Saturday, July 18, 2015

የማስመሰል ክህሎቱን ያጣው ስርዓት:- መቶ በመቶ አሸንፌያለሁ የማለት ጉዳይ

በኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ላይ “ኢህአዴግ ለምን መቶ በመቶ ውጤት ደፍኖ ለማሸነፍ ፈለገ” ለሚል ጥያቄ የተሰጠ ምላሽ፤ (የተወሰነ ማስተካከያ እና ጭማሪ ጋር)
እኔ እንደምረዳው በዋናነት አንድ ሥርዓት ወደ ማብቂያው አፋፍ ላይ ሲቃረብ፣ የማስመሰል ክህሎቱን ያጣል፡፡ ለዚህ አመለካከት ብዙ የታሪክ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በቅድሚያ፣ ኢህአዴግ ከደርግ የሚለይበት አንድ ወሳኝ ነገር ነበር፡፡ ደርግ ማስመሰል ላይ ደካማ ሲሆን ኢህአዴግ ማስመሰል ላይ በጣም የተካነ ነበር፡፡ አሁን ጊዜው እያለፈ ሲሄድ፣ ኢህአዴጎች ማስመሰል እየተሳናቸው መጥቷል፡፡ ማስመሰል ለማንኛውም የፖለቲካ ስርዓት አብሮ የሚጓዝ አካል ነው፡፡ ወደ ተነሳንበት ጥያቄው ስንመለስ፣ አገኘን የተባለውን የውጤት ጠንጠረዥ በምንመለከትበት ጊዜ በህዝብ ተቀባይነት ይኖረዋል ብለው ማመናቸው፣ ለማስመሰል መሰጠት ያለበትን አተኩሮ እና ችሎታ በእጅጉ እንዳጡት ማሳያ ነው፡፡

በዚህ ብቻ ሳይሆን፣ በሰሜን አፍሪቃ እና በአረብ አገር ኢትዮጵያውያን ስደተኖች በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ እና ዜናው እንደተሰማ፣ የመንግሥት ሹመኞች ስለተፈጸው ዘገናኝ ሁኔታ በነበራቸው አቀራረብ ብዙ ሰዎች በእጅጉ አዝነዋል፡፡ እነሱ ከነገሩ ክብደት ይልቅ ፖለቲካቸውን በማስቀደም የሀዘን ስሜት እንኳን እንዳደረባቸው ለማስመሰል አልቻሉም፡፡በማግስቱ፣ህዝቡ በራሱ ተነሳስቶ፣ ወደ ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጣ ‹‹አይ የነገን እለፉንና እኛ እራሳችን ሰልፍ እንጠራለን ብለው፣ የሆነው ነገር ሆኗል፡፡ ለማጠቃለልም መቶ በመቶ አሸንፈናል ብለው ሲወጡ፣ ለፖለቲካ ግብዓት ሊያግለግል የሚችለው የማስመስል ዘይቤ እንኳን እንዳጡት መረዳት አያዳግትም፡፡
በሁለተኛ ደረጃ፣ ከዚሁ ጋር በማያያዝ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በህይወት በነበሩ ጊዜ፣ ያለምንም ጥርጥር የተለያዩ የመንግሥት ዘርፎች ሁሉ፣ በሳቸው መዳፍ ሥር የወደቁ ነበሩ፡፡ በእርግጥ፣ እሳቸውን የተካ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢኖረንም ቅሉ፣ የሥርዓቱን ሁኔታ በቅርብ የሚከታተሉ ሰዎች እንደሚረዱት፣ በሥርዓቱ ውስጥ የኃይል ትንቅንቅ እና በተቋማት መካከል ልዩነትን እና ጥቅምን ያዘለ ግብግብ አለ፡፡ የክፍፍሉን አሰላለፍ በምንመለከትበት ጊዜ የሚከተለውን ረድፍ እናያለን፤ ሠራዊቱ ለብቻው ሄዷል፤ ደህንነቱና ጸጥታው በሌላ በኩል እየሄደ ነው፡፡የተዳከመው ፓርላማም ቢሆን አልፎ አልፎ ለብቻው አቋም ይዞ ይንቀሳቀሳል፡፡ ከዛ ደግሞ ከፍተኛ የፓርቲ አመራሮች አሉ፡፡ በመጨረሻም ደግሞ የክልል አስተዳዳሪዎች አሉ፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ ስራዓቱ በሠራዊቱ፣ በጸጥታው ፣ በፓርላማው እና በከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮቹ መካከል ክፍፍል እና ክፍተት አለው፡፡
አገሪቱ ያለችበትን የፖለቲካ ድባብ ለማየት ስንሞክር ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ህልፈት በኋላ ፣ ሁሉንም በበላይነት አጠቃልሎ የሚይዝ ፈረንጆቹ ‘Strong Man’ የሚሉት ‘ጠንካራ ክንድ’ ስራዓቱ ገና አላወጣም፡፡ ስለዚህ፣ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጊዜ እንደሚያደርጉት፣ መክረው-ዘክረው እንደዚህ ያለ ቁጥር ያስፈልገናል፤ በእንደዚህ ያለ ቦታ እንዲህ እናሸነፋለን፣ በዚህ ቦታ ደግሞ እንዲህ እንይዛለን የሚል ኢህአዴግአዊ የጋራ ሥምምነት ፈጥረውና ስትራቴጂ ነድፈው መቅረብ አቅቷቸዋል፡፡
በሶስተኛ ደረጃ ፣መንግስት ደጋግሞ ሊያሳምነን የሚፈልገው አገሪቱ በአለም ደረጃ ከሚገኙት ግዙፍ የፋይናንስ ተቋማት ብር የመበደር አቅሟ ጨምሯል፡፡ ከዚህም ጋር በማያያዝ የዓለም አቀፋዊ ተቋማት አስተያየትና ነቀፊታ እምብዛም አያሳስበንም ብለው ያምናሉ፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የምዕራቡ ዓለም ብቻ ሳይሆን “ቻይናም አለችን” የሚለው አመለካከታቸው እየተጠናከረ መጥቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር ለማደጋችን እንደማሳያ የሚያቀርቡት፣ “የዓባይ ግድብ ግንባታ በራሳችን አቅም እየገነባን” እንገኛለን የሚል ነው፡፡ ከአሁን ወዲህ ዴሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብት አያያዝ ብሎ ሊያስተምረን የሚሞክረውን ማንኛውንም ተቋም አንቀበልም ወደ ማለት ተደርሷል፡፡

በአንጻሩ መዳኘት ያለብን ዴሞክራሲ በማምጣት፣ ሰብዓዊ መብት በማስጠበቅ፣ በአጠቃላይ ነፃነትን ለኢትዮጵያ ህዝብ በማጎናጸፍ ሳይሆን ፈረንጆቹ ‹‹ግብራዊ ቅቡልነት›› (Performance Legitimacy) በሚሉት፣ ‹‹በምንሰራው ልማት፣ በምንሰራው የሸንኮራ አገዳ ፋብሪካ፣በምንገነባው ግድብና መንገድ… ወዘተ ነው፡፡››
ለነገሩ የህዝብ ቁቡልነትን ለማገኘት ሙከራ ብናደርግም ይሁንኑ ማሳካት ቢሳነን ሠራዊቱ፣ ደህንነቱ እና ኢኮኖሚው በእጃችን ስለሆነ እምብዛም አሳሳቢ ሆኖ አናገኘውም ብለው ያምናሉ፡፡የውጭውን ዓለም በሚመለከት ከቻይናም ባሻገር የምዕራብ ዓለሙን ጥቅም የምንገዳደር ስላልሆንን ዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት አላከበራችሁም ብለው ጠንከር ያለ ጫና አያሳድሩብንም፡፡
ስለነጻና ፍትሃዊ ምርጫ በምንነጋገርበት ጊዜ፣መንግሰት አቃሎ እንደሚያቀርበው ሳይሆን ቢያንስ ቢያንስ የአምስት ዓመቱን የፖለቲካ ድባብ፣ ነጻ የፍትህ ተቋም፣ የመናገርና የመሰብሰብ መብት እና ገለልተኛ የምርጫ ቦርድን ያካትታል፡፡
በምርጫው ሂደት ተገኘ የተባለውን ቁጥር ስንመለከት ግን አውሮፓውያን እንደሚሉት ‹‹የመሽን ፖለቲክስ›› ውጤት ነው፡፡ ‹‹የመሽን ፖለቲክስ›› ሲባል ከዚህ በታች የሚከተለው ባህሪያት ያካትታል፤ ሀገሪቱን በአንድ ለአምስት በማደራጀት እና በመጠርፍ “መሽኑ” ቁጥር ፈብርኮ እንዲያወጣ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም ከዚህ በፊት ደጋግመው በየክልሉ በዓመት ለስልሳ ቀናት ያህል ገበሬውን ለአካባቢ ጥበቃ በሚል ሰበብ ያለምንም ክፍያ በቁጥር እያሰለፉ ሲያስወጡት ከርመዋል፡፡ ይህኑኑም ተሞክሮ፣ “መሽኑ” ካርድ ለማስወሰድም ተጠቅሞበታል፡፡ ይህንን ካደረጉ በኋላ በአንድ ሳምንት ውስጥ 36 ሚሊዮን ህዝብ መመዝገቡ “የሃገሪቷን የዲሞክራሲ እድገት አመላካች ነው” በማለት አቅርበዋል፡፡
እነሱ እንደሚያቀርቡት በሳምንት የተጠቀሰው ቁጥር በፍላጎትና በራስ ተነሳሽነት ካርድ የወሰደ ቢሆን ኖሮ በእርግጥም ሃገራችን በዴሞክራሲ የተናወጠች ናት ማለት ነው፡፡ የተባለው ዲሞክራሲ ካለም ህብረተሰቡ በትራንስፖርት፣ በካፌቴሪያ፣ በመዝናኛ ቦታዎች…ወዘተ ላይ የተሟሟቀ የፖለቲካ ውይይት እና ክርክር ሲያደርግ ይስተዋል ነበር፡፡
ለነገሩ ጋዜጣው ላነሳው ምልከታ የመሰለኝን አተያይ ለማቅረብ ሞከርኩ እንጂ ምርጫን በሚመለከት በእኔ በኩል ተገቢ እና ወሳኙ ጥያቄ የሚከተለው ነው፡፡ በእርግጥ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ስርዓት ተዘርግቷል ወይ? በተጨማሪም ዲሞክራሲያዊ ሃገራት እንደሚያደርጉት እና እንደሚረዱት በኢትዮጵያ ምድር ላይ “ምርጫ” ይቻላል ወይ? ለዚህ ጥያቂ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ከተቻለ በእርግጥ ስለቀረበው ውጤት የፖለቲካ ትንተና ማቅረብ ይቻላል፡፡ በእኔ በኩል ግን ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ተገቢ እና በቂ የሆነ ሁኔታ (Condition and possibility) አለ ብዬ አላምንም፡፡

No comments: