Thursday, September 8, 2016

በቂሊንጦ አደጋ የሞቱትስ እነማን ናቸው?


Kilinito-Picture /Google

በቂሊንጦ ወህኒ ቤት የደረሰውን የእሳት አደጋ ተከትሎ አሁንም የኢትዮጵያ መንግስት የሟቾችን ማንነት ለመግለፅ ፈቃደኛ አይደለም። ይልቁንም ከአደጋው የተረፉትን እስረኞች ስም ዝርዝርና የሚገኙበትን ወህኒ ቤት ገልጿል። ታዋቂ የፖለቲካ መሪዎችና ጋዜጠኞች ከአደጋው መትረፋቸው ታውቋል። የሟቾችን ማንነት ከመግለፅ ይልቅ የተረፉትን የመግለፅ አካሄድ ሰለአደጋው ዝርዝር የሚነሱ ጥያቄዎችን ለማዳፈን የተቀየሰ ስልት ሳይሆን አልቀረም። ከእሳት አደጋው በተጨማሪ በእስር ቤቱ ውስጥ የተኩስ እሩምታ እንደነበር መገለፁ ሁኔታውን አጠራጣሪ አድርጎታል።
በኦሮሚያ ከተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ በርካታ አባላቱ ለእስር የተዳረጉበት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሩ በቀለ ገርባን ጨምሮ የስራ አመራር ኃላፊዎቹ በህይወት እንደሚገኙ መረጃ ማግኘቱን ለዋዜማ ገልጿል፡፡ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ እንደሚናገሩት ከሆነ እስረኞቹን እስካሁን በአካል ባያገኟቸውም በቂሊንጦ እንደሚገኙ ከቤተሰብ መረጃውን አግኝተዋል፡፡
ማረሚያ ቤቱ ቂሊንጦ መኖራቸውን ለቤተሰብ ተናግሯል፡፡ እኞ ደግሞ መረጃውን ከቤተሰብ ሰምተናል ሲሉ አቶ ሙላቱ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ አጠቃላይ ዝርዝር ይዘን ሄደን ለመጠየቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ ለቤተሰብ ብቻ ነው መረጃ የሚሰጡትብለዋል፡፡
እስካሁን ባሰባሰቡት መረጃ መሰረት ከበቀለ ሌላ የፓርቲው ምክትል ዋና ጸሀፊ ደጀኔ ጣፋ፣ የወጣቶች ጉዳይ ሊቀመንበሩ ደስታ ዲንቃ እና ምክትላቸው ጉርሜሳ አያኖ፣ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊው ደረጀ መርጊያ እንደዚሁም የወጣቶች ጉዳይ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አዲሱ ቡላላ በህይወት መኖራቸውን እንደሰሙ ገልጸዋል፡፡
እኛ የአንድ ሰው ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሁኔታ ያሳስበናልሲሉ መረጃ ለማግኘት የገጠማቸውን ችግር ያስረዳሉ፡፡
ኢትዮጵያ መንግስት ከቃጠሎው አደጋ በኋላ የሟቾቹንም ሆነ የሌሎቹን እስረኞች ሁኔታ ባለመግለጹ ከፍተኛ ትችት እና ወቀሳ በማህበራዊ ድረ-ገጾች እና በብዙሃን መገናኛ አውታሮች ሲያሰተናግድ ቆይቷል፡፡ መንግስት ከአደጋው የተረፉ እስረኞች የት እንደሚገኙ በዝርዝር ያሳወቀው አደጋው ከደረሰ ከአምስት ቀን በኋላ ዛሬ ጠዋት ነው፡፡
በህይወት ከተረፉት ውስጥ የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው ዮናታን ተስፋዬ እና የፓርቲው ልሳን በሆነውነገረ ኢትዮጵያዋና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ይገኙበታል፡፡ ዮናታን እና ጌታቸው በሽብር ወንጀል ተከስሰው ጉዳያቸውን ቂሊንጦ በእስር ሆነው ይከታተሉ ነበር፡፡ ከአደጋው በኋላ ዮናታን በቂሊንጦ እንዲቀር ሲደረግ ጌታቸው ወደ ዝዋይ እንደተወሰደ የቂሊንጦ አስተዳደር ያወጣውን የስም ዝርዝር የተመለከቱ ይናገራሉ፡፡
ወደ ዝዋይ የተወሰዱ እስረኞችን ለመጎብኘት ዛሬ ረፋዱን በርካታ ቤተሰብ ወደ ቦታው ቢያቀናም ከተዛወሩ እስረኞች ጋር ለመገናኘት ባለመፈቀዱ ለእንግልት መዳረጋቸውን በቦታው የነበሩ ጠያቂዎች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ የዝዋይ ማረሚያ ቤት አስተዳደርየእስረኞቹ ዝርዝር እንደደረሰን መጠየቅ ትችላላችሁየሚል ምላሽ ለቤተሰብ እንደሰጠ ጠያቂዎቹ ይገልጸሉ፡፡
መንግስት በአደጋው የሞቱት እሰረኞች ቁጥር 23 መሆኑን ሰኞ ምሽት በሬድዮ ፋና በኩል ቢያሳወቅም እስካሁንም በይፋ ማንነታቸውን ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡ እንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ግን ከሟቾቹ ውስጥ የተወሰኑትን አስክሬን መንግስት ለቤተሰቦች ሰጥቷል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የሆነው የኤፍሬም አዲሱ ቀብር ትናንት ሐሙስ መከናወኑን ዋዜማ የሀዘን ስነርዓቱን ከተካፈሉ ምንጮች መረዳት ችሏል፡፡ ነዋሪነቱ በአዲስ አበባ ፈረንሳይ ለጋሲዮን በተለምዶ ደበላ ሰፈር ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ የነበረው ሟች ኤፍሬም አስክሬኑ ለቤተሰቦቹ የተሰጠው ረቡዕ ምሽት ሶስት ሰዓት አካባቢ እንደነበር ምንጮች ይናገራሉ፡፡
ዋዜማ ራዲዮ

No comments: