Thursday, September 1, 2016

ዘመኑ የኛ ነው፣ የነርሱ ዘመን አልፏል - ( የሚሊዮኖች ድምጽ)



ለስሙ ሕገ መንግስት አለን ይባላል። ሆኖም ሕግ መንግስቱ ወረቀት ብቻ ነው። ገዢዎች፣ በጠራራ ጸሐይ በተግባር ሕገ መንግስቱን ቀዳደው ጥለዉታል። ዳኞች ሕግን አጣቅሰው ሳይሆን የሚፈርዱት፣ ከደህንነት /ቤት የተሰጣቸውን መመሪያ ነው የሚያነቡት። ዜጎች ሕግ መንግስቱ የሚፈቅድላቸውን የመጻፍ፣ የመናገር የመደራጀት የሃይማኖት ነጻነታቸውን በመጠቀማቸው ሽብርተኞች እየተባሉ በገፍ እየታሰሩ ነው። ዜጎችን በወህኒ ቤቶች አሰቃቂ ድብደባና ቶርቸር ይፈጸምባቸዋል።
አዎን ለነጻነትና ለፍትህ ብዙ ወገኖቻችን ትልቅ ዋጋ እየከፈሉ ነው። ሆኖም በጥቂቶች መስዋትነት ብቻ ለዉጥ አይመጣም። ትግል የሁላችንም አስተዋጾን ይጠይቃል። ትግል የወደቁትን ማንሳት፣ የተበተኑትን መሰብሰብ፣ የተጎዱት መርዳት፣ የታሰሩትን ማሰብና መደገፉን ይጠይቃል። ትግል ቅብብሎሽ ነው። አንዱ ሲደክምና ሲታሰር ሌላው ከተዘናጋና ተስፋ ከቆረጠ፣ ዉጤት አያመጣም። ሆኖም እንደ ዱላ ቅብብሎሽ፣ አንዲ ሲታሰር አንዱ ሲዝል ሌላው ዱላዉን ተቀብሎ የሚቀጥል ከሆነ፣ ያኔ የአምባገነኖች ፍጻሜ ነው የሚሆነው።
እነ ብርቱካን ሚደቅሳ ሲታስሩ፣ እነ እስክንደር ነጋ እነ አንዱዋለም፣ እነ ኦልባና ለሌሳ፣ እነ አንድዱዋለም አራጌ ተነሱ። እነ አንዱዋለም ሲታሰሩ እነ አብርሃ ደስታ፣ እነ ሃብታሙ አያሌው፣ እነ ተመስገን ደሳለኝ፣ እነ ዘመነ ምህረት፣ እነ ዞን ዘጠኞች ተነሱ። እነ ሃብታሙ፣ እነ የሺዋስ እነ ዘመነ ምህረት ሲታሰሩ፣ ሌሎች ተነሱ። በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ እና በአማራው ክልል በተነሳው ተቃዉሞ በሺሆች የሚቆጠሩ ወደ ወህኒ ወየወረዱ ነው። ዮናትን ተስፋዬ፣ ጌታቸው ሽፈራው፣ በቀለ ገርባ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ መርቱ ጉቱ፣ ዘሩሁን ገሰሰ ..እያልን ቆጥረን ልኝቸርሳቸው አንችልም።
ህወሃት የሕዝብ ጥያቄ ከማክበር ይልቅ ማሰር አባዜው ሆኗል። ሆኖም ግን ዜጎንች በማሰር አገዛዙ ፋታ አላገኘም። የለዉጥ ጥያቄም አልተዳፈነም።
ሚሊዮኖች ነን። ሕወሃቶች ሚሊዮኖችን ሊያስሩ አይችሉም። እኛ ከተነቃነቅን አገዛዙ የበሰበሰ በሕዝብ በጣም የተጠላ፣ በስለላ መረብና በአሜሪካኖችን ቻይናዎች ድጋፍ ላይ ብቻ የተመሰረተ በመሆኑ፣ እፍ ተብሎ በቀላሉ የሚወድቅ አገዛዝ ነው። የስርዓቱ ጥንካሬ እኛን መበታተኑና እና ተስፋ ማስቆረጡ ነው።
ህዝብ በድፍን ጎንደር እና ድፍን ጎጃም፣ በወለጋ፣ በምሀራብ ሸዋ፣ በምእራብ አርሲ፣ በሃረረጌና በባሌ ድምጹን እያሰማ ነው። ተቃዉሞን በነቂስ ወጥቶ በአገዛዙ ላይ እያቀረበ ነው። ኢትዮጵያዉይን በአጋዚ ጦር ጭካኔያዊ እርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕይወታቸው እየተቀጠፈ ነው።
በተቀረው የኢትዮጵያ ግዛት ያለን ሁሉ የምንነሳበት ጊዜ አሁን ነው። በአሁኑ ጊዜ በጎንደር እና በጎጃም የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመፈጸም፣ ህወሃቶች ታንኮችንና ከባባድ መሳሪያዎችን እያጓጓዙ ነው። በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በጂማ፣ በደሴ፣ በድረዳዋ፣ በአዋሳ፣ በአርባ ምንጭ፣ በደብረ ብርሃን ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች የምንኖር ይሄ በአቶ ሃይለማሪያም ተእዛዝ እየተደረገ ሕዝብን በጅምላ መጨረሽ በአስቸኳይ እንዲቆም ማድረግ እንችላለን። እኛ እያለን ወገኖቻችንን ሲያርዱ ዝም ብለን ማየት የለብንም። ልናስቆማቸው ያስፈልጋል።
እነርሱ ጥቂቶች ናቸው። እኛ ሚሊዮኖች ነን። እነርሱ በጥላቻና በክፋት የተሞሉ ናቸው። እኛ ፍቅርና ምህረትን እንሰብካለን። እነርሱ በዘረኝነት የተለከፉ ናቸው። እኛ ሁሉንም በስብእናዉና በኢትዮጵያዊነቱ እናሰባስባለን። እንነሳ። እንቀሳቀስ። እግዚአብሄር የሰጠንን አገራችንን ከጨለማ ነጻ እናውጣ። ከሚሊዮኖች አንዱ እንሁን !!!!


No comments: