Monday, September 26, 2016

ሦስቱ የሕዝብ ማስጠንቀቂያዎች

ሕዝብ ለመሪው በሦስት ደረጃ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፡፡ የመጀመሪያው ‹አርም› የሚል ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ሕዝቡ ሦስት ነገሮችን አምኗል ማለት ነው፡፡ አንድም መሪው በጎ ኅሊና አለው፤ ለማረም የሚችል ዐቅም አለው፤ ችግሩ የተፈጠረው ከአሠራሩ ላይ ነው ብሏል፡፡ አንድም ደግሞ ሕዝቡ መሪው እንደማንኛውም ፍጡር ተሳሳተ እንጂ ራሱ ስሕተት አይደለም፡፡ ስለዚህ ሊያርም ይችላል ብሎ አምኗል፡፡ በመጨረሻም ሕዝብ መሪውን ይወዳል፣ ስሕተቱን ግን ይጠላል ማለት ነው፡፡
እዚህ ላይ የደረሰ መሪ የታደለ የሚሆነው ስሕተቶቹን ነቅሶ ‹ሳይርቅ በቅርቡ፣ ሳይደርቅ በርጥቡ› ለማረም ከቻለ ነው፡፡ የሚሳሳት ፈጣሪ እንደሌለ ሁሉ የማይሳሳት መሪ የለም፡፡ መሪዎችን ታላቅና ታናሽ የሚያደርጋቸው ስሕተታቸውን ለማመንና አምነውም ለማረም ያላቸው ዐቅምና ቁርጠኛነት ነው፡፡ መሪ የሕዝቡን ጥቆማ ሰምቶ፣ የሕዝቡንም ልብ አድምጦ ችግሩን በጊዜ ካረመ ስሕተቱ ከሥራ የመጣ እንጂ ከመሪው ጠባይ የመነጨ አይደለም ብሎ ሕዝብ በመሪው እንዲተማመን ያደርገዋል፡፡ ‹ከሰው ስሕተት፣ ከብረት ዝገት አይጠፋም› ብሎ ያልፈዋል፡፡ ሕዝብ የነገረውን ስሕተት ከማረም ይልቅ ‹እኔ ደኅና ነኝ ችግሩ ከአፈጻጸሜ የመጣ ነው› እያለ ችላ ካለው ሕዝብ ወደ ሁለተኛው ደረጃ ይሻገራል፡፡ ጃን ሜዳ ሠፍሮ እያደመ ራስ ተፈሪን ወደ ዙፋን ያመጣው መሐል ሠፋሪ ጦር (ሠራዊቱ) ነበር፡፡ በኋላም አርሙ ቢላቸው አላርም ሲሉ በ1953 መፈንቅለ መንግሥት ያደረገው ይኼው ሠራዊት ነው፡፡
ሁለተኛው የሕዝብ ማስጠንቀቂያ ‹ታረም› የሚል ነው፡፡ ሕዝብ መሪውን ‹ታረም› ካለ ሁለት ነገሮችን አስቧል፡፡ ‹መሪው ልክ ነበር ነገር ግን እንደማንኛውም ፍጡር ተሳስቷል› የሚለው ሐሳቡን ቀይሯል፡፡ ‹መሪው ስሕተቱን ሊያርም ይችላል› ከሚለው ወጥቷል፡፡ ይህንን ዕድል ላይመለስበት አልፎ መሪው ስሕተት የሚሠራ ሳይሆን ስሑት (የተሳሳተ) መሪ ነው፡፡ ስሕተቱ ከሥራ ሂደት ሳይሆን ከአመራሩ፣ ከአስተሳሰቡና ከአካሄዱ የመጣ ነው፡፡ ተግባሩ እንዲስተካከል መሪው መስተካከል አለበት ብሎ ሕዝቡ አምኗል ማለት ነው፡፡ ከኩርንችት በለስ፣ ከአጋምም ወይን ሊለቀም አይችልም፡፡ ውኃው እንዲስተካከል ምንጩ መስተካከል አለበት ብሎ ሕዝብ ማሰብ ጀምሯል፡፡ እንደዚያም ቢሆን ግን መሪው ራሱን ሊያረም የሚችል መሪ ነው ብሎ አምኗል፡፡
በዚህ እከን ላይ የደረሰ መሪ ራሱን ፈትሾ፣ መርምሮና አንጥሮ እንደ ወይን ግንድ እየገረዘ ሸለፈቱን መጣል አለበት፡፡ ሌላውን ሰውነት ለማዳን ሲባል ሕመምተኛው የሰውነት አካል እንደሚቆረጠው ሁሉ ሀገርን ለማዳን ሲባል የሚቆረጡ አሠራሮች፣ አስተሳሰቦች፣ አካሄዶች፣ መሪዎች፣ ፖሊሲዎችና መርሖች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ‹ታረም› የተባለ መሪ እነዚህን አርሞ እንደ እባብ ሳይሆን እንደ ንሥር ታድሶ ከመጣ፤ ጥፋቱ ከአፈጻጸሜ የመጣ ነው፣ ሕዝቡ ስላልገባው ነው፣ ስላልተማረ ነው፣ ስላልሠለጠነ ነው፣ እያለ የመሥዋዕት በግ ፍለጋ ካልኳተነ፤ ‹ችግሩ እኔ ነኝ፤ መፍትሔውም የእኔ መለወጥ ነው› ብሎ ካመነ፤ አምኖም ከሠራ፤ ሠርቶም ከተለወጠ፡፡
ሕዝቡ፡-
‹አሁን ወጣች ጀንበር
ተሸሽጋ ነበር› ብሎ ይቀበለዋል፡፡
ይህንን ሁሉ ትቶ መሪው በሕዝቡ ትዕግሥት ላይ ከቀለደ፤ ሕዝብም ለትዕግሥቱ ምላሹ ካለፈው የባሰ፣ ከተስፋው ያነሰ ሲሆንበት፤ ሕዝብ አመለካከቱን ይቀይራል፡፡ አርም፣ ታረም ማለት ዋጋ አልባ መሆኑን ይረዳል፡፡ ሊያርም ሊታረም የሚችል መሪና አመራር የለም ብሎ ያምናል፡፡ ችግሩ መሠረታዊ ነው ብሎ ይረዳል፡፡ በዚህ ጊዜ ሦስተኛውንና የመጨረሻ ማስጠንቀቂያውን ይሰጣል፡፡ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴን ሆ ብሎ ወደ ሥልጣን ያመጣው ወታደር፣ ስሕተቶቻቸውን ማረም ሲያቅታቸው በ1953 መፈንቅለ መንግሥት ያደረገው ወታደር፤ በ1966 ደግሞ ሥልጣናቸውን አሳጣቸው፡፡ የ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት ‹ታረም› የሚል መልእክት እንዳለው ንጉሡ ቢረዱ ኖሮ የ66ቱን ነገር ያስቀሩት ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ‹ታረም› የሚለውን አልረዳ ሲሉ ‹ተወገድ› የሚለው የመጨረሻው ማስጠንቀቂያ መጣ፡፡
ደርግም እንዲህ ነበር፡፡ በ66 አብዮቱ ሲፈነዳ፣ መሬት ላራሹ ሲታወጅ የሕዝብ ድጋፍ ነበረው፡፡ ቆይቶ ስሕተት ሲያበዛ ‹አርም› የሚለው መልእክት ከያቅጣጫው መጣ፡፡ ሰልፎች፣ ወረቀቶች፣ ተቃውሞዎች መጡ፡፡ ከማረም ይልቅ ‹መረምረም› ስለመረጠ የመጀመሪያውን ዕድል አሳለፈው፡፡ ከውስጥና ከውጭ ጠብመንጃ አንሥተው ግራ ቀኝ የወጠሩት ኃይሎች ‹ታረም› ቢሉትም መታረም ትቶ ማውደምን መረጠ፡፡ የ1981 ዓም መፈንቅለ መንግሥት ‹ተወገድ› የሚለውን መለከት ነፋ፡፡ ደርግ የሚተርፍ መስሎት ለፋ፡፡ ግን ተወገድ ከተባለ በኋላ መትረፍ በተአምር ብቻ ነበርና ሊተርፍ አልቻለም፡፡
ይህ ‹ተወገድ› የሚለው ሦስተኛው ማስጠንቀቂያ የመጨረሻው የሕዝብ ጥያቄ ነው፡፡ መሪው ታምሞ አይደለም፡፡ ራሱ በሽታ ነው፡፡ ተቸግሮ አይደለም፡፡ ራሱ ችግር ነው፡፡ ደክሞ አይደለም፡፡ ራሱ ደካም ነው፡፡ ተፈትኖ አይደለም፤ ራሱ ፈተና ነው ብሎ አምኗል፡፡ ስለዚህም መፍትሔው መወገድ ብቻ ነው ብሎ ይቆርጧል፡፡ ቆርጦም ይሠራል፡፡ ሕዝብ እዚህ ደረጃ ከደረሰ በኋላ መመለስ ብዙ ጊዜ ከባድ ነው፡፡ ማረምንም መታረምንም ከሚቀበልበት እርከን አልፏልና ቀሪው ዕድል የሚሆነው በሰላም መሰናበት ነው፡፡
የአንድ መሪ ብስለት በሁለት ደረጃ ይለካል፡፡ የመጀመሪያው ሲቻል በፊተኛው፣ ሳይቻል በቀጣዩ ደረጃ ላይ መንቃት፣ ነቅቶም ተገቢውን ማድረግ፡፡ ያም ዘመን ካለፈና ጀንበር ካዘቀዘቀች ደግሞ ራሱንም ሀገሩንም ሳያጠፋ መልካም የወንድ በር ማዘጋጀት ነው፡፡
ዘቦ እዝን ሰሚዐ ለይስማዕ፡፡

No comments: