍርድ ቤቱ አብርሃ ደስታንና ዳንኤል ሽበሺንም ችሎት በማወክ፣ በማንጓጠጥና የችሎት ሥራን በማስተጓጎል ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡ ጥፋተኛ የተባሉት ተከሳሾቹ የቅጣት ሐሳብ እንዲያቀርቡ ሲጠየቁ ፍርድ ቤቱ እንደሚጨቁናቸው፣ በፍርድ ቤቱ ዕምነት እንደሌላቸውና ትክክለኛ ፍትሕ እናገኛለን የሚል ሐሳብ እንደሌላቸው ሲናገሩ፣ ፍርድ ቤቱም ተገቢ ንግግር አለመሆኑን በመግለጽ ለማስቆም ባደረገው ጥረት ለተወሰኑ ደቂቃዎች መሰማማት ያልነበረ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔውን መጋቢት 1 ቀን 2007 እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡
ሌላው ችሎቱ በተመሳሳይ የክስ መዝገብ ላይ ሰባተኛ ተከሳሽ አብርሃም ሰለሞን፣ ክሱ እንዲሻሻል በቀረበው ተቃውሞ ምክንያት ዓቃቤ ሕግ አሻሽሎ እንዲቀርብ የታዘዘ ቢሆንም፣ አሻሽሎ ባለማቅረቡ በድጋሚ አሻሽሎ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ የስምንተኛ ተከሳሽ የአቶ ሰለሞን ግርማ ክስ መሻሻሉን ገልጾ ችሎቱ አብቅቷል፡፡ 
Source: ethiopianreporter

No comments: