Tuesday, September 6, 2016

አምባሳደር ሳማንታ ፓወር የኢትዮጵያን መንግስት ተችተዋል፣ ከአዲስ አበባ ተመልሰዋል

Amb. Samantha Power, FILE
በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ሳማንታ ፓወር ለአጭር የስራ ጉብኝት ትናንት በአዲስ አበባ ቆይታ ቢያደርጉም በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ ጉዳይ ላይ ከሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ሳይነጋገሩ መመለሳቸውን ምንጮች ገለጹ ፡፡
አምባሳደር ፓወር ወደ አዲስ አበባ የመጡት በደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ግጭት ላይ ከአፍሪካ ህብረት እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ለመምከር ነበር፡፡ የደቡብ ሱዳን ቀውስን ለመፍታት በጸጥታው ምክር ቤት አማካኝነት በተዋቀረው ልዑክ አባል የሆኑት ፓወር ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን ትላንት በጽህፈት ቤታቸው አግኘተዋቸው ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዑካኑን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ሊቀመንበርነቷ የደቡብ ሱዳንን ችግር ለመፍታት ያደረገችውን አስተዋጽኦ አብራርተዋል፡፡ በሶማሊያ አለ ያሉትን ሰላም እና መረጋጋት እንደዚሁም በሀገሪቱ ብሔራዊ ጦር ለመመስረት ስለሚደረገው ጥረት ገለጻ ማድረጋቸውን የመንግስት ብዙሃን መገናኛዘግበዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ላይ ከረር ያለ አስተያየታቸውን የሰጡት አምባሳደር ፓወር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አሊያም ከሌሎች የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር የጎንዮሽ ውይይት ይኖራቸዋል ተብሎ ቢጠበቅም ዲፕሎማቷ ማንንም ሳያነጋግሩ ትላንት ምሽቱን አዲስ አበባን መልቀቃቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡
ለጸጥታው ምክር ቤት ልዑክ ሽፋን የሰጡት የመንግስት ብዙሃን መገናኛዎች የአምባሳደር ፓወርን በስብሰባው መገኘት ሳይጠቅሱ አልፈዋል፡፡ አምባሳደሯም በኦፊሲሊያዊ ትዊተር ገጻቸው በአዲስ አበባ ከአፍሪካ ህብረት ሰዎች ጋር መገናኘታቸውን በፎቶ አስደግፈው የገለጹ ቢሆንም ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጋር መገናኘታቸውን ሳይጠቅሱት ቀርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጉዳይ ክፉኛ ያሳሰባቸው የሚመስሉት አምባሳደር ፓወር ወደ አዲስ አበባ ከመጓዛቸው አንድ ቀን አስቀድሞ በደቡብ ሱዳን ጁባ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ በሀገሪቱ ውስጥ እየተካሄዱ ስላሉ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ሲጠየቁ ጠንከር ያሉ ቃላት ተጠቅመው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ አሁን ያለው ሁኔታበጣሙኑ አሳሳቢሲሉ የጠሩት አምባሳደር ፓወር ሀገራቸው የኢትዮጵያ መንግስት ሁኔታዎችን እንዲያሻሽል ጥሪ ማቅረቧን ይናገራሉ፡፡ ለፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ቅርብ ናቸው የሚባሉት እና በአንድ ወቅት ጋዜጠኛ የነበሩት አምባሳደር ፓወር በሰብዓዊ መብት እና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቶች ላይ ጠንካራ አቋሞችን በማንጸባረቅ ይታወቃሉ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ህዝቡ የመቃወም መብቱን በሰላማዊ መንገድ እንዲያካሂድ፣ በነጻነት መሰብሰብን እና ሀሳብን በነጻ መግለጽን እንዲፈቅድ ጥሪ አቅርበናልበማለት የመንግስታቸውን ጥረት የገለጹት አምባሳደሯበተቃዋሚዎች ላይ የሚወሰዱ ያልተመጣጠኑ የኃይል እርምጃዎች ላይ ያለንን ጥልቅ ቅሬታ አንስተናል ሲሉ አሜሪካ የመንግስትን የተቃውሞ አያያዝ እንዴት እንደምትመዝነው በዚያው ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡
መንግስታቸው በተቃውሞዎቹ ላይ ለጠፋው ህይወት ተጠያቂነት ሊኖር እንደሚገባ እንደሚያምኑ ለጋዜጠኞች የተናገሩት አምባሳደሯ ግልጽ እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ ጥሪ ማቅረቡንም ገልጸዋል፡፡ አሜሪካ በወቅቱ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ ላይ በዲፕሎማት ደረጃ ጠንከር ያለ አቋሟን ስትገልጽ የመጀመሪያው አይደለም፡፡
ባለፈው ሳምንት የስራ ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው የተመለሱት አምባሳደር ፓትርሺያ ሀስላክ በመሰናበቻ ንግግራቸው ከአምባሳደር ፓወር ጋር የሚመሳሰል አቋማቸውን አስተጋብተዋል፡፡እንድታውቁት የምፈልገው ነገር መልዕክታችን ግልጽ መሆኑን ነውህግን ያልተከተለ እስር እና ጥቃት ሊቆም ይገባልሲሉ መንግስት እየወሰደ ባለው እርምጃ አሜሪካ ደስተኛ እንዳልሆነች ጠቆም አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ እንድታድግና ስኬታማ እንድትሆን የሚፈልግ ሁሉ መረዳት ያለበት ኢትዮጵያ ጠንካራ የምትሆነው የሁሉም ድምጾች ሲሰሙባት እና መንግስት ለሁሉም ተጠያቂ ሲሆን ነውሲሉም ተናግረዋል፡፡
የኦባማ አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ቶም ማልኖውስኪ ከሁለት ሳምንት በፊት ከሁለቱ ዲፕሎማቶች ጋር የሚስማማ ይዘት ያለው አስተያየት በኦል አፍሪካ ድረ-ገጽ ላይ አውጥተው ነበር፡፡ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ምክትል ሚኒስትር የሆኑት ማልኖውስኪ በቅርቡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች እየተካሄዱ ያሉ ተቃውሞችንፈታኝ ተግዳሮቶችሲሉ ጠርተዋቸው ነበር፡፡
እነዚህ ተቃውሞዎች ኢትዮጵያውያን በሕገ-መንግስቱ በሰፈረው መሰረት ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ የሚሰጥና የፖለቲካ ብዘሃነትን የሚያሰፍን መንግስት እንዲኖር መፈለጋቸውን የሚያመለክቱ ናቸውሲሉም ሁሉን ነገር በራሴ እፈታለሁ ከሚለው መንግስት የተቃረነ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
የደህንነት ኃይሎች ከመጠን ያለፈ ኃይል በመጠቀም ኢትዮጵያውያን በሰለማዊ መንገድ እንዳይሰበሰቡ መከልከል፣ በርካቶችን መግደልና ማቁሰል እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ማሰራቸውን ቀጥለዋልሲሉ በጽሁፋቸው ያሰፈሩት ማልኖውስኪበሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተቃውሞ ሰልፎች ላይ ተገኝተዋል በሚል መሰረተ ቢስ ክስ በእስር እንደሚገኙ፣ አብዛኛዎቹም ለሕግ ያልቀረቡ፣ የሕግ አማካሪ የተከለከሉ ወይም በአግባቡ የወንጀል ክስ ያልተመሰረተባቸው እንደሆኑ እናምናለንማለታቸው ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ለተቃውሞቹ በሚሰጠው ምላሽ እየተከተለ የሚገኘውራስን የመጻረር ስልትእንደሆነም አስምረውበታል፡፡
እነዚህ ጠንካራ አስተያየቶች እና አቋሞችአሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የአቋም ለውጥ እንዳደረገች ማመላከቻዎች ናቸው?” የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ በዋሽንግተን በሚገኘውሴንተር ፎር ስትራቴጂክ ኤንድ ኤንተርናሽናል ስተዲስየአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ሪቻርድ ዶውኒ በኢትዮጵያ ላይ ከአሜሪካም ጭምርእውነተኛ ጫናእንደሚመጣ ተስፋ ያደረጋሉ፡፡ ነገር ግን ጫናው አሁኑኑ ይከሰታል በሚልትንፋሻቸውን ሰብስበውእንደማይጠብቁ ይናገራሉ፡፡
የአሜሪካ መንግስት ስለ ኢትዮጵያ በአንድ ድምጽ አይናገርምይላሉ ምክትል ዳይሬክተሩ ለኢንስቲትዩት ኦፍ ሲኪዩሪቲ ስተዲስ በሰጡት አስተያየት፡፡ የቶም ማልኖውስኪ ቢሮ በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ ጫና እንዲደረግ ሲጎተጉት እንደ .ኤስ. ኤይድ ያሉ ሌሎች የአሜሪካ መንግስት ተቋማት ግንዝምታን በመምረጥ ላይ ከፍ ያለ ፍላጎት አላቸውይላሉ፡፡
ይህም በኢትዮጵያ ለልማት የሚያፈሱትን ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ለመጠበቅ ያለመ ነውሲሉ ያብራራሉ፡፡ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ኢትዮጵያ እንደ ሶማሊያ እና ሁለቱ ሱዳኖች ባሉ ሀገራት የአከባቢያውን ጸጥታ ለማስጠበቅ ለምትጫወተው ሚና ቦታ ይሰጣል ባይ ናቸው፡፡
በውስጥ ያሉ እንደዚህ አይነት የአመለካከት ልዩነቶች የሚነግሩን አሜሪካ አሁን ያለው ሁኔታ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየተባባሰ ካልመጣ በስተቀር በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ የመሆን ዕድሏ የመነመነ መሆኑን ነውይላሉ ሪቻርድ ዶውኒ፡፡

ዋዜማ ራዲዮ


No comments: