በወታደራዊ አገዛዝ ስር የወደቀች አገር!
ከአርባ አመት በፊት፤ ደርግ
የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አውጥቶ ነበር። አዋጁ በአጭር እና ግልጽ ቋንቋ – “ማንኛውንም አይነት ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ እና ጽሁፍ
አባዝቶ መበተን ክልክል ነው።” የሚል ስሜት ያለው ነው። ከዚያው ጋር ተያይዞ የሰአት እላፊ አዋጅ ተከተለ። ቀጥሎም ያለህግ
ማሰር እና መግደል፤ ነጻ እርምጃ መውሰድ፤ ቀይ ሽብር ማፋፋም የወቅቱ ግዴታ ሆነ።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር
መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት ሲናገሩ፤ “ተማሪዎች ሆነን በነጻነት ሃሳባችንን እንገልጽ ነበር። ነገር ግን የደርግ አቸኳይ ግዜ
አዋጅ፤ ምርጫ ስላሳጣን ወደ ትጥቅ ትግል እንድንገባ ተገደድን” በማለት የራሳቸውን ግለ ህይወት አጋርተውናል። የቀድሞው
ፕሬዘዳንት ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም በበኩላቸው ከዚያ አዋጅ በኋላ የመጣውን እልቂት “መሆን ያልነበረበት፤ ግን የሆነ…
በታሪካችን ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ወቅት…” በማለት በቁጭት ጭምር ያስታውሱታል።
ይህ ሁሉ ዘመን አልፎ፤ አንድ ትውልድ በግፍ ረግፎ፤ አሁንም በህዝቡ ላይ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ይፋ ሆኗል።
በኢትዮጵያ አስቸኳይ ግዜ አዋጅ State of Emergency የሚወጣው አገሪቱ በጦርነት ወይም በተፈጥሮ አደጋ ስር ስትወድቅ
ወይም የወረርሽኝ በሽታ ሲስፋፋ እና መንግስት የመፍረስ አደጋ ሲያጋጥመው መሆኑን ህገ መንግስቱ ጭምር በአንቀጽ 93 ላይ፤
“…ስርአቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የህግ ማስከበር ስርአት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን …የፌዴራሉ መንግስት
የሚንስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የመደንገግ ስልጣን አለው” ይላል። (Read in PDF)
ጥቁር ሽብር ለማፋፋም የወጣ፤ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ!
እስካሁን ድረስ… በኢትዮጵያ
እና ኤርትራ መካከል ጦርነት ሲነሳ፤ አቶ መለስ ዜናዊ ምክር ቤቱን አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት አዋጁን ማጽደቃቸው ይታወሳል።
ከዚያም በምርጫ 97 ወቅት ምክርቤቱ ያላጽደቀው አስቸኳይ ግዜ አዋጅ ተነግሮ ነበር። እሱን ሳንቆጥረው… አሁን የተደነገገው
አስቸኳይ ግዜ አዋጅ ለኢህአዴግ 2ኛው፤ ለጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ደግሞ የመጀመሪያ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ሆኗል።
ሆኖም በህጉ መሰረት ይህ አዋጅ ምክር ቤት ቀርቦ በ2/3ኛ ድምጽ ሲሰጥበት ነው፤ አዋጅ ሆኖ የሚጸድቀው። በነግርዎ ላይ ምክር
ቤቱ ከመከፈቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነው አዋጁ በእሽቅድድም እንዲወጣ የተደረገው፤ በንጋታው ፓርላማው ስራውን ሲጀምር አዋጁን
እንዲያጸድቁ አልተደረገም። ለነገሩ የምክር ቤቱ አባላት የቀረበላቸውን ነገር አጨብጭበው የሚያጸድቁ በመሆናቸው አዋጁ ያለምንም
ተቃውሞ በመጽደቅ፤ በቅርቡ የህዝብን የወል መብት መግፈፍ ይጀመራል።
ይህ አዋጅ ተግባራዊ በሚሆንበት
ወቅት…. ወታደር፣ ፖሊስና ደህንነት በአንድ የእዝ ሰንሰለት ስር ሆነው መመሪያ እየተሰጣቸው እንደሚሰሩ ወይም በተቀናጀ ሁኔታ
የሰብአዊ መብት ገፈፋውን እንደሚያካሂዱ ግልጽ ነው። እንደ ህገመንግስቱ ቃል ከሆነ የአቸኳይ ግዜ አዋጅ ሲታወጅ፤ በጠቅላይ
ሚንስትሩ ስር ሰባት አባላት ያሉት “መርማሪ ቦርድ” ይቋቋማል። ገና ከጅምሩ ጠ/ሚ ኃይለማርያም መርማሪ ቦርዱን – Command
Post ብለውታል። ልብ በሉ። Command Post በወታደራዊ እዝ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውል ቃል ሲሆን፤ በአማርኛ “ጠቅላይ
መምሪያ” የሚለው ወታደራዊ ቃል በአቻነት ይዋሰነዋል። ቃሉ ላያጣላን ይችላል። ሆኖም በህገ መንግስቱ ላይ ያለውን ቃል ቀይሮ
‘ኮማንድ ፖስት’ በሚል ወታደራዊ ቃል መተካታቸው፤ በህዝቡ ላይ ጦርነት የማወጅ ስሜት ውስጥ መሆናቸውን ያሳብቃል። በኮማንድ ፖስቱ
አማካኝነት የአጋዚ እና ሌላውን ገዳይ ቡድን በአንድ እዝ ስር በማድረግ፤ በመንግስት የተደገፈ ጥቁር ሽብር ለማስፋፋት ያላቸውን
ህልም በጉልህ ያሳያል።
ይህ አስቸኳይ ግዜ አዋጅ፤
በመላ አገሪቱ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ተግባራዊ እንዲሆን የታወጀ ነው። (በየአራት ወሩ እየታደሰ የሚቀጥል ነው) በ’ነዚህ
ስድስት ወራት ውስጥ ለወታደራዊው ክንፍ የተሰጠው ስልጣን አለ። በነገርዎ ላይ… ከላይ እያወራን የመጣነው በህጉና
በህገ መንግስቱ ላይ ያሉትን ጉዳዮች ነው። ከህገ መንግስቱ ውጪ ለዚህ አካል የተሰጠውን ስልጣን እንመልከት። በአስቸኳይ ግዜ
አዋጁ ወቅት፤ በቡድን መንቀሳቀስ፣ የመጻፍ እና ሃሳብን መግለጽ ይገደባል። የእጅ ምልክት ማድረግ – ሁለት እጆች በተቃውሞ
ማውጣት ወንጀል ሆኖ ሊያሳስር ወይም ሊያስገድል ይችላል።
ይህ ብቻ አይደለም። ወታደራዊ
ኃይሉ የማንንም ሰው ቤት ሰብሮ ገብቶ የመበርበር ሙሉ ስልጣን ተሰጥቶታል። ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተጠርጣሪ ያላቸውን ሰዎች
የማሰር ስልጣን አለው። ሰዎችን አስቁሞ መፈተሽ፣ ‘አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ’ ያላቸውን ነገሮች መውረስ ይችላል። ዜጎችን
ከአንድ ቦታ አስነስቶ ወደሌላ ክልል በመውሰድ የማስፈር ስልጣን ተሰጥቶታል፤ ወይም ሰዎች ወደ አንድ ቦታ እንዳይገቡ ማገድ
ይችላሉ። የሁኔታው ልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫ የሆኑ ተቋማትን መዝጋት ይችላል ተብሏል። በዚህ ላይ የፍሬ ነገር እና የስነ
ስርአት ህጎች ተሰርዘዋል። ይህ ማለት አንድ ወታደር መጥቶ በምክንያትም ሆነ ያለ ምክንያት አንድን ዜጋ ቢያስር ወይም ቢገድል
አይጠየቅም። በሌላ በኩል ደግሞ በአስቸኳይ ግዜው አዋጅ ወቅት ለሚደረጉት ነገሮች አለመተባበር ከ3 እስከ አምስት አመት
የሚያሳስር መሆኑ ተገልጿል።
እንግዲህ በአንድ በኩል፤
“በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ወቅት የሰብአዊ መብቶች የሚጠበቁ መሆናቸው በህገ መንግስቱ ላይ ተገልጾ አለ፤ ግን አይከበሩም። ለነገሩ
ከላይ የገለጽናቸው… ቤትን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ መበርበር ወይም ሰውን ማሰር ከአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በፊትም ሲደረጉ ነበር።
የአሁኑን ለየት የሚያደርገው “ህጋዊ” ሽፋን ስለተሰጠው እና መጠነ ሰፊ አፈና ስለሚደረግበት ነው። ከሁሉም በላይ የሚገርመው
ግን፤ ከላይ የዘረዘርነው፤ የወል እና የግል መብትን የሚጨፈልቀው ስልጣን በህግ ያልጸደቀ፤ ህጋዊ መሰረት የሌለው ህግ
እና ህገ መንግስቱን የሚጻረር መሆኑ ነው።
ከላይ የገለጽነውን አባባል
ግልጽ ለማድረግ ያህል… አሁን ኢህአዴግ በአስቸኳይ የግዜ አዋጅ ጥሩንባ ህዝቡን፤ ለግዜው ለማስደገጥ ፈልጎ ካልሆነ በስተቀር፤
እነዚህ የመብት ጥሰቶች ላለፉት በርካታ አመታት በህዝቡ ላይ ሲጫኑበት ነበር። የመሰብሰብ እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት
ከተገደበ ቆይቷል። ያለምክንያት ማሰር፣ ማሰቃየት እና መግደል አዲስ ነገር አይደለም። በመጻፋቸውና ሃሳባቸውን በነጻነት
በመግለጻቸው “አሸባሪ” ተብለው የታሰሩ ብዙ ናቸው። የአሁኑን ልዩ የሚያደርገው… የድርጊቱ ፈጻሚዎች ህገ ወጥ ተግባር
እንዲፈጽሙ፤ የህግ ሽፋን የተደረገላቸው መሆኑ ነው። (ዝኒከማሁ)
ይህ ሁሉ ሆኖ… በጣም
የሚገርምና የሚያሳዝነውን ነገር ሳንጠቅስ ማለፍ የለብንም። ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ በዚህ ጉዳይ መግለጫ ሲሰጡ፤ “የጠላት
እንቅስቃሴን ለማስቆም…” ብለዋል። ግን ማነው ጠላት? ለመብቱ የተነሳው የአማራ እና የኦሮሞ፤ የኮንሶ እና የጋምቤላ ህዝብ
እንዴት ነው በጠላትነት የሚፈረጀው? ህዝብ ጠላት ከሆነ ወይም በጠላትነት ከተፈረጀ ኑሯችን የነብር እና የፍየል አይነት፤
በመገዳደል ላይ የተመሰረተ የአውሬ ግንኙነት ሊኖረን ነው – ማለት ነው። እንኳንስ በዚህ ዘመን ቀርቶ በምኒልክ ዘመን እንኳን፤
ህዝብ በክብር እና በፍቅር እንጂ በሃይል ተረግጦ አልተገዛም። ይህ ሊሰመርበት ይገባል።
ሌላው መታወቅ ያለበት… በዚህ
የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ማንም ማንንም አያሸንፍም። ነገሩ አሸናፊ የማይኖረው የጦርነት አዋጅ ነው። አውሬ የሰውን ልጅ
አፍስሶ አሸናፊ እንደማይሆነው ሁሉ፤ ኢህአዴግም ብዙ ህዝብ ገድሎ ዜጎችን ሰጥ ለጥ ቢያደርግ ዋንጫ የሚሸልመው ወይም አሸናፊ
ብሎ የሚያጨበጭብለት አይኖርም። እጁን በደም ታጥቦ፤ በዜጎች ሬሳ ላይ ቆሞ የሃዘን መግለጫ እያወጣ፤ የሚያቅራራ ጀግና ከሴት
ማህጸን መሆኑም ያጠራጥራል። እንኳንስ ሌላ መቶ እና ሺዎችን መጨመር ቀርቶ፤ እስካሁን ባለው ሁኔታ የብዙ ንጹሃን ዜጎች ደም
እየጮኸ ነው ያለ። ሌላ ተጨማሪ የደም ማፋሰስ ለማድረግ አዋጅ ማስነገር፤ ስርአቱን የበለጠ ያፈራርሰዋል እንጂ አይገነባውም።
ህዝቡ የንግድ እና የመንግስት
ተቋማትን የሚያፈራርሰው እኮ ጥቅም እንዳላቸው አጥቶት አይደለም። ተቋማቱ እንደሚጠቅሙት ስለሚያውቅ ላለፉት አመታት ተቃውሞውን
ሲያቀርብ አላወደማቸውም። ከቢሾፍቱ ግድያ በኋላ “አንድም ጥይት አልጮኸም” ህዝቡ ሊናደድ ይችላል። መንግስት ወይም መንግስትን
የሚወክል አካል ሲዋሽ ውስጥን ያማል። ህዝቡ በንዴት ተቋማትን ቢያወድም የምሬቱ መጨረሻ ሆኖበት ነው። እናት አባቱን፤ ወንድም
እህቱን ቀብሮ የመጣ ሰው በንዴት ቤት ቢያቃጥል፤ ትክክል ባይሆንም እንኳን ለዚያ ያደረው ምክንያት አለ። “አቤት” የሚልበት
ችሎት ሲያጣ፤ የእንባውም ጽዋ ሞልቶ ቢፈስበት ነው ግብታዊ እርምጃ የሚወሰደው። ከመሬቱ ያለምንም ካሳ እና ክፍያ
የተፈናቀለ ገበሬ፤ ከናት አባት አያት ቅድማያቱ የወረሳት መሬት ለባለሃብት ተሰጥቶበት፤ ልጆቹን የሚያበላው አጥቶ ሲብከነከን…
ባለሃብቱ ደግሞ ያችን መሬቱን ወስዶ ሸንኮራ እና አበባ ሲያበቅልበት ማየት ለዚያ ገበሬ ምን ማለት እንደሆነ ለአንድ ደቂቃ
እናስበው።
አንዳንዶች ስለህገ መንግስቱ
መፍረስ እናወራለን። ህገ መንግስት የተሰራው መንግስት ህዝብን እንዳይበድል መቆጣጠሪያ ነው። ህዝቡማ ከድሮም ሚዳኝበት የፍትሐ
ብሄር እና የወንጀል ህገ ስርአት አለው። ህገ መንግስት ግን የተሰራው እንደኢህአዴግ ያሉ አምባገነን መንግስታት በህዝቡ ላይ
አፈና እንዳይፈጽሙበት ነው። አሁንም ህገ መንግስቱን እየናደ ያለው እራሱ ኢህአዴግ እንጂ ህዝቡ አይደለም። ህዝቡማ ከሰው በታች
ተቆጥሮ… እየታሰረ፣ እየተቀጠቀጠ፣ እየሞተ ነው ያለ። ህዝቡ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ፤ ስለህገ መንግስት መናድ ቀርቶ ስለአገር
መፍረስ ላያስብ ይችላል። ህዝብ በዚህ አይነት የጭንቅ ማጥ ውስጥ ሲገባ፤ እንደሰይጣን ነገሩን የሚያባብስበት ሳይሆን፤
እንደአባት ችግሩን የሚሰማለት አካል ይፈልጋል። መንግስት ይህን ለማድረግ ስለተሳነው፤ የህዝብን ድምጽ በጉልበት ለመደፍጠጥ
አዋጅ አውጥቷል።
አሁን ባለው ሁኔታ… ኢህአዴግ
የህዝቡን ትክክለኛ ብሶት አዳምጦ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ፤ ለህዝቡ ሞት እየደገሰለት ነው የሚገኝ። የህዝቡ ጩኸት የአስተዳደር
እጦት ብቻ አይደለም። ሰው በአገሩ እንደ2ኛ ዜጋ ተቆጥሮ ከመሬቱ ሲፈናቀል፤ ተፈናቅሎም መሬቱ ለባለግዜ ሲሰጥበት ማየት በጣም
ያማል። ሁለት ሰዎች ፍርድ ቤት ቀርበው አንደኛው የእገሌ ብሔር ሌላኛው ኦሮሞ ወይም አማራ ወይም የሌላ ብሔር ተወላጅ ስለሆነ፤
በፍርድ ቤትአድልዎ ሲደረግበት፤ ሌላኛው ብሔር ከሌላው ኢትዮጵያዊ በልጦ ሲፈርድለት ማየት ህሊናን ይበጠብጣል። የአንድ ብሔር
የበላይነት ብቻ ሳይሆን የአንድ ፓርቲ ተጠቃሚነት በአዋጅ ስላልተነገረ እንጂ በህግ ፊት ሁሉም ዜጋ እኩል አለመሆኑ በራሱ ቆሽት
ያደብናል። አንደኛው ወገን ያለምንም ይሉኝታ ሙስና ውስጥ ተዘፍቆ ገንዘብ በገንዘብ ሲሆን፤ ፎቅ ሲሰራ፤ ልጆቹን ውጪ ልኮ
ሲያስተምር፤ ሚስቱን ታይላንድ ወስዶ ሲያሳክም፤ ሌላኛው በንጹህ ኢትዮጵያዊ ልብ የሚያገለግለው ዜጋ ደግሞ ቁልቁል ሲወርድ ማየት
አንጀት ይቆርጣል።
ኢህአዴግ እና አባላቱ እነዚህን
ያፈጠጡ እውነቶችን ከመቀበል ይልቅ ጣታቸውን የተቃወሟቸው ሰዎች ላይ ቀስረው፤ አፈሙዛቸውን ወደ ህዝቡ አዙረው፤ የሞት አዋጅ
አውጀዋል። የመብት ጥያቄ የሚያነሱ እና ሃሳብ የሚያቀርቡ ሰዎች ጭምር፤ “ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ” የሚል አንቀጽ ተጠቅሶባቸው
የሚታሰሩበት አዋጅ ተዘጋጅቷል። ኢህአዴግ ራሱ የችግሩ አካል ስለሆነ፤ የችግሩን ስረ-መሰረት ማየት አልቻለም ወይም ሽምጥጥ አድርጎ
ሃቁን እየካደ ነው። ስለ ልማት ሲያወሩ ስለሰው እና ስለ ህብረተሰብ የህሊና ልማት አያወሩልንም። የአንድ ህዝብ ልማት የሚለካው
በፎቅ እና በመንገዱ ብዛት አይደለም። የአንድ ህዝብ ልማት መለኪያ የህዝቡ ንቃተ ህሊና እድገት ጭምር ነው። የህዝብ እድገት
ደግሞ መለኪያው ሃሳቡን በነጻነት መግለጽ ሲችል፤ የመደራጀት እና የመሰብሰብ ነጻነቱ ሲጠበቅለት ነው። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ግን
ይህ እየሆነ አይደለም።
ይልቁንም እነዚህ የሰው ልጅ
መሰረታዊ መብቶች እየተሸረሸሩ እርቃናቸውን ቀርተዋል። ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የምናየው የሰብአዊ መብት አያያዝ እርቃኑን የቀረ
አጽመ ሰብ ሆኗል። እነአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የህወሃት ባለስልጣናት የሚፈጽሙትን በደል እያዩ፤ በነሱ ላይ ምንም እርምጃ
አይወስዱባቸውም። ይፈሯቸዋል – በጣም ይፈሯቸዋል። የህወሃት ወታደራዊ እና የደህንነት ክፍል፤ ለነአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ
እንደማይደፈር የ’እስራኤል ብረት ግንብ ነው። ህወሃትን ሊናገሩ ቀርቶ፤ ሌላው ህወሃትን ሲናገር ይደነግጣሉ፤ ፍራቻቸው ለከት
የለውም። ይህ ፍራቻ በአቶ ኃይለማርያም ላይ ብቻ ሳይሆን በሌላውም የኢህአዴግ አባል እና ደጋፊዎች ላይ ይታያል። አቶ መለስ
ዜናዊ ጣኦት ሆኖ የሚመልክበት ቢሆን ያመልኩበታል። እንደነብይ ወይም እንደቅዱስ ሃዋርያ ስለሚያዩት መለስ ዜናዊን በመጥፎ
ማንሳት ማለት፤ እግዚአብሔርን የመሳደብ ያህል የሚቆጥሩ አሉ።
በአቶ መለስ ዜናዊ ዘመን፤
የ97ቱን እንቅስቃሴ ታፍኖ ስለቆመ… አሁንም ያንን መድገም የሚቻል የሚመስላቸው፤ አሁንም ድረስ የትላንት በርኖስ ለብሰው የተኙ
ሰዎች አሉ። እውነታው ግን የትላንቱ አለም ብቻ ሳይሆን የትላንቱ ትውልድ ጭምር እየተቀየረ ነው የመጣው። ትላንት ተራራን
ያንቀጠቀጡ የተባለላቸው ሰዎች፤ አሁን በህዝብ ጩኸት ፍርሃት ይዟቸው የሚንቀጠቀጡ ድንጉጣን ሆነዋል። ሁሉም የናጠጡ ሃብታሞች
በመሆናቸው ድሃው እንዲሞትላቸው የውሸት ፕሮፓጋንዳ ከማሰማት ያለፈ ሚና አይጫወቱም። አንዳንዶቹ እንኳንስ እንደድሮው በርሃ
ተመልሰው ሊገቡ ቀርቶ ጠመንጃውን መቋሚያ ሊያደርጉት ካልሆነ በቀር፤ ለሸክም ይከብዳቸዋል። እነዚህ ያረጀው ኢህአዴግ የሚፈራቸው
የህወሃት አባላት፤ እንደጉርጥ ከማበጥ ውጪ ተጨባጭ ለውጥ የማያመጡ፤ መገዘኛቸው የረሰረሰ፣ መቃብራቸው የለሰለሰ ሰዎች
መሆናቸውን የዘነጉ ብዙዎች አሉ። እነዚህ እኩያን የመሰረቱት ስርአት ግን፤ አሁንም ዜጎችን የማሰር እና የመግደል ሙሉ ስልጣን
ተሰጥቶታል። ልዩነቱ እያረጀ የመጣውን ስርአት እና የስርአቱን ተጠቃሚዎች እድሜ ለማራዘም ሲባል የአስቸኳይ የግዜ አዋጅ ወጥቶ፤
የቆየውን የህወሃቶች ህገ ወጥ ተግባር እነአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ህጋዊ ማድረጋቸው ነው። ልዩነቱ ይሄ ብቻ ነው።
ፍሬ ነገራችንን እያጠቃለልን
ነው። ይህን ሁሉ ካልን በኋላ አንድ የተዘነጋ ጉዳይ እናስታውሳቸው። ኢህአዴግ እና አባላቱ ለህወሃት የሚሰግዱትን
ያህል፤ ህዝቡ ህወሃቶችን ለአፍታ ያህል መፍራቱን አቁሟል። እነአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ካቢኔያቸው… ህወሃትን ስለሚፈሩ
ህዝቡም በነሱ መጠን ፈሪ መስሎ ይታያቸዋል። ይህ ግን ልክ አይደለም። ይልቁንም ህዝቡ ቆርጦ እንዲነሳ ያደርጉታል እንጂ፤
የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የህዝቡን ንቅናቄ አይገታውም። እንዲያውም መንግስት እዚህ ደረጃ ደርሶ፤ ፈርቶ እና ተንጰርጵሮ አዋጅ
ማስነገሩ፤ የህዝቡ ትግል አንድ እርምጃ ወደፊት ለመሄዱ ዋነኛ ምልክት ነው።
በአጠቃላይ አዋጁን ተከትሎ
የሚመጣው አሸናፊነትም ሆነ ተሸናፊነት ብሔራዊ ውርደትን እንጂ፤ ኩራት ሊሆነን አይችልም። ሲጀመር ባዶ እጁን የወጣን ህዝብ ጋር
በጠመንጃ ደብድቦ የሚገኝ ድል አይኖርም። ሲቀጥል ይሄ ሁሉ ፉከራ ተደርጎ ሽንፈት ቢመጣ ውርደቱ ለኢህአዴግ ባለስልጣናት ብቻ
ሳይሆን፤ “አሉኝ” ለሚላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባሎቹ ጭምር ነው። ሽንፈቱ እና ውርደቱ ያሳፍራል። አንገት
ያስደፋል። አሳፋሪ ነው። በአገር ደረጃ ስሜትን ይነካል።
የዚህ ጥቁር ሽብር ውጤትም…
እስካሁን ሰራን የሚሏቸውን ነገሮች በዜሮ ማባዛት ማለት ነው።
Source: ethioforum
No comments:
Post a Comment