Wednesday, September 21, 2016

ኢህአዴግ በእርግጥ መለወጥ ይቻለዋልን?

EPRDF logo
ኢህአዴግህዝባዊ አመጽ ከተነሳበት ወዲህ ራሱን ጥፋተኛ በማድረግ እና የተስፋ ቃል በመስጠት ተጠምዶ ከርሟል፡፡ በቅርቡ የገዥው ግንባር ነባር አመራሮች ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ውይይት የሚሰራ፣ ብቃት ያለው ሰው ከየትም ይምጣ በሚንስትርነት እንሾማለን የሚል ሃሳብ ተነስቷል፡፡ ባለስልጣናቱ አፍታተው ባይናገሩትም ሃሳቡ ግን ኢህአዴግ እስካሁን ለሹመት ሲጠቀምበት የነበረውን የፓርቲ ታማኝነት መመዘኛ ወደጎን በመግፋት ችሎታን እና ብቃትን ለመጠቀም መታሰቡን ጠቁሟል፡፡ ይህ ለውጥ ከመስከረም ወር ጀምሮ መሰረታዊ ለውጥ አመጣለሁ በማለት የገባው ቃል ኪዳን አንዱ አካል መሆኑ ነው፡፡ በያዝነው ኣመት የተባለውን ለውጥ ለመተግበር ከሚወሰዱት ርምጃዎች አንዱ የአስፈጻሚውን አካል ስልጣን የሚወስነውን አዋጅ ማሻሻል ሊሆን ይችላል፡፡
ቻላቸው ታደስ ያስናዳው ዘገባ በድምፅ እዚህ ያገኙታል፣ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ

ኢህአዴግ ግን የፖለቲካ ታማኝነትን ወደ ጎን ገሸሽ ለማድረግ ግን በርካታ እንቅፋቶች አሉበት፡፡ አንደኛው እንቅፋት ድርጅቱ የሚመራበት ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ ነው፡፡ በዴምከራሲያዊ ማዕከላዊነት የሃሳብ እና ውሳኔ ከላይ ወደታች እንጂ በተቃራኒው የማይፈስበት አሰራር ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ውይይት እስከተወሰነ ደረጃ ቢኖርም እንኳ የመጨረሻው የሚጸናው ውሳኔ የበላይ አመራር ውሳኔ ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ ብሎ ነገር የለም፡፡ አንዱ አባል ድርጅት ሌላኛውን ሊተችም አይችልም፡፡ በዚህ መርህ አሁን ኢህአዴግ የሚለው ዴሞክራሲያዊ የሃሳብ መንሸራሸር ሊኖር አይችልም፡፡ ከላይ እስከ ታች እንታደሳን፤ የታችኛው ካድሬ የበላይ አመራሩን የሚገመግምበት አሰራር እንዘረጋለን የሚባለው ሁሉ አስቸጋሪ የሚሆነው በዚሁ መርህ ሳቢያ ነው፡፡
በመሰረቱ ላንድ ሊታደስ የሚችለው በአሮጌው እና አዲሱ ትውልድ አመራር መካከል የሃሳብ ትግል ሲቀጣጠል ነው፡፡ የመታደሱ ሃሳብ የመጣው ራሱ ጭምር እንደበሰበሰ ካመነው የላይኛው አመራር ነው፡፡ ለውጥ የሚባለው ነገር አሁንም ከፍተኛው አመራር ለራሱ ስልጣን ለማራዘም በሚያመቸው መንገድ በማንኪያ መጥኖ ከሚሰጠው መድሃኒት ተለይቶ አይታይም፡፡ ውስጣዊ መታደሱ ተሳክቶ የማያውቀው በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ ሳቢያ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ኢህአዴግ መርሁን ይለቃል ተብሎ ስለማይታሰብ ውስጣዊ ህዳሴ ወደፊትም ይሳካል ብሎ መጠበቅ አዳጋች ይሆናል፡፡
ለውጥ አመጣለሁ የሚለው የላይኛው አመራር ራሱ ብቃት አለው ወይ? የሚለው ጥያቄም አልተመለሰም፡፡ ማን ማንን በብቃት ገምግሞ መስፈርት አውጥቶ በብቃት ሊገመግም ይችላል? ቢባል መልስ የለም፡፡ በተቃራኒው ነባሩ አመራር ብቃት ያላቸው አመራሮችን ባላፈራበት ሁኔታ ለግዙፉ የሀገሪቱ ችግሮች የመጨረሻ መፍትሄ አፈላላጊ እና ለውስብስቡ ቢሮክራሲ የብቃት መስፈርቶች አውጭ ማድረጉን እያየን ነው፡፡ መንግስት እና ፓርቲ አንድ በሆኑበት ሀገር የፓርቲ ሰዎች የመንግስት ሹሞችን ወይም የመንግስት ሹሞች የፓርቲ ፖለቲከኞችን ሊተቹ የሚችልበት ዕድል ተዘግቷል፡፡
ሌላኛው ችግር ተንሰራፍቶ የቆየው ከፖለቲካ ስልጣን የሚመነጨው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ነው፡፡ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት ከመንግስታዊ ስልጣን ከሚገኘው ጥቅማጥቅም ተጋሪ ሆነው ቆይተዋል፡፡ በተለይ 1997 . ወዲህ መንግስታዊ እና የፓርቲ መዋቅሩ በጣም በመለጠጡ በርካቶች ተሰግስገዋል፡፡ የመንግስት መዋቅር ያለቅጥ ተንዛዝቷል፡፡ የግሉን ዘርፍ ውጦታል፡፡ ገዥው ድርጅት አባላቱን እና የተመዘገቡ ደጋፊዎቹን በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፡፡ 1997 ምርጫ በኋላ እንኳ የአዲስ አበባ ቀበሌ መዋቅር እጅጉን በመለጠጡ 300 በላይ የመንግስት ተቀጣሪዎችን እንዲያቅፍ ተደርጓል፡፡ የእነዚህን የስራ ዕድል እና ስልጣን ፍላጎት ለማርካት በግዙፉ መዋቅር ሰግስጎ የጥቅም ተጋር አድርጓቸዋል፡፡
አቶ አባይ ፀሃዬም ኢህአዴግነት የስልጣን መቆናጠጫ ሆኗል፤ ብቃት የጎደለውን ሰው መሾምን፣ ስልጣን ርስት መሆኑን፣ ችሎታ የሌላቸው መኖራቸው እየታወቀ ተጠያቂነት ሳይኖርባቸው ዝም ሲባሉ ኖረዋል ሲለ ተደምጠዋል፡፡ ለምን ብለን ብንጠይቅ ግን ዞሮ ዞሮ ከመሰረታዊው መንግስታዊ እና ፓርቲ መዋቅር ጋር ይያያዛል፡፡ መንግስታዊ መዋቅሩን ከስረ መሰረቱ ለማሻሻል ደሞ መጀመሪያ የገዥውን ፓርቲ አወቃቀር እና ፖሊሲ መቀየር ይጠይቃል፡፡ በተለይ ቃል በተገባው መሰረት ከገዥው ድርጅትው ውጭ ያሉ ባለሙያዎችን ማስጠጋት የሚቻለው ጠንካራ ተቋማዊ አሰራር ሲኖር ነው፡፡ ኢህአዴግ ግን አሁንም የአራት ብሄር-ተኮር ድርጅቶች ግንባር እንጂ ውህድ ፓርቲ አይደለም፡፡ ውህድ ፓርቲ ቢሆን ኖሮ ግንባር ቀደም መመዘኛውን ብቃት እና ችሎታን ለማድረግ ባልተቸገረ ነበር፡፡ በግንባርነቱ ግን የአራቱን አባል ድርጅቶች አመራር አባላት በፖለቲካዊ ስልጣን ድልድል ከማርካት ውጭ ሌላ አማራጭ ያለው አይመስልም፡፡
በአቶ መለስ ጊዜ በነበረው የመጨረሻው ካቢኔ እንኳ ከገዥው ድርጅት በብቃታቸው የተሾሙት አቶ መኮንን ማንያዘዋል ብቻ ነበሩ፡፡ በወቅቱ አቶ መለስ ለፓርላማው የካቢኔ ሹመታቸውን ሲያቀርቡ የአቶ መኮንንን የፓርቲ አባል ሳይሆኑ መሾም እንደ ስኬት ሲናገሩት እንደነበር ይታወሳል፡፡
ኢህአዴግ መጠነ-ሰፊ ህዝባዊ ቀውስ ከተነሳበት ወዲህ ድንጉጥ ድርጅት ሆነዋል፡፡ ባሁኑ ጊዜ ብቃት የሌላቸውን ከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች እያነሳ ችሎታ ባላቸው ሰዎች ልተካ ቢል የሚገለሉ አባላቱ የስልጣን መሰረቴን ይሸረሽሩብኛል ብሎ ይሰጋል፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ ግንባር እንደመሆኑ መጠን ውስጣዊ የመሸርሸር አደጋ ይደርስብኛል የሚለው ስጋቱ የቆየ ስጋቱ ነው፡፡ ሚንስቴርነት በይገባኛል የሚገኝ አይደለም ያሉት አቶ በረከት ስምዖን የፓርቲ አመራር የሖነ ሰው የመንገስት ስልጣን መያዙ መሰበር ያለበት ሀገር አጥፊ አካሄድ ነው ብለዋል፡፡ ስለ ከፍተኛው አመራር መተካካት መጓተት ሲጠየቁ ግን ሀገሪቱ የምትፈልገው የበቃ አመራር ሳይሆን እየተማረ የሚሄድ አመራር ነው የምትፈልገው በማለት ቀደም ብለው የተናገሩትን ማፍረሳቸው ድርጅቱ ለመሰረታዊ ለውጥ ከልቡ እንዳልቆመ አመላክቷል፡፡ አቶ በረከት ቀጠል አድርገውም ውጤታማነታቸው አጥጋቢ ያልሆኑ ግን ደሞ መሰረታዊ የስነ ምግባር ችግር ለሌለባቸው በልዩ ትኩረት ድጋፍ እንሰጣለን ማለታቸው ያው የተለመደው አቅም ግንባታ ፖሊሲ እንደሚቀጥል ያመላከተ ነው፡፡
ህገ መንግስቱ ጠንካራ ጠቅላይ ሚንስትር ቢፈቅድም ከአቶ መለስ ህልፈት ወዲህ ስልጣኑ በተግባር ላልቶ ይታያል፡፡ አንድ የካቢኒ አባል የሚሰራው ስህተት መንግስት በጠቅላላው የጋራ ሃላፊነት እና ተጠያቂነት እንዲኖርበት ማድረግ ሲገባው የተናጥል ችግር አድርጎ የማየት አዝማሚያ ተንሰራፍቷል፡፡ ሚንስትሮች ከስልጣናቸው ሲነሱ ምክንያቱ የስነ ምግባር ጉድለት ወይም አቅም ማነስ ስለመሆኑ ተገልጾ አያውቅም፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ የከተማ ልማት ሚንስትሩ መኩሪያ ኃይሌ በድንገት ከስልጣናቸው ተነስተው የጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪ ስለተደረጉበት ምክንያት አንዳችም ግልጽ ማብራሪያ አልተሰጠም፡፡
ለዚህ ዓይነቱ አሰራር ሁለት ምክንያቶችን ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ ባንድ በኩል መንግስት ይፋዊ ምክንያት በመስጠት ባለስልጣኖቹ የሚወክሏቸውን የኢህአዴግ ብሄር-ተኮር አባል ድርጅቶች ማስቀየም አይፈለግም፡፡ በሌላ በኩል ደሞ የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ በባህሪው ሚስጢራዊ እና የጋራ ሃላፊነት እና ተጠያቂነት የሌለበት መሆኑ ይፋዊ ምክንያቱን ለመግለጽ እንቅፋት ፈጥሮበታል፡፡
ላለፉት ጥቂት ዓመታት የክላስተር አስተባባሪ ሦስት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሮች ተሸመውም መዋቅሩን ከማንዛዛት እና የአባል ፓርቲዎች ስልጣን ድልድል ከመሆን ውጭ ያመጣው አንዳችም አወንታዊ ለውጥ ያለ አይመስልም፡፡ ላለፉት ጥቂት ዓመታት ደሞ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከደርዘን በላይ በሚሆኑ አማካሪ ሚንስትሮች ተከበዋል፡፡ ከመጀመሪያዎቹ አራት የፖሊሲ አማካሪዎች ሌላ የአማካሪዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሰራር ግን የካቢኔውን ስልጣን በቀጥታ የሚሸረሽር መሆኑን ታዛቢዎች ይገልጻሉ፡፡ እንዲያውም አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች የአማካሪዎችን ስብስብ የጓዳ ካቢኔ (kitchen cabinet) ይሉታል፡፡ አሁን ቃል እንደተገባው ከገዥው ግንባር ውጭ ያሉ ሙያተኞች ተሸመው የቴክኖክራት ካቢኔ ቢቋቋም እንኳ የይስሙላ ከመሆን አያልፍም፡፡ ምክንያቱም የጓዳ ካቢኔው ከኋላ ሆኖ ለመዘወር የተዘጋጀ ነውና፡፡
የፓርቲ ስልጣን በቀጥታ መንግስታዊ ስልጣን ሲያስገኝ ስለኖረ አሁን የሹመት ቦታቸውን የሚያጡ አባላቱ ለፓርቲው ያላቸው ተዓማኒነት እና ቀርጠኝነት ይቀንሳል፡፡ በርግጥ ገዥው ፓርቲ የበርካታ ኢንዶውመንቶች ባለቤት በመሆኑ ግዙፍ ሙዓለ ንዋይ ያንቀሳቅሳል፡፡ ሆኖም ኢንዶውመንቶቹ በዋናነት በህወሃት ባለቤትነት ስለተያዙ በአባል ድርጅቶቹ መካከል የተመጣጠን የሃብት ክፍፍል የለም፡፡ ስለዚህ ከመንግስት ስልጣን የሚገለሉ ከፍተኛ የፓርቲው አመራር አባላት ከየድርጅቶቻቸው የሚያገኙት ጠቀም ያለ ማካካሻ ላይኖር ይችላል፡፡ ምናልባት በብቃት ማነስ ሲነሱ የኖሩ ሰዎችም ተመልሰው የጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪ የሚሆኑት የዚሁ ስጋት ውጤት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ግን በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የስልጣን እና ሃብት ክፍፍል ጥያቄ በመጠኑ እየተነሳ ሲወድቅ ኖሯል፡፡ ሆኖም የትኛውም አባል ድርጅት በይፋ በግንባሩ ውስጥ ዋነኛ አጀንዳው ሳያደርገው በአማራ ክልል ህዝባዊ አመጽ ጥያቄው መወያያ መሆን ጀምሯል፡፡ ስለዚህ ይህ ጥያቄ ወደ ግንባሩ በደንብ እየተጋባ ባለበት ጊዜ የሹመት መመዘኛውን መቀየር ለህወሃት አዋጭ አይሆንለትም፡፡
ለውጡ ለይስሙላ ፌደራል መንግስቱ ላይ በመጠኑ ሊተገበር ይችል ይሆናል፡፡ የገዥው መንግስት እና ግንባር ማዕከላዊ ስልጣን እየላላ መሆኑ በሚነገርበት ወቅት ግን ለውጡን በተመሳሳይ በክልሎች መሞከር አዳጋች መሆኑ አይቀርም፡፡ የየአባል ድርጅቶቹ ልሂቃን የፌደራል መንግስት ስልጣን ባያገኙ እንኳ ብቸኛው ስልጣን እና ሃብት ምንጫቸው የክልል መንግስታዊ መዋቅር መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡
ነባር አመራሮቹ አጽንዖት ሰጥተው የተናገሩት ስለ ገዥው ድርጅት መታደስ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ለውጦች መታሰባቸው ራሱ ይፋ የተደረገው በፓርቲው ነባር አመራሮች እንጂ በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አለመሆኑ የሚናገረው ነገር አለ፡፡ ድርጅቱ የነደፋቸው የልማት እና ዴሞክራሲ ሰነዶች ግን አሁንም ጥያቄ አልተነሳባቸውም፡፡ የህገ መንግስታዊ ተቋማትን ገለልተኝነት ስለማረጋገጥ፣ ስለ መገናኛ ብዙሃን እና ፍርድ ቤቶች ነጻነት፣ ስለ ጠንካራ የፓርላማ ቁጥጥር እንዲሁም ስለ ነጻ ሲቪል ማህበራት አደረጃጀት አልተነሳም፡፡
ዋነኛ ችግር ተደርጎ የቀረበው የላይኛው አመራር ፖሊሰዎችን ለመፈጸም አቅም የሌለው መሆኑ ብቻ ነው፡፡ በርግጥ በገደምዳሜ ግን ህዝቡንም እናሳትፋለን ብለዋል፡፡ ለህዝባዊ ተሳትፎው ሁነኛ መድረኮች አድርገው የጠቀሷቸው ግን እንደ ሴቶች እና ወጣት ማህበራት ያሉ ህዝባዊ አደረጃጀቶችን፣ መገናኛ ብዙሃንን እና በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶችን ነው፡፡ እነዚህ አካላት ግን በገዥው ግንባር ሙሉ ቁጥጥር ስር የወደቁ መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በተደጋጋሚ ህዝቡ ቅሬታ ሲያነሳ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ሊያደርግባቸው እንዳልቻለ ለበርካታ ዓመታት ታይቷል፡፡ የክልሉ ምክር ቤቶችም ባለፈው ዓመት በተደረገው ምርጫ መቶ በመቶ በገዥው ድርጅት በተያዙበት ሁኔታ እንደምን ዴሞክራሲያዊ የህዝብ ተሳትፎ መድረኮች እንደሚሆኑ ግልጽ አይደለም፡፡

ዋዜማ ራዲዮ

No comments: