Thursday, March 26, 2015

የሙስና አሳነባሪዎችና ሻርኮች !!! ግርማ ካሳ

በዘጠና ሰባት አዲስ ዜና የምትሰኘዋ ነጻ ጋዜጣ ላይ የትምህርት ሚኒስቴሯ ገነት ዘዉዴ፣ የዉሃ ሃብት ሚኒስትሩ ሽፈራው ጃርሶ እና የከተማ ልማት ሚኒስተሩ ሃይሌ አሰግዴ ሶስት ትላልቅ ፎቆች እንደነበራቸው  ፎቶዎችን ዋቢ በማድረግ ዘግባ ነበር።
ያለፈውን ትተን ወደ አሁን ስንመለስ ደግሞ አይን ባወጣ መልኩ ከፍተኛ የሆነ የስልጣን መባለግን እያየን ነው። በአዲስ አበባ ቦሌ መድሃኔአም ፊት ለፊትና በቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጎን፣ የሚሰሩትና የተሰሩት ከአራተኛ ፎቅ ጀመሮ ያሉ ሕንጻዎች 90% በላይ የሆኑቱ፣ የሕወሃት ጀነራሎችና ባለስልጣናት ንብረት እንደሆኑ ይነገራል። በስምቸው፣ አሊያም በቤተሰባቸው ስም ያሰሩት ወይም የገዙት።
ለምሳሌ የሚከተሉትን ፎቶዎች ይመልከቱ። እነዚህ ፎቆች የሕወሃት ጀነራሎች እያሰሯቸው የነበረ አሁን ያለቁ ፎቆች ናቸው። እነዚህ ጀነራሎች ገንዘቡን ከየት አምጥተው ነው እንደዚህ አይነት ፎቅ የሚሰሩት የሚል መሰረታዊ ጥያቄ ይጠየቃል። መልሱን ለተመልካች መተዉ የሚሻል ይመስለኛል።
ሌላው ኢትዮጵያዊ በጠኔ እየተቃጠለ፤ ኢትዮጵያዊያን የኮንዶሚኒየም እጣ ዉስጥ ለመግባት ከአስር አመት በላይ እየጠበቁ፣ አምስት ሚሊዮን ህዝብ በምትኖርባት ከተማ በምርጫ ሰሞን ለፖለቲክ ተብሎ ጥራት በሌላው ሁኔት ጥቂት ሺዎች ኮንዶሚኒየም ብቻ እየተሰሩ፣ የኑሮ ዉድነት ሽቅብ ወደ ላይ እየተመዘገዘገ እነዚህ የሕወሃት ጀነራሎች ፎቆቻቸውን በአንዴ፣ ቢዝነሶቻቸን በአንዴ ገንብተው መጨረሳቸው፣ ያንን ያህል ወጭ የማወጣት አቅም ማግኘታቸው ተደባብሶ የሚያልፍ ነገር አይደለም። ኢትዮጵያ በርግጥ ለጥቂቶች ገነት ለብዙሃኑ ግን ገሃነም መሆኗን የሚያሳይ ነው እነዚህ ጀነራሎችና ሕወሃቶች፣ ወይም ከሕወሃቶች ጋር ትስስር ያላቸው፣ እላይ እየደረሱ (ሰርተው ቢሆን እሺህ ግን ሰርቀዉና መዝብረው) ሌላው ተምሮም፣ ጥሮም ግሮም፣ ኑሮን መግፋት ሲያቅተው ማየት በርግጥ እንደ ሕዝብ መውደቃችንን እና መዋረዳችንን የሚያሳይ ነው።
ይሄንን ስንል ፈጥረን እያወራን እንዳልሆነ ይታወቅልን። የምትመለከቷቸው ፎቶዎች ይመስክሩ። ሕሊና ያለውም ራሱን ይጠይቅ። ይሄ የስልጣን መባለግና የሕዝብን ንብረት መመዝበር፣ ህዝብን መናቅ አይደለምን ? ይሄ መንግስታዊ፣ ወያኔያዊ ሌብነትና ሙስና አይደለምን ? የሚያስቀው የማይታዘዙላቸውን ወይንም ጥያቄ መጠየቅ የጀመሩትን፣ ትናንሽ አሳዎችን በሙስና ስም እያጠመዱ፣ «ሙስና፣ ሙስና» ይሉናል። ሆኖም የሙስና አሳነባሪዎችና ሻርኮች እነርሱ ራሳቸው እንደሆኑ ግን የሚገነቧቸው ፎቆች ይመሰክራሉ።
እነዚህ ጀነራሎች እንደው በዛ ቢባል የሚከፈላቸው 10 ሺህ ብር ነው። የወር ደሞዛቸውንም እንዳለ ቢያጠራቅሙ በአመት ወደ 120 ሺህ፣ በሃያ አመት ደግሞ ወደ 2 ሚሊዮን ብር ቢሆን ነው። ምግብ፣ ልብስ፣ የመኪና ነዳጅ፣ ለልጆች የሚያስፈልጉ ወጨዎች አሉ። አሁን ባለው የኑሮ ዉድነት አንድ ኩንታ ጤፍ 2400 ብር ነው። ስለዚህ። ለአስቤዛ የሚወጣው ወጭ ቀላል አይሆንም። ግማሹን ደሞዛቸው አጥፍተው ግማሹን አጠራቅመው ነው ብንል እንኳን ሊኖራቸው የሚችለው ከአንድ ሚሊዮን ብር አይበልጥም። ታዲያ 40 50 ሚሊዮን ብር ከየት አምጥተውት ነው ?
ተበድረው ነው የሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል። ፎቶዎቹ ላይ የታየዉን ትንሹን የባጫ ደበሌን ፎቅ እንመልከት። እንደው በጣም ሃሪፍ ባንክ ተገኘና 12 ሚሊዮን ዶላር 3.0 % ወለድ በሰላሳ አመት ከፍሎ ለመጨረስ ብድር ተወስደ ቢባል እንኳን፣ ባጫ ደበሌ በወር 50 ሺህ ብር መክፈል ይኖርበታል።
የጀነራል ወዲ አሸብርን 55 ሚሊዮን ብር ፎቅ ከወሰድን ደጎ፣ ወዲ አሽብር ወርሃዊ ክፍያ 210 ሺህ ብር በወር ነው የሚሆነው።
ማንም ፕሮፌሽናል ባንክ ከወርሃዊ ገቢያችን 40% በላይ ያለው ብድር አያበድርም። ባጫ ደበሌና ወዲ አሸብር 10 ሺህ ብር ይከፈላቸው ከነበረ፣ ሊበደሩ የሚችሉት የወር ክፍያው 4 ሺህ ብር የሚሆን ብድር ብቻ ነው። ታዲያ 50 ሺሃና 210 ሺህ ወርሃዊ ክፍያ መክፈል የሚጠይቅ ብድር ሊያበድር የሚችል ባንክ የት ይገኛል ?
እንግዲህ ያለ ምንም ጥርጥር፣ እነዚህ ጀነራሎችና የሕወሃት ባለስልጣናት ስልጣናቸውን፣ የያዙት ጠመንጃ ተጠቅመው ከሕዝቡ የዘረፉት ገንዘብ ለመሆኑ ማንም ያወቀዋል።


No comments: