Friday, September 2, 2016

በአማራው ክልል ላይ የታወጀው የጦርነት አዋጅ ዉጤት - #ግርማ_ካሳ

ፖርተር ጋዜጣ፣ ጀነራል አባበ ተክለሃይማኖትን ጨምሮ ብዙዎቻችን ቀደም ብለን ሕወሃት የሕዝብን ጥያቄ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በዉይይት እንዲፈታ፣ ለብሄራዊ እርቅ እንዲዘጋጅ ስንመከር፣ ካልሆነ ነገሮች በጣም እየከረሩ በመምጣታቸው ኢትዮጵያ እንደ ሲሪያ ልትሆን እንደምትችል ስናስጠነቅቅ ነበር።
በጣም ያሳዝናል። ሰሚ አላገኝንም። ይኸው ሶሪያን በትንሹ ማየት ጀመረናል። በአምባ ጎዮርጊስ፣ በባህር ዳር...የዜጎች ደም እየፈሰሰ ነው። ሕጻናት ሳይቀሩ። ከደብረ ታቦር እስረኞች በእሳት እየነደደ ካለ እሥር ቤት እንዳይወጡ ተደርገው፣ ሊወጡ ሲሉ በአጋዚ እየተተኮሰባቸው በቁማቸው እየነደዱ ነው። በመተማ የብዙ ወገኖች ቤት እየተቃጠለ ነው። መተማ ደርቡሾች ወረዋት ተነበረ ጊዜ እንኳን አሁን እንደሆነችው ሆና አታውቅም ነው የሚባለው።በጣም ብዙ ወገኖች የለየለት የርስ በርስ ጦርነት ስለተከፈተ፣ ከቤታቸው ተፈናቅለው ወደ ሱዳን እየሄዱ ነው። አብዛኞቹም የትግራይ ተወላጆች እንደሆኑ አቶ አምዶም ገብረስላሴ የአረና የሕዝብ ግንኙነት ክፍላ ሃላፊ ለአሜሪካን ድምጽ ራዲዮ ገልጸዋል።
በመተማ፣ በአምባ ጊዮርጊስና በበርካታ የአማራው ክልል ቦታዎች ጦርነቱ የተቀሰቀሰው በሕወሃት ነው። ችግሮች ከቁጥጥር በላይ እንዲሆኑ ያደረገው ሕወሃት ራሱ ነው።ለዚሁ ሁሉ ተጠያቂው ሕወሃት ነው የሚሆነው።
የሕወሃት ባለስልጣናት አብዛኞቹ የሚኖሩት አዲስ አበባ ነው። ባለ ፎቅ ናቸው። ባለ ዶላር ናቸው። ልጆቻቸው የሚማሩት በለንደን በኑዮርክ ነው። ጉንፋን ሲይዛቸው የሚታከሙት ታይላንድና አሜሪካ ሄደው ነው።
ግን በሚያራምዱት ዘረኛና አፋኝ ፖሊሲዎች፣ ለፍቅር፣ ለዉይይትና ለብሄራዊ መግባባት በራቸውን በመዝጋታቸው፣ ያለነርሱ አዋቂ፣ ያለነርሱ ተራማጅ ያለ ስለማይመስላቸው፣ አገር እየታመሰች ነው።
የግፍ ጽዋ ሞልቶ ስለፈሰሰ፣ ሕዝብ ተቃዉሞ አሰማ። የሕዝብን ተቃዉሞና ጥያቄ ከማዳመጥ ይልቅ በሕዝብ ላይ ጦርነት ከፈቱ። "ምሀረት የሌለበት እርምጃ እንወስዳለን" አሉ። እንዳሉትም በጭካኔ ህዝብ ላይ ጥይቶቻቸውን አርከፈከፉ።
በአማራው ክልል የተለያዩ ቦታዎች ተቃዉሞዎች ሲሰሙ መተማ በአንጻራዊነት ሰላም ነበረች። ሆኖም ግን፣ ህዝቡ ትግሬ፣ አማራ ሳይባባል፣ በሰላም በሚኖርበት ቦታ አጋዚዎች መጡ። በዚያ ያለውን ነዋሪ መደብደብ ጀመሩ። ሁለት የአማራ ተወላጆችን ገደሉ። ህዝቡ ተቆጣ ብጥብጥ ተነሳ። የብዙ ወገኖች ቤት ተቃጠለ። ከሃያ የሚበልጡ በአጠቃላይ ሕይወታቸውን አጡ። ብዙዎች ተሰደዱ።በጣም ያሳዝናል።
ከሁለት ወር በፊት በጎንደር ሰላም ነበር። ሕወሃቶች በሌሊት የወልቃይት የማንነት ኮሚቴ አባላትን ለማፈን በሌሊት እንደ ወንበዴ መጥተው በመረበሻቸው ነው ቀዉሱ የተነሳው። እንርሱ አርፈው ቢቀመጡ ኖሮ፣ የብአዴን የክልሉ መንግስት ችግርችን ከሕዝቡ ጋር እየተወያየ እንዲፈታ ቢያደረጉ ኖሮ ብዙ ነገሮች መፍትሄ ሊያገኙ ይችሉ ነበር። ግን ከጥጋባቸው የተነሳ የጎንደር ህዝብ "የሻእቢያ አሽከር ነው" እስከማለትም ደረሱ።
በአምባ ጊዮርጊስ ሕዝብ በሰላም ነበር የሚኖረው። በሰላም ተቃዉሞ አሰማ። ከየት እንደመጡ የማይታወቁ ታጣቂዎች፣ ሕጻናትን ሁሉ ሳይቀር ገደሉ። በየቤቱ እየገቡ መደብደብ ጀመሩ።አብዛኛው የከተማዋ ወንድ ሸሽቶ ወደ አካባቢ ጫካ ሄደ። ከአሁን በኋላ ቤታችን አንሄድ ሽፍቶች ነው የምንሆነው አሉ። ወጣቱትን ከቤቱ አማራው አስወጡት።
በዚህ ሁሉ ቀዉስ፣ ድሃው ትግሬ፣ ድሃው ጎንደሬ እንዲሰደድ፣ እንዲገደል እያደረጉ፣ሕወሃቶች ግን በሼራተን ዊስኪ መራጨት ነው ስራቸው።
ትግሬዉም አማራውም ይሄን ማወቅ አለበት። ለዘመናት በሰላም ነው የኖርነው። እነዚህ ሰይጣኖች መጥተው ነው፣ በዘር ከፋፍለው፣ እንድንቃቃር ያደረጉን። የሕወሃት አገዛዝን በቃ ብሎ በአማራው ክልል ህዝቡ ተቃዉሞ እያሰማ እንዳለው፣ በትግራይም ህዝቡ በሕወሃት ላይ መነሳት አለበት። አንደኛ የትግራይ አብዛኛው ግፍና መከራ እየተቀበለ ያለ ህዝብ ነው። ሁለተኛ ለአመታት የማይሽር ጠብና ቂም እንዲፈጠር አድርጎ ከሌላው ማህበረሰብ ጋር ትግሬዉን እያላተመው ነው።
ወገኖች የነዚህ ሰዎች የዘር መዘዝ፣ ይሄ የአማራ መሬት፣ ይሄ የትግሬ መሬት፣ ይሄ የኦሮሞ መሬት የሚሉት በሽታ ነው ችግር ያመጣብን። ሁሉም ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ናት የሚል ፖለቲክ ቢኖር ኖሮ፣ "ወልቃይት የትግሬ ናት፣ ወልቃይት የአማራ ናት፣ ሸዋ የኦሮሞ ነው፣ ሸዋ የአማራ ነው ..." የሚባል ነገር አይኖርም ነበር።
ከዚህ በታች የምታዩት ወደ ሱዳን የተሰደዱ የመተማ ነዋሪዎችንና በአምባ ጊዮርጊስ በጥይት የተመቱ ሕጻናትን ነው። ቁም ነገሩ ዘራቸው አይደለም። የሰው ልጆች ናቸው። ኢትዮጵያዉይን ናቸው። በኢትዮጵያ ምድር ኢትዮጵያውያን ላይ እንደዚህ አይነት ነገር መኖር አልነበረበትም።
በአቶ ሃይለማሪያም በኩል ሕወሃት በአማራው ክልል ላይ ያወጀው ጦርነት ዉጤት ነው።

No comments: