Sunday, October 9, 2016

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ህዝባዊ አመፁን ያቆመዋል?

PM Hailemariam Desalegn
ቅዳሜ ዕለት የኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ካቢኔ ተሰብስቦ በመላ ሀገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡ በሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ ያሁኑ የመጀመሪያ መሆኑ ነው፡፡ በተለይ አዋጁ ጸንቶ የሚቆየው ለስድስት ወራት መሆኑ ደሞ አስደንጋጭ ነው፡፡ መንግስት ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት አድርጎ የጠቀሰው በኦሮሚያ ክልል ፀጥታ አሽቆልቁሎ፣ የዜጎች ሕይወት በመጥፋቱ፣ እንደ ኦሮሞ ነጻነት ግንባር ያሉ በሽብርተኛነት የተፈረጁ ጸረ ሰላም ሃይሎች ከሀገሪቱ ጠላቶች ጋር በመተባበር የሀገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል እያሴሩ መሆኑን እንዲሁም የውጭ ባለሃብቶች ኩባንያዎች እና የመንግስት መሰረተ ልማቶች መውደማቸውን ነው፡፡
ህገ መንግስቱ በደነገገው መሰረት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ ፓርላማው የተወሰኑ አባላቱን ያቀፈ የአዋጁን ህገ መንግስታዊ አፈጻጸም የሚከታተል ገለልተኛ ቦርድ እንደሚቋቋም ስለደነገገ በመጭዎቹ ቀናት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቦርዱን ያቋቁማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ምናልባትም ጠቅላይ ሚንስትሩ ሰኞ ዕለት ለሚሰበሰበው ፓርላማ አዋጁን እና ዝርዝር አፈጻጸሙን አቅረበው ማጸደቃቸው አይቀርም፡፡ አዋጁን ለማስፈጸምም በጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ስር ልዩ ኮማንድ ፖስት መቋቁሙ ተገልጧል፡፡ ሆኖም ከኢህአዴግ ባህሪ አንጻር ሲታይ ከቦርዱ ይልቅ ዋነኛውን የፈፃሚነት እና ተቆጣጣሪነት ስልጣን ደርቦ የሚይዘው ወታደራዊ ኮማንድ ፖስቱ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡
አሁን በአዋጁ ላይ ሦስት መሰረታዊ ጥቄዎችን ማንሳት ይገባል፡፡ አንደኛው ጥያቄ አዋጁ ምን ዓይነት ፖለቲካዊ እና ህጋዊ አንድምታዎች ይኖሩታል? የሚለው ነው፡፡ ከጠቅላይ ሚንስትሩ መግለጫ መረዳት የሚቻለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በይዘቱ እና በአፈጻጸም ወሰኑ መጠነ-ሰፊ መሆኑን ነው፡፡ በሀገር ውስጥ በቅርቡ በአሮሚያ ክልል የተከሰቱትን ክስተቶች መነሻ ቢያደርግም አዋጁ የታወጀው ግን በመላ ሀገሪቱ ነው፡፡ ሆኖም ኮማንድ ፖስቱ የሀገሪቱን ጸጥታ ሁኔታ እያየ አፈጻጸሙን በተወሰኑ ቦታዎች ሊገድበው እንደሚችል አዋጁ ግልጽ አድርጓል፡፡
አዋጁ በመላ ሀገሪቱ የመሰብሰብ፣ ሃሳብን ያለማንም ጣልቃ ገብነት በነጻነት የመግለጽ እና የፕሬስ መብት፣ ሰላማዊ ሰልፍ እና ተቃውሞ የማድረግ፣ በፊርማ የተሰባሰበ አቤቱታ ወይም ፒቲሽን የማቅረብ፣ ፖለቲካዊ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ትዕይንት ማሳየት፣ ስብሰባ፣ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ የመሳሰሉት በህገ መንግስቱ የተፈቀዱ ዴሞክራሲያዊ እና ፖለቲካዊ መብቶች በጠቅላላው ለስድስት ወራት ሊከለከሉ እንደሚችሉ አዋጁ ደንግጓል፡፡ አዋጁ የመገናኛ ዘዴዎች እንዲዘጉ የማድረግ እና ሁሉም ዜጎች ለአዋጁ ተፈጻሚነት ተባባሪ እንዲሆኑ የማስገደድን ስልጣን ለኮማንድ ፖስቱ ሰጥቷል፡፡ እንደ ሀኔታው እየታየም ባንዳንድ ከተሞች የሰዓት እላፊ ገደብ ሊጣል እንደሚችልም የጠቅላይ አቃቤ ህግ ሃላፊው ዕሁድ ማምሻውን አስታውቀዋል፡፡ ጸጥታ ሃይሎች ሰዎችን በጅምላ በማጎሪያ ጣያዎች ላልተወሰነ ጊዜ የማጎር፣ ፍርድ ቤት ሳያቀርቡ ላልተወሰነ ጊዜ የማሰር፣ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ፍተሻ የማድረግ መብት እና አዋጁን ተላልፈው በሚገኙትም ላይ የሃይል ርምጃ የመውሰድ መብት ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ በተለይ መንግስት አጋጣሚውን በመጠቀም በወልቃይት፣ ኦሮሚያ እና ኮንሶ የሚገኙ ተቃዋሚዎችን እና የህዝብ መብት ተሟጋች ኮሚቴ አባላት ላይ መጠነ-ሰፊ የአፈና ርምጃ ሊወስድ እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡
ኢሰብዓዊ ቅጣት እና አያያዝ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜም ክልክል ቢሆንም የጸጥታ ሃይሉ ርምጃዎች ግን ህገ መንግስቱን ማክበር አለማክበራቸውን የሚከታተለው በገዥው ፓርቲ መቶ በመቶ በተያዘው ፓርላማው ጥላ ስር የሚያቋቋመው ቦርድ ነው፡፡ ከፓርላማው የእስካሁኑ ባህሪ መገንዘብ የሚቻለው ግን በዜጎች ላይ ሲፈጸሙ ለኖሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ስራ አስፈጻሚውን ተጠያቂ አድርጎ ስለማያውቅ አሁንም ከድሮው የከፉ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ላለመፈጸማቸው ምንም ዋስትና የለም፡፡
ከአስተዳደር አንጻር ሲታይ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙ አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ኢህአዴግ መላ ሀገሪቱን በልዩ ወታደራዊ ቀጠናዎች በመከፋፈል ወታደራዊ አመራር ለማስፈን መዘጋጀቱን ያሳያል፡፡ ዝርዝሩ በቀጣዮቹ ቀናት የሚገለጽ ቢሆንም ኮማንድ ፖስቱ በጠቅላይ ሚንስትሩ ጽህፈት ቤት ስር ከደኅንነት፣ ከጠቅላይ አቃቤ ህግ እና ፌደራል ፖሊስ፣ እንዲሁም ከመከላከያ ሰራዊት የሚውጣጣ አንድ ማዕከላዊ አመራር እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡ በመሆኑ በየክልሉ ያሉ መደበኛ የፖሊስ ሃይሎች እና የሲቪል አስተዳደር አካላት የዕለት ተለት እንቅስቃሴ በሙሉ በወታደራዊው ኮማንድ ፖስት ዕዝ ስር ይወድቃሉ ማለት ነው፡፡
ሁለተኛው ጥያቄ ለአዋጁ መውጣት ዋናው ገፊ ምክንያት የሀገር ደህንነት እና ሰላም አደጋ ላይ መውደቁ ነው ወይንስ ፖለቲካዊ ምክንያት አለው? የሚለው ነው፡፡ በአሸባሪነት የተፈረጀው ኦነግ ከግብጽ መንግስት ጋር በተባበር በሀገሪቷ ሰላም፣ ጸጥታ እና ብሄራዊ ደህንነት በተለይም ታላቁን የህዳሴ ግድብ ለማሰናከል ጥምረት መፍጠሩን መንግስት የገለጸው አስቿኳይ ጊዜ አዋጁ ከመታወጁ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ነበር፡፡ ሆኖም ለውንጀላው አሳማኝ ማስረጃ ሳያቀርብ በጥድፊያ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መደንገግ ዋና ምክንያት አድርጎ መትቀሱ መከራከሪያውን ውሽልሽል አድርጎበታል፡፡
በሀገር ውስጥም ቢሆን በብሄረሰቦች ወይም በሃይማኖቶች መካከል የርስበርስ ግጭት ለመከሰቱ አንዳችም ሁነኛ ማስረጃ ቀርቦ አያውቅም፡፡ እስካሁን የሚወጡት ማስረጃዎች የሚያሳዩት የዜጎች ሕይወት በዋናነት የሚጠፋው ጸጥታ ሃይሎች በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ የሃይል ርምጃ በመውሰዳቸው ሳቢያ ነው፡፡ የተደራጁ ጸረ ሰላም ሃይሎች የሚላቸው አካላት ከመደበኛው ጸጥታ ሃይል አቅም በላይ ሆነው መጠነ0ሰፊ ሁከት ለመፍጠራቸው አንዳችም ማስረጃ አቅርቦ አላሳየም፡፡
ይልቁንስ ዋነኛ ምክንያቱ ፖለቲካዊ እንደሆነ መታዘብ አይከብድም፡፡ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች የተቀሰቀሱት ተከታታይ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ሊበርዱ ስላልቻሉ ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር ሁለገብ ድርድር ለማድረግ በሩን ሊከፍት ይችላል የሚል ተስፋ በተጠናከረበት ሰዓት ነው አዋጁ የታወጀው፡፡ ይህም ኢህአዴግ ለገጠሙት ቀውሶች ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት ፍላጎት እንደሌለው በግልጽ ይጠቁማል፡፡ መንግስትም ሁነኛ እና አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት ባለመቻሉ በቀውስ ላይ ቀውስ እየተጨመረ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ከአቅሙ በላይ መሆናቸው እስከማመን ደርሷል፡፡
በርግጥ ህዝባዊ አመጽ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ከተቀጣጠለ ወራት ቢያስቆጥርም መንግስት ግን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የተገፋፋው በአዲስ አበባ ዙሪያ ህዝባዊ አመጾች መነሳታቸውን በገለጸ ማግስት መሆኑ የአሁኑ አዋጅ መውጣት ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች እና የውጭ ሀገራት ኢምባሲዎች ወዳሉባት ዋና ከተማ ተሸጋግሮ ገመናው እንዳይጋለጥበት ስጋት ውስጥ መግባቱን ጠቋሚ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ አሁን መንግስት በአዋጁ ሽፋን ያለ የሌለ ሃይሉን ተጠቅሞ፣ ራሱን መልሶ ለማረጋጋት እና እግሩን መልሶ ለመትከል ሲል ለወራት የሚዘልቅ የመተንፈሻ ጊዜ ለማግኘት መቁረጡ ግልጽ ሆኗል፡፡
ሌላው ጥያቄ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ብቻውን ህዝባዊ ተቃውሞውን ሊያበርደው ይችላል ወይ? የሚለው ነው፡፡ 1997 ምርጫ ዕለት የመሰብሰብ እና ተቃውሞ የማድረግ መብቶችን የሚገድበው ላንድ ወር የዘለቀው ወታደራዊ ኮማንድ ፖስት ቢቋቋምም ብዙም ሳይቆይ አዲስ አበባ ላይ ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ጸጥታ ሃይሎች ከፈቱት ተኩስ ከሁለት መቶ በላይ ንጹሃንን ማለቃቸው ይታወሳል፡፡ ወደፊት የሚታይ ቢሆንም አዋጁ የሚጸናው ለተራዘመ ጊዜ መሆኑ ደሞ በራሱ የአደባባይ ተቃውሞ ቀስቃሽ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ተቃውሞ ከተነሳ ፀጥታ ሃይሎች አዋጁ የሰጣቸውን መብት ተጠቅመው ንጹሃንን በጅምላ ከመግደል ወደኋላ ይላሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ይህ ደሞ ወደ መጠነ-ሰፊ ግጭት ማምራቱ አይቀርም፡፡
መንግስት መከላከያ ሰራዊቱን በከተሞች አሰማርቶ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን መጨፍለቅ የጀመረው ካንድ ወር በፊት በአማራ ክልል የተነሳውን ግጭት ለማስታገስ በሚል ጠቅላይ ሚንስትሩ ጦር ሰራዊቱ የሃይል ርምጃ እንዲወስድ ከማዘዛቸው በፊት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ስለዚህ የአሁኑን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተለየ የሚያደርገው የመከላከያ ሰራዊቱ ተቃውሞን በሃይል ለመጨፍለቅ ህገ መንግስታዊ መብት መጎናጸፉ ብቻ ነው፡፡
ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ያወጀው ለጥቂት ቀናት በመላ ሀገሪቱ የኢንተርኔት አቅርቦትን አቋርጦ ከሰነበተ በኋላ ነው፡፡ በርግጥም ባለፈው ሳምንት የታየው የመንግስት አካሄድ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመደንገግ እየተዘጋጄ መሆኑ ጠቋሚዎች ነበሩ፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታወጀው ኢህአዴግ ከያዝነው ወር ጀምሮ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስፋት፣ ተጠያቂነት ለማስፈን እና ስር ነቀል መዋቅራዊ ማሻሻያ ለማድረግ ቃል በገባ ማግስት መሆኑ መንግስት ከፖለቲካ መፍትሄ ይልቅ የሃይል ጭፍለቃውን አጠናክሮ ለመቀጠል መወሰኑን ግልጽ አድርጓል፡፡
የተባበሩት መንግስታት በበሀገሪቱ የሰው ህይወት የጠፋባቸውን ግጭቶች ለመመርመር ጥያቄ ቢያቀርብም ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም በባህር ዳር፣ ጎንደር እና በቅርቡም በቢሾፍቱ እሬቻ በዓል ላይ የደረሰው እልቂት፣ እንዲሁም በቂሊንጦ እና ጎንደር ወህኒ ቤቶች የሰው ህይወት ያጠፉት ቃጠሎዎች መንስዔ ሳይጣራ አስቸኳይ ጊዜ አውጇል፡፡ አሁን እነዚህ ሁሉ ክስተቶች አዋጁ ጸንቶ በሚቆይበት ጊዜ ተጣርተው ለህዝብ ይፋ የመደረግ ዕድላቸው አነስተኛ ሆኗል፡፡
በህገ መንግስቱ አንቀጽ 93 መሰረት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው የውጭ ወረራ ሲያጋጥም፣ ህግና ስርዓት ተቃውሶ በመደበኛ ጸጥታ ሃይሎች ጸጥታን ማስከበር የማይቻልበት ደረጃ ሲደረስ ወይም ወረርሽን ሲከሰት መሆኑ ተደንግጓል፡፡ ከእነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ አሁን መንግስት ምክንያት አድርጎ የጠቀሰው ህግና ስርዓት ተጓድሎ ከአቅም በላይ መሆኑን ነው፡፡ መንግስት አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ለአራት ወራት የማራዘም ስልጣን በህገ መንግስቱ ተሰጥቶታል፡፡
በጠቅላላው አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሀገሪቱን በማረጋጋት ስር ነቀል ዴሞክራሲያዊ ለውጦች እንዲፈጠሩ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ይልቅ ቀውሱን እንዳያባብሰው ስጋት አለ፡፡

ዋዜማ ራዲዮ

No comments: