Sunday, October 2, 2016

ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ የሐዘን መግለጫ!!!

የንፁሃን ዜጎችን ሕይወት በመቅጠፍ ወንጀል ተጠይቆ የማያውቀው ስርዓት አሁንም ንፁሃንን መግደል ዝንብን የመግደል ያህል እየቆጠረው በአረመኔያዊ ግድያዉ ቀጥሎበታል፡፡ ባለፉት ቅርብ ጊዚያት በተለያዩ የሐገራችን ክፍሎች በተፈፀሙ ጭፍጨፋዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ሐዘን ሳይበርድ ዛሬ መስከረም 22 ቀን 2009 . በኦሮም ሕዝብ በድመቀት የሚከበረውን አመታዊ የኢሬቻ በዓል ለማክበር በደብረዘይት/ቢሾፍቱ በተገኙ በብዙ ሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የገዥው ቡድን ስርዓት ጠባቂዎች በወሰዱት አረመኔያዊ ጭፍጨፋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት መቀጠፉን ከበዓሉ ታዳሚዎች በተገኘ መረጃ ታውቋል፡፡ የዜጎችን የእምነትና የባሕል ነፃነት አስከብራለሁ በማለት የሚታበየውና ይልቁንም ያለፉ ስርዓቶችን የዜጎችን የእምነት ነፃነት በመንፈጋቸው የሚኮንን ስርዓት ዛሬ ዜጎች የሚያብሯቸውን በዓላት ለገዥው ቡድን የፖለቲካ ፍጆታ ካልጠቀሙ በስተቀር ዜጎች እምነታቸውንና ባህላቸውን እንዲያከብሩ እንደማይፈቅድ የዛሬው አረመኔያዊ ድርጊቱ ጉልህ ማስረጃ ነው፡፡ 
ጨቋኝ ስርዓት አስካለ ድረስ የተጨቋኞች ጥያቄ አይቆምም፡፡ የጭቁኖችን ጥያቄ ለዕለቱ በኃይል ማፈን ይቻል ይሆናል፡፡ ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል ግን ከዛሬዎቹ ገዥዎቻችን የበለጠ ምስክር ሊሆን የሚችል አይገኝም ነበር፡፡ 
ሰማያዊ ፓርቲ በዜጎች ላይ በደረሰው የሞትና የአካል ጉዳት ጥልቅ ሃዘን የተሰማው መሆኑን እየገለፀ ለቤተሰቦቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ መፅናነትን ይመኛል፡፡ የንፁሃንን ደም ያፈሰሱም ለፍርድ እንዲቀርቡ እየጠየቀ ዛሬ በመላ ሃገራችን ያጠላው የሞት ጥላና የአረመኔዎች የግፍ እርምጃ ማቆሚያ ያገኝ ዘንድ ስርዓቱ መለወጥ ስላለበት ዜጎች ሰላማዊ ትግላቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ፓርቲው ጥሪውን ያቀርባል፡፡

No comments: