Monday, March 2, 2015

በኢህአዴግ ለባርነት የተሸጠችው ወገን ሰቆቃ


ኢትዮጵያ - “ህጋዊ የኮንትራት ሰራተኛ”፤ ሳውዲ - የባሪያ ባሪያ!!
genet-a
ገነት አበበ ሞላ ትባላለች፤ የልጅነት ጊዜዋን ሩጣ ያልጠገበች በአስራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ ኮረዳ ነች። ከዛሬ 3 አመት በፊት ነበር በኑሮ ውድነት የተጎሳቆሉ ቤትሰቦችዋን ከድህነት ለመታደግ በወቅቱ እስከ ገጠር በዘለቀው የአሰሪና ሰራተኛ የደላሎች ዘመቻ ከአርሲ ኮሌ ወረዳ ኩዬ ከተማ ተመልምላ የማይጨበጠውን የአረቡን ዓለም መከራ ለመጋፈጥ ተስፋ ሰንቃ ወደ ሳውዲ አረቢያ ያቀናቸው።
በወቅቱ በሰው ልጆች ህይወት ዶላር ለማግበስበስ በየአካባቢው በተከፈቱ የአሰሪና ሰራተኛ ኤጀንሲ ደላሎች ከእናቶቻቸው ጉያ ተነጥቀው ለአቅመ ሄዋን ያልደረሰውን እድሜዎቻቸውን ቆልለው ፓስፖርት የወሰዱ ህጻናት ሳይቀሩ በቀን 1500 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን የኮንትራት ሰራተኞች ያለህይወት ዋስትና ወደ ሳውዲ አረቢያ በጅምላ ይላኩ የነበረበት ወቅት በመሆኑ ወጣት ገነትም ሰው እንደሆነው እሆናለሁ ብላ በፌስታል የተሞሉ ልብሶቿን ይዛ የምትወዳቸውን ወላጆቿን በዕንባ የተሰናበተቸው። አንድም ቀን ከቤት ወጥታ የማታውቀውን ገነት አስረክበው ወደ ቀዬያቸው የተመለሱ ወላጆቿ የገነትን ድምጽ ቢናፍቁም ባህር አቋርጣ ሳውዲ ሄደች ከተባለ ወዲህ ወራት ተቆጥረው ዓመት ቢደፍንም ገነትን የበላ ጀብ አልጮህ አለ።
ወትሮስ ለማን አቤት ሊባል? “የገነትን ስቃይ ማን ይወቅላት?” ክፉ አጋጣሚ ሆኖ  በአሰሪዎቿ “ኃይል” ወደሚባል ገጠራማ የሳውዲ ግዛት ለስራ የተወሰደችው ገነት ወግ ባህሉ ቋንቋው ባዕድ በሆነባት ሃገር ሁሉም ነገር እንዳሰበቸው እና እንደተነገራት አልነበረም።  ታዲያ ገነት ከቤትሰቦቿ ጋር ስትለያይ ሲያነቡ የነበሩት አይኗቿ እንባ እንደቋጠሩ ነበር    ፍጹም ከባድ የሆነውን የአረቡን ዓለም የቤት ስራ የተጋፈጠቸው፡፡
genetበማለዳው ምናምን ቢጤ ቀማምሳ ለአመታት ተጠርጎ የማያውቀውን አቧራ የለበስና ቆሻሻ የተከመረበትን ግቢ ከአሰሪዎቿ በምልክት በተሰጣት ትዕዛዝ ስታፀዳና ከ4 ያላነሱ መኪኖችን ስታጥብ መዋል የዘወትር ተግባሯ ሆነ። በዚህ መልኩ ለወራት የተዋሃዳትን የአሰሪዎን የቤት ውስጥ ስራ ጨምሮ የማይመለክታትን ከባድ ስራዎች ሁሉ ካጠናቀቀች በኋላ ለሌላ አረብ ተላልፋ እየተሰጠች የቤት ሰራተኛ ለሌላቸው የሰፈሩ አረቦች ሁሉ አገልጋይ ሆናለች።
ገነት እረፍት የላትም እንደ ዘበኛ መኪና በመጣ ቁጠር የግቢ በር ትከፍታለች፤ የአሰሪዎቿን መኪናና ግቢ ታጥባለች፤ ከባድና ቀላል የሆኑ እቃዎችን እስከ 3ኛ ፎቅ ተሸክማ በመውጣት ከአቅም በላይ የሆነና የማይመለከታትን ስራ በግዳጅ እንድትሰራ ትደረጋለች። ከቤተሰቦቿ ከተለየች ወዲህ በስልክ ወላጆቿን አግኝታቸው የማታውቀው ገነት ከሥራው ክብደት ይልቅ በናፍቆት ከሰውነት ጎዳና የወጣው አካሏና የልጅነት ወዝ በቁም የተገነዘች ሬሳ አስመስሏታል፡፡
በአስሪዎቿ ታግት በደል የሚፈጸምባት ገነት አበበ ሞላ ከሚፈፀምባት ግፍ እና በደል  እግር ወደ መራት በመሄድ እርሷን ከባርነት ለመታደግ የሞከረችበትም አጋጣሚ እንደነበር ይነገራል። ከዚያ ወዲህ ገነትን ለማግባባት ብዙ ሞክረው እንዳልተሳካላቸው የተረዱት አሰሪዎቿ ገነት ላይ የሚያደርጉትን ክትትል በማጠናከር የስራ ግዳጅዋን ስትጨርስ ባዶ ቤት ይቆለፉባታል። የቤት ሰራተኛ እጥረት የገጠማት ሳውዲ አረቢያ ውስጥ በአሰሪዎቿ የታገተቸው ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ገነት አበበ ለአሰሪዎቿ እያበረከተች ካለው ነጻ አገልግሎት ባሻገር በወር እስከ 3800 በሚደርስ ክፍያ ለሦስተኛ ወገን ተላልፋ በመሰጠት ጥሩ የገቢ ምንጭ እስከ መሆን መድረሷ ይነገራል። ከአንዱ የአረብ መኖሪያ ወደ ሌላው የአረብ መኖሪያ ቤት እየተቀባበሉ ያለ በቂ እረፍት የአረብ አገልጋይ ለመሆን የተገደደቸውን ኢትዮጵያዊት “የኮንትራት ሰራተኛ” ከማለት ይልቅ በኢህአዴግ ህጋዊ ፈቃድ አግኝቶ በሚንቀሳቀስ አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ የተሸጠች ባሪያ ማለት ይቀላል።
አዲስ አበባ ውስጥ በተለምዶ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ ሴብሪን “sebirn” እየተባለ በሚጠራ አንድ ኤጀንሲ አማካኝነት ተዋውላ “ህጋዊ” በሆነ መንገድ ለስራ ሳውዲ እንደገባች የሚነገርላት ገነት ዛሬም የድረሱልኝ የሰቆቃ ድምጽዋን ታሰማለች – የሚሰማት ካገኘች!
አሁን አሁን ለህይወቷ የምትሳሳው ገነት ይገሉኛል በሚል ስጋት በድብደባ ከተጎሳቆለው አካሏ ባሻገር ሌሎች ምስጢራዊ በደሎችን ለግዜው ከመግለጽ መቆጠቧን ለልጅቷ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይገልጻሉ። እነዚህ ወገኖች አቤቱታቸውን በጅዳ ለኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት ቢገልጹም እስክ አሁን የገነት የሰቆቃ ድምጽ ምላሽ አላገኘም፡፡
ሰሞኑን በደመወዝ ጥያቄ በጥይት የቆሰለችውን ኢትዮጵያዊት ከወራት ቆይታ በኋላም ቢሆን እውነታውን በአካል ሄደው ያረጋገጡት የጅዳ ቆንስላ ጽ/ቤት ሃላፊዎች የሰቆቃ ድምጽ ለምታሰማው ወጣት ገነት አበበ ሞላ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል። ይህ በዚህ እንዳለ በዚህ መልኩ ሳውዲ አረቢያ ውስጥ በ10 ሺህ የሚቆጠሩ እንደ ጨው ተበትነው ያሉበት ሁኔታ በውል የማይታወቅ ግፍ እና በደል እያስተናገዱ የሚገኙ እህቶች መኖራቸው በተደጋጋሚ ተገልጾል። (Ethiopian Hagere Jed Bewadi)

No comments: