Friday, October 14, 2016

ኢቲቪ በፕሮፌሰር ብርሃኑ፣በጀዋር እና ግብፅ ዙርያ በሚሰራው ፕሮፓጋንዳ የሕዝብ መሳቅያ ሆኗል።

f85c5426
ኢቲቪ = ´´ሕወሓት ስልጣን ላይ ካልቆየ ትጠፋላችሁ´´
ሕዝብ=´´ውረዱ እንጂ እንደማንጠፋ ታያላችሁ´´
ኢቲቪ ሰሞኑን አክቲቪስት እና የኦኤምኤን ቴሌቭዥን ጣብያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጀዋርን፣ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን እና የግብፅ መንግስትን የሚወቅስልኝ ያለውን ፕሮፓጋንዳ ተያይዞታል።ጉዳዩ ግን ሕዝብን በእራሱ ዜጎች የማስፈራራት ሙከራ ካልሆነ በቀር በእዚህ ደረጃ ያለ የህዝብ ጥያቄን ማደባበስ አይቻልም።ለመሆኑ ሕወሓት ከመቼ ወዲህ ነው የሀገር ጠበቃ የሆነው? እስኪ ሶስቱን የፕሮፓጋንዳው መነሻ የሆኑትን ተራ በተራ ባጭሩ እንመልከት።
ጀዋር
ጃዋር ገና በልጅነቱ የተናገራቸውን (ሰውነቱም ቀጭን ሆኖ ነው በኢቲቪ የሚታየው) ንግግሮች ኢቲቪ እየመዘዘ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሊያስፈራራበት ይሞክራል።ጀዋር ቀድሞ ያላቸውን አባባሎች በተለያየ ጊዜ ማስተባበያ ሰጥቶበታል።ጀዋር ባለፈው ለሕወሓት የጋበዘው እና ፌስ ቡኩ ላይ የለጠፈውን የአማርኛ እስክስታ ኢቲቪ ለምን ደበቀው? ኢቲቪ በሚለው ደረጃ ጀዋር በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ውስጥ ያልተፈጠረ አስመስሎ ለማቅረብ የሚደረገው ሙከራ ውሸት መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ማወቅ አለበት።የኢትዮጵያ ሕዝብ በመተዳደርያ ማንፌስቶ ላይ ሕዝብን ጠላት ብሎ ከፈረጀ ድርጅት ጋርም 25 ዓመታት ኖሯል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ
ኢቲቪ ፕሮፌሰር ብርሃኑን በፕሮፓጋንዳው ላይ ደጋግሞ የሚያቀርበው ንግግር የወያኔ ንብረት ላይ ስለሚፈፀሙ ጥቃቶች ነው።ፕሮፌሰር ብርሃኑ የወያኔ ንብረት ጥቃት ላይ ተናገሩ እንጂ የትግራይ ንብረት አጥፉ አላሉም።የፕሮፌሰር ብርሃኑን ያህል ከትግራይ ሕብረተሰብ ጋር ተከባብሮ የሚኖር ሰው ለማምጣት መሞከር ሌላው የወያኔ ማጨናበርያ ነው። ይልቁንም ፕሮፌሰርን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደዛ በበረሃው ሰውነቱ ተጎሳቁለው ሲመለከት ግሎባል ሆቴል ትዝ ይለዋል።ይህ ሰው እንዲህ የጠቆረው ለእኔ አይደለምን? የኢትዮጵያ ሕዝብ መበደል የአገሩ ጉዳይ ቢያሳዝነው አይደለምን? እኔስ ኃላፊነቴ ምንድነው? እንዲል አድርጎታል። ስለሆነም ኢቲቪ እዚህም ላይ አልተሳካለትም።
ግብፅን በተመለከተ
ሰሞኑን ኢቲቪ ግብፅን አስመልክቶ የሚያስተላልፈው ፕሮግራም ኃላፊነት የጎደለው ነው።
የፕሮፓጋንዳው ጭብጥ አንድ የቴሌቭዥን ጣብያ ስለ ኦነግ አወራ ነው።ከእዚህ ጋር አስታኮ የአባይ ግድብ ይነሳል።እዚህ ላይ አንድ ማወቅ ያለብን ነገር ከኢትዮጵያ በስተቀር በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ለቁጥር የሚያታክቱ የግል ቴሌቭዥን ጣቢያዎች አሉ።ባለፈው ሳምንት አንድ የኬንያ ተወላጅ ወጣት በሀገሩ ስንት የግል ቴሌቭዥን ጣቢያዎች እንዳሉ ስጠይቀው የመለሰልኝ በጣም ብዙ እንደሆነ እና አላውቅም የሚል ነው።በእርግጥ በኬንያ ያሉት ቴሌቭዥን ጣብያዎች ከቁጥር በላይ ሆነው ሳይሆን ብዛት ያላቸው ቴሌቭዥን ጣብያዎች መኖር ለአፍሪካውያን ብርቅ አለመሆኑን ነው።
ግብፅን ደግሞ በእዚሁ መልክ ማየት ይቻላል።በእዚህ ፅሁፍ አቅራቢ መሰረት በግብፅ ውስጥ 120 በላይ የሳተላይት ተሌቭዥኖች መኖራቸውን ከድረ-ገፅ ላይ ተመልክቷል። ይህ ማለት አንድ ዩንቨርስትም የእራሱ ሳተላይት ቴሌቭዥን የመክፈት መብት ያላቸው የአፍሪካ ሀገሮች ውስጥ ያሉ ቴሌቭዥኖች በማናቸውም ጉዳዮች ላይ ተመልካች ለማግኘት ከመጣር አንፃር ፕሮግራሞች ያቀርባሉ። ኢቲቪ የወሰደው ከእነኝህ ቴሌቭዥኞች አንዱን መዞ ´´ኦነግን እየረዳን ነው፣ አባይ ቆመ መንገዱ ተዘጋ´´ ይለናል።
ይህንን በምሳሌ እንየው ለአቅመ ነፃ ሚድያ አልደረሰም እንጂ እንበል እና ሚሚ ስብሃቱ ቅልጥ ያለ ኬንያን የሚሰድብ ፕሮግራም አቅርባ ስትሳደብ ብትውል እና የኬንያ ቴሌቭዥን የኢትዮጵያ መንግስት እንዲህ እያደረገ ነው ብሎ ሲናገር ይታያችሁ።ጤነኛ መንግስት በመጀመርያ የሚያደርገው በተቅራኒው ሀገር የመደበውን ኢምባሲ ስለቴሌቭዥን ጣቢያው ምንነት ይጠይቃል።በመቀጠል ጉዳዩን ከሀገሩ አምባሳደር ማብራርያ ይጠይቃል።በግብፅ አንፃር ግብፅ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስራቤቷ በኩል ምላሽ ሰጥታለች።በሌላ አንፃር ግብፅ ስለግድቡ መከታተሏን የኢትዮጵያ ሕዝብ ባትነግሩትም ያውቀዋል።ይህ ምን ይደንቃል? ከእዚህ ይልቅ ግብፅ ሕወሓት በትጥቅ ትግል ላይ እያለ ምን ያህል እንደረዳች ቢነገረን ጥሩ ነበር።
ባጠቃላይ ኢቲቪ´´ውሸት ሲደጋገም እውነት ይባላል´´ በሚል የተሳሳተ እሳቤ ሕዝብን ያስፈራራልኛል ያለውን ፕሮግራም ያለውን እየመረጠ ሕዝቡን እያሸበረው ነው።የመልክቱ አጠቃላይ ይዘት ሲመዘን ´´ሕወሓት ስልጣን ላይ ካልቆየ ትጠፋላችሁ´´ የሚል ነው።ሕዝብ ደግሞ የሚለው ´´ውረዱ እና እንደማንጠፋ እናሳያችሁ´´ የሚል ሆኗል።ከእዚህ ሁሉ ይልቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሁሉንም ንግግር በጉጉት እየተከታተለ እና የበለጠ መረጃ እያገኘ ከመሆኑም በላይ በእየለቅሶ ቤቱ ሁሉ በኢቲቪ መቀለድ የተለመደ ሆኗል።በኢቲቪ ፕሮግራም እራሳቸውን በእራሳቸው እያስደሰቱ ያሉት የስርዓቱ አቀንቃኞች ብቻ ናቸው።ጀዋርም ሆነ ፕሮፌሰር ብርሃኑን ወደ እንዲህ አይነቱ የትግል መስመር ያስገባቸው የሕወሓት 25 ዓመታት በደል እና ግፍ ነው።የኢትዮጵያ ህዝብም ጥያቄ የግለሰቦች ስብዕና አይደለም።አምባገነንነት እና ዘረኝነትን የሌለበት ሁሉም በሕግ የምተዳደርባት ኢትዮጵያን ማምጣት ነው።ይህ ደግሞ ከሕወሓት ጋር እንደማይሆን ካወቀው ቆይቷል።

ጉዳያችን GUDAYACHN

No comments: