Wednesday, September 7, 2016

ነባር ታጋዮች እና ነባራዊ ሁኔታው "አንዳንድ ኢትዮጲያዎች" (አሌክስ አብርሃም)

ባለፉት ቀናት በኢቢሲ ነባር ታጋዮች ሲወያዩ ነበር .... ሳስበዉ ይህ ውይይት ከዚህ በተሻለ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ማተኮር ይችል ነበር !! ነባር ታጋዮች ነባራዊው የአገራችን ሁኔታ ጋር ተላልፈዋል ! ከታች ያለው ካድሬና ደጋፊ ደግሞ የባሰ ከህዝቡ ጋር እንደሚተላለፉ ማሰብ ቀላል ነው !!
ችግሩን ዙሪያውን ማከክና ቁስሉን ማባባስ 25 ዓመት ገድል እየደገሙ ማሰልቸት አሁን ካለው ሁኔታ ጋር ያን ያህል ተዛምዶ ያለው አልመሠለኝም ! ዉይይቱ ጠቅለል ሲል
"ህገ መንግስታችን... ፖሊሲያችን ችግር የለበትም አፈፃፀማችን እንጅ" ነው !! እንግዲህ ህገ መንገስትም ይሁን ፖሊሲ የፈጣሪ ቃል አይደለም ህዝብ እንደዳዊት ደግሞት እንደቁርዓን ቀርቶት ፈፃሚውን "ብታደርግም ባታደርግም እናመሠግናለን ለሺህ ዓመት ንገስ" ሊል አይችልም !!
አንድ መንግስት ራሱ እተዳደርበታለሁ የሚለውን ህግ መፈፀም አልቻልኩም ካለ ህዝብ አደባባይ ወጥቶ " አልቻልክም " ሲለው ለምን ያስራል ለምን ይገድላል ? ይሄ በኃይል ዝም ማሰኘትስ እድሜው ምን ያህል ነው ? ዋና ዋና ሂደቶችን በማየት ሃይል ምን እንደፈየደ እንመልከት ....
1993 ዓም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አመፅ ተነስቶ ነበር....በዚያ አመፅ ንብረት ወደመ በርካታ ተማሪዎችም ወደጎረቤት አገራት ተሰደዱ ! እና መንግስት እንዲህ አለ "በአንዳንድ አፍራሽ ተማሪዎች የተነሳው ብጥብጥ በቁጥጥር ስር ዉሏል !! ያኔ ጥያቄው የአንዳንዶች አልነበረም !! ስላልነበረም በህዝቦች ልብ ውስጥ ተዳፍኖ ሲቀጣጠል ቆየ !!
ቀጥሎ ከአራት አመት በኀላ አዲስ አበባ በምርጫ 97 አመፅ ሲነሳ የያኔው ኢቲቪ ምናለ ?"በአንዳንድ የአአ መንደሮች የተነሳው ብጥብጥ በቁጥጥር ስር ዉሏል" ከመዋሉ በፊት በአስርሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደአሰቃቂ እስር ቤቶች ተነዱ ! በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ህይወት በአደባባይ በተከፈተባቸው ተኩስ ረገፈ ...አለምም ድርጊቱን በግልፅ አወገዘው ! ጥያቄው ግን የመላው ኢትዮጲያዊ ነበር !! በኀይል ቢዳፈንም በሁሉም ልብ ውስጥ ተደብቆ ቆየ !ይሄንኛው ከመጀመሪያው የጠነከረና የከፉ ነበር !
ቀጥሎ የሙስሊሞች ጥያቄ ተነሳ ...በአንዳንድ አክራሪዎች ተባለ ....ጥያቄው ግን በሚሊየን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ነበር ......ይሄንኛው ደግሞ ከመጀመሪያዎቹ ሁለት አመፆች በተሻለ ቅርፅ የያዘና የተደራጀ ነበር ! እንደውም የት እንዳለ ማን እንደሆነ እንኳን የማይታወቅ ሃይል የመንግስትን ተሰሚነት በቁሙ ነጥቆ "ድምፃችን ይሰማ" በሚል መሪ ቃል ህዝበ ሙስሊሙን ሲመራው ነበር !
ቀጠለ.... በመላው ኦሮሚያ አመፅ ተቀሰቀሰ ....ከመጀመሪያዎቹ ሶስት አመፆችና ተቃውሞዎች በላይ በርካታ አካባቢዎችን የሸፈነ የበርካታ ንፁሃን ህይወትም የቀሰፈ ነበር መንግስት ግን አሁንም "በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በፀረ ሰላም ሃይሎች በተነሳ ሁከት " ብሎ ለማቃለል ሞከረ .... የቻለውን የሃይል ርምጃም ወሰደ ግን ማቆም አልቻለም !
ቀጠለ ... በአማራ ክልል ጎንደር የህዝብ ተቃውሞ ተነሳ "አንዳንዶች" ዜና የቸገረ ጭራሽ ግን አንዳንዶች በሚል ርእስ ዜና የተሰራለት አመፅ ...ይሄኛው ካለፉት ሁሉ የባሰ ሆነና አረፈ በሚያስደነግጥ ፍጥነት መላውን የአማራ ክልል እያዳረሰና ወደሁሉም አካባቢዎች እየሰፋ የመጣ ተቃውሞ ሆነ !!
አሁን መንግስት "አንዳንዶች" ያረጀና ያፈጀ ብሂል አቁሞ የህዝብ ተቃውሞዎቹ ምን ያህል እያደጉና እየጠነከሩ እንዲሁም እየተደራጁ እንደመጡ አውቆ ቢመረውም ምክንያትና ስም መለደፉን አቁሞ የመንግስትም የህዝብም ሆድ ለሚያውቀው አንኳር አንኳር ችግር የሚታይ የሚታመንበት አገርን በጋራ የሚታደግ መፍትሄ የሚያስቀምጥበት ሰዓት ይመስለኛል!! አሁን ሁሉም ነገር " አንዳንድ ኢትዮጲያዎች " ላይ ደርሷል !!
ቀጥሎ ምን እንደሚፈጠር ማንኛችንም አናውቅምና "አንዳንድ ባለስልጣናት" ወደቀልባቸው ተመልሰው ጤናማ አገርና ህዝብን የሚታደግ መፍትሄ ማቅረብ ይኖርባቸዋል !!በተጨማሪም ክልሎች በየጓዳቸው በመግለጫ ስም የሚያወጡትን ህዝብን አጋጭ መርዘኛ መልእክት ማቆም አለባቸው ! በተለይ በሁለት ክልል ህዝቦች መሃል ግጭት የተፈጠረ በማስመሠል በሌሎች ክልሎች ስም የሚወጡ አዛኝ ቅቤ አንጓች የውግዘት መግለጫዎች አገር አፍራሽ ፀያፍም ናቸውና በፍጥነት ከዚህ ድርጊት መታቀብ አስፈላጊ ነው !
አገራችን ላይ (((የመንግስትን ብልሹ አስተዳደር ))) በመቃወም ህዝቦች በተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞ እያሰሙ ነው !! ማንም ህዝብ ከማንም አልተጋጨም ማንም ህዝብ በተለይ የጥቃት ኢላማ አይደለም ! መንግስት "አመፀኛ" ያላቸው ላይ የሚተኩሰው ጥይት ሰልፈኞችን ስቶ ህፃናት ላይ እንደሚያርፈው ሁሉ "አመፀኞችም" የሚወረውሩት ድንጋይ መንግስት ያሰማራቸው የፀፅታ አካላትን ስቶ ንፁሃን ንብረት ላይ ሊያርፍ ይችላል ብሎ ህዝብ መሃል የሚዘራ ቂምን ማብረድ ደግ ነው !!
ሻሎም !!


No comments: