Sunday, July 5, 2015

‹‹የሳሙኤል ግድያ ለታጋዮችም ለገዳዮችም ትልቅ ትምህርት ነው!››



(ኢ/ር ይልቃል ጌትነት የሳሙኤል አወቀ መታሰቢያ ፕሮግራም ላይ ከተናገሩት)
ስለ ሳሙኤል ግድያ ብዙ ነገር ተብሏል፡፡ ብዙዎች ቁጭታቸውን ገልፀዋል፡፡ ለእኔ ከሳሙኤል አወቀ ግድያ ምን እንማራለን? የሚለው ነው ትልቁ ቁም ነገር፡፡ ሳሙኤል በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ንግግር ተናግረው የተገደሉ ሰዎች ጋር የሚመደብ ሰው ነው፡፡ የሳሙኤል ትውልድ አካል በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል፡፡ እንደገሚገሉት እያወቀ፣ ነገር ግን ያ ሞቱ ከንቱ እንዳይሆን አስፈላጊውን መረጃ አስቀምጦልናል፡፡ አቡነ ጴጥሮስ መንፈሳዊ አባት ማለት ምን ማለት እንደሆነ አስተምረው ህዝቡ ለጣሊያን እንዳይገዛ ሰብከው ተገድለዋል፡፡ ለዚህም ሀውልት ቆሞላቸዋል፡፡ ይህ መታሰቢያ ለኢትዮጵያዊነት የመንፈስ ልዕልና እና የአልበገሬነት ምልክት ሆኖ ለዘላለም ይኖራል፡፡
የአቡነ ጴጥሮስን ታሪክ ተማሪዎችም ይማሩበታል፡፡ የሳሙኤልን ንግግርም ወደፊት እድሜ ከሰጠን እኛ እናየዋለን፡፡ እኛ ባንደርስበት እንኳ መጪው ትውልድ ሳሙኤል ለሀገሩ ሲል ዋጋ እንደከፈለ መታወሱ የማይቀር ነው፡፡ ምክንያቱም ይህን አይነት ታሪክ የሰሩ ሰዎች በህዝቡ ውስጥ ትንሽና የተመረጡ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ በመሆኑም ሳሙኤል ከመካከላችን የተገኘ ልዩና ዕንቁ የኢትዮጵያ ልጅ ነው፡፡ ሳሙኤል እኔ በምመራው ፓርቲ፣ በእኔ ትውልድ ውስጥ እንዲህ አይነት ታሪክ መስራቱ ትልቅ የመንፈስ ጥንካሬ ሰጥቶኛል፡፡ ህይወት ምን እንደሆነም አስተምሮኛል፡፡
በህይወት መቆየትን እንደ ትልቅ ነገር ቆጥረውት ከትግል እንድንወጣ የሚመክሩን በርካቶች ናቸው፡፡ እነሱ የሚሉን ህዝብ ሲጨቆን ዝም በሉ ነው፡፡ ሳሙኤል ደግሞ እንዲህ አይነቱን ነገር መስራት እንደሌለብን በደሙና በአንድ በማትተካ ህይወቱ አሳይቶናል፡፡ እንደዚህ የሚሉንን ሰዎች ለመናቅ ሳሙኤልን ማሰብ ብቻ በቂ ነው፡፡ ገንዘብ ሲቸግረኝ ሳሙኤል ህይወቱን ማጣቱን ማስታወስ ይገባኛል፡፡ ለህይወት ትኩረት ስሰጥ፣ መኖር ስመኝ፣ መንፈሴ ሲላላ በእኔ ትውልድ ዘላለማዊ ሆኖ ያለፈውን ሳሙኤልን ማስታወስ አለብኝ፡፡ የሳሙኤል ግድያ ለታጋዮችም ለገዳዮችም ትልቅ ትምህርት ይሰጣል፡፡ በእኔ እምነት ሳሙኤልን የገደሉት በግል ስለሚጠሉት አይመስለኝም፡፡ ሳሙኤል የብሩህ አእምሮ ባለቤት ነው፡፡ የመረጃና የአቋም ሰው ነው፡፡ በጣም ጠንካራ ልጅ ነው፡፡ ይህን አስተሳሰቡንና እምነቱን ነው የጠሉት፡፡ ይህ ሲጠፋ ለሌሎቹም መቀጣጫ መሆኑ ነው፡፡ ዛሬ ግን በሳሙኤል ደም እኛ ተሰባስበናል፡፡ መፍራትና ወደኋላ ማለት እንደሌለብንም አስተምሮናል፡፡ ከዚህ ባለፈ በዚህ ትግል ውስጥ ለነገ የሚባል ነገር እንደማይሰራ የሳሙኤል ግድያ አሳይቶናል፡፡
የሰው ልጅ በባህሪው ሞኝ ነው፡፡ ዛሬን ብቻ አይደለም ዘላለምንም የምንኖር ነው የሚመስለን፡፡ ለሳሙኤል ግድያ ግን ህይወት ምን ማለት እንደሆነች አሳይቶናል፡፡ ዛሬውኑ ልትጠፋ የምትችል ከንቱ እንደሆነች አስተምሮናል፡፡ በመሆኑም የሳሙኤል ሞት ትርጉም ያለውን ነገር ዛሬ አድርጌ እንዳልፍ እንጅ ለነገ እንዳልል ትልቅ ትምህርት ሆኖኛል፡፡ ዕቅድ አንድ ነገር ነው፡፡ ሆኖም ሞት አብሮን ያለ መሆኑን ተረድተን ለሀገራችን የሚጠቅመውንና ዛሬ ማድረግ ያለብንን ነገር ዛሬውኑ መስራት እንዳለብን ነው፡፡ እንደ ሳሙኤል በዚህ አለም የማያልፍ ነገርን ሰርተን ማለፍ አለብን፡፡ በነፃነት ትግል ውስጥ ሳሙኤል ስም ሲነሳ ይኖራል፡፡ እንደ ሳሙኤል በህይወት ትርጉም ያለው ነገር መስራት ለህይወትም ትልቅ ትርጉም ይሰጣል፡፡ በኢትዮጵያ ከሉሲ ጀምሮ በሚሊዮን የሚቆጠር ሰው ሞቷል፡፡ ዋናው ነገር ግን 80ና 90 ቆይቶ መሞት አይደለም፡፡ እንደ ሳሙኤል በአጭር እድሜው ያመነበትን ሰርቶ መሞት ትልቅ ትርጉም አለው፡፡
እኛም 90ና 80 አመትን መጠበቅ ሳይሆን በ27 አመትም መቀጨት እንዳለ አውቀን አሁን መስራት ያለብንን በፍጥነት ማከናወን አለብን፡፡ በዚህ ግለኝነት፣ አግበስባሽነት በነገሰበት ሀገር ላይ ህይወትን ያህል ነገር ከፍሎ በደሙ ለእኛው ትውልድ አስተምሮ ሄዷል፡፡ ለሀገር፣ ለህዝብና ለእውነት መቆም የተከበረ ስራ መሆኑን ያውም ህይወቱን እንደሚያጣ አውቆት ለዓላማው በፍላጎቱ ሲሞት ከዚህ በላይ አስተማሪ አያስፈልግም፡፡ በወቅቱ ‹‹ይህ ትውልድ አይረባም፣ ሀገሩን አይወድም፣ ከዝሙትና ከመጠጥ ያለፈ ነገር አያውቅም፣ አይችልም›› የሚባለውን ሳሙኤል የሚባል ብርቱ ልጅ ከመካከላችን ወጥቶ እውነት እንዳልሆነ በተግባር አሳይቶናል፡፡ በዚህ ዘመን ደግሞ የጠፋው ከሳሙኤል አይደለም፤ ለራሳችን የቃል ኪዳን ሰው መሆን ነው፡፡ የሳሙኤልን ቃል የራስ አድርጎ መውሰድ፡፡ ክብር፣ ሞገስ፣ እውነትና ቃል ኪዳን ለራስ ነው፡፡ እሱ አከበርንለትም አላከበርንለትም የሚያምንበትንና የድርሻውን ሰርቶ ሄዷል፡፡ ለራሳችን ለእውነት፣ ለህዝብ፣ ለሀገር መቆም የሚያስከብር መሆኑን አስተምሮን አልፎአል፡፡
ይህንን ሳሙኤል እያወቀው ሞቶ የሰጠንን ክብር፣ ቃልና መስዋዕትነት ሳናጓድል አደራ የማንበላ ሰዎች እንዳንሆን፡፡ እኔ የምታገለው ለማንም አይደለም፡፡ ይች እግዚያብሄር የሰጠኝ እድሜ ትርጉም ያላት ሆና እንድታልቅ ስለምፈልግ ነው፡፡ ሳሙኤል በልጅነት እድሜው ቤተሰቦቹን አሳዝኖ ለእኛ ዋጋ ከፍሎልናል፡፡ ይህን ቃል ኪዳን ድርጅታችን እንደ ሰማያዊ፣ እያንዳንዳችን እንደ ግለሰብም፣ እንደማህበረስብና እንደትውልድም እንዳንበላ ብርታቱን ይስጠን እላለሁ፡፡

No comments: