Tuesday, July 14, 2015

ፍርድ ቤቱ ለሶስተኛ ጊዜ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትን ጉዳይ አላይም አለ

• ‹‹ባራክ ኦባማ ሲመጣ ሰልፍ ለመጥራት እያደራጁ ነው›› ፖሊስ
ባራክ ኦባማ ሲመጣ ሰልፍ ለመውጣት እያደራጃችሁ ነው ተብለው በፖሊስ የተያዙትን የእነ ደብሬ አሸናፊ ጉዳይ ፍርድ ቤቱ ለሶስኛ ጊዜ አላይም አለ፡፡ ፖሊስ እነ ደብሬ አሸናፊን በትናንትናው ዕለት በመናገሻና አራዳ ፍርድ ቤት ቢያቀርባቸውም ሁለቱም ፍርድ ቤቶች ‹‹ጉዳዩን አናይም!›› ማለታቸው ይታወቃል፡፡ ፖሊስ ዛሬ ሀምሌ 7/2007 እነ ደብሬን ለሶስተኛ ጊዜ ሰባራ ባቡር አካባቢ የሚገኝ ፍርድ ቤት ቢያቅርባቸውም ፍርድ ቤቱ ለሶስተኛ ጊዜ ‹‹የሚረባ መረጃ ስላላቀረባችሁ ጉዳዩን ልናይ አንችልም፡፡›› ብሏቸዋል፡፡
ፖሊስ ‹‹ምስክር አለኝ፣ መረጃ አጠናክሬ እመጣለሁ›› በማለቱ ፍርድ ቤቱ ሁለት ቀን ቀጠሮ ፈቅዶለታል፡፡ በመሆኑም እነ ደብሬ አሸናፊ፣ ቴዎድሮስ ሻንካና ኤፍሬም የተባሉት ታሳሪዎች ሀሙስ ሀምሌ 9/2007 ዓ.ም ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡ ደህንነቶች ታሳሪዎቹን በተለይም አቶ ደብሬ አሸናፊን ሌሊት በመጥራት ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ኦባማ ሲመጣ ሰልፍ ለመጥራት በድብቅ እየሰራ እንደሆነ ደርሰንበታል፡፡ ንገረን!›› እያሉ እንደሚመረምሩት ታውቋል፡፡
በተመሳሳይ የሰማያዊ ፓርቲ የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባል የሆነው አቶ መርከቡ ኃይሌ ትናንት ሀምሌ 6/2007 ዓ.ም አራዳ ፍርድ ቤት ቀርቦ 10 ቀን ቀጠሮ ተሰጥቶበታል፡፡ አቶ መርከቡም ‹‹ኦባማ ሲመጣ ሰልፍ ለመጥራት እያደራጀህ ነው›› የሚል ክስ የቀረበበት ሲሆን ፖሊስ እስከ ሀምሌ 16/2007 ዓ.ም ተጨማሪ መረጃ አቀርባለሁ ብሏል፡፡ በተመሳሳይ የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነው አቶ ሲሳይ ካሴ በተመሳሳይ ክስ ታስሮ ከእስር በዋስ የወጣ ቢሆንም ቅዳሜ ሀምሌ 4/2007 ዓ.ም አራዳ ፍርድ ቤት ቀርቦ ለሀምሌ 11/2007 ቀጠሮ ተሰጥቶበታል፡፡ አቶ መርከቡ ኃይሌ ወረዳ ዘጠኝ እስር ቤት ይገኛል፡፡

No comments: