Saturday, July 18, 2015

“እስቲ አንነጋገር የማስረጃን ነገር 5 “

“ቃላቸው” 
ተከሳሾች ሠጡት የተባለውን ቃል ስንመለከተው ደሞ ከመጻፍም አልፎ ከላይ የተባሉትን ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ማንበባቸውም ጭምር ተከሳሾችን ያሳሰራቸው ይመስላል፡፡ በብዙ ድብደባ እና አንግልት የተገኙት እነዚህ የተከሳሽ ቃላት ከላይ የሚገኙትን ከሰነዶች ላይ በመገልበጥ የእኔ ነው ብለው አንዲፈርሙ የተገደዱበት ነው ወንጀል ያልሆኑ ጉዳዬችን ዘርዝሮ ተከሳሹን ራሱን ጥፋተኛ ነኝ ማስባል ተከሳሾችን ራሳቸውን አንዲወነጅሉ ማድረግ ሲሆን ያም ሆኖ ተከሳሾች ጥፋተኛ ነን አንዲሉ የተገደዱባቸው እና ለፍርድ ቤት የቀረቡትን የማስረጃነት ሰነዶች ለአብነት አንይ ፡፡
- “የዞን ዘጠኝ የስም ስያሜ ስህተት ነው ፡፡ ምክንያቱም ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውጪ የሚገኝ ማለውን የኢትዬጲያ ህዘብ እስረኛ ነው በማለት ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ታራሚዎች ጋር ማነጻጸሬ ጥፋቴ ነው”
- “የተቃዋሚ ፓርቲዎችን አላማ በማስተዋወቅ ህዝቡ በምርጫ 2007 ኢህአዴግን አንዳይመርጥ መቀስቀሳችን ጥፋት ነው
- ህገ መንግስቱ ይከበር የሚል ከህዳር 27-29 2005 ድረስ በተደረገው ዘመቻ ህገ መንግስቱ ተከብሮ እያለ ህገ መንግስቱ ይከበር በማለቴ ጥፋተኛ ነኝ”
- “የትራንስፓርት ችግር በአዲስ አበባ የሚለው ጽሁፍ ዞን9 ጦማር ላይ እንዲጻፍ በማድረጌ ጥፋተኛ ነኝ”
- “የጸረ ሽብር አዋጅ የኢትዬጲያ መንግስት ሆነ ብሎ ሰዎችን ለማጥቃት ፈልጎ ያወጣው ህግ መሆኑን ለአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ለመጡት የፓርላማ አባላት መረጃ በመስጠቴ ጥፋተኛ ነኝ፡፡”
- “የኬንያ ነጻነት እስከ ምርጫ ድረስ የሚል ጽሁፍ በዞን9 ጦማር ላይ በመጻፌ ጥፋተኛ ነኝ፡፡”
- ““Freedom of expression” የሚል ፌልም አዘጋጅቼ ለስራዬ የተከፈለኝን ክፍያ በባንክ በኩል ባለመላኩ ምክንያት መንግሰት ሊያገኝ የሚገባውን የአገልግሎት ክፍያ ባለመከፈሉ ጥፋተኛ ነኝ”
- “እስክንድር ነጋ ፣ ርእዮት አለሙ መ ውብሸት ታዬ አንዷለም አራጌ እና በቀለ ገርባ የተባሉ እስረኞችን ለማስፈታት ሰላማዊ ሰልፎች ላይ እና ድረ ገፅ ተሳትፎ በማድረጌ ጥፋተኛ ነኝ”
እነዚህን ጥፋቶች ነው ተከሳሾች በሶስት ወር የማእከላዊ ምርመራ ከብዙ ማሰቃየት በኋላ አንዲፈርሙ የተደረጉት፡፡ ይህንን መርምሮ ብይን ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ይዟል፡፡
“ስልካቸው”
ሌላው ተከሳሾች ላይ በማስረጃነት የቀረበው የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት በሽብር ህጉ አንቀጽ 652/2001 አም አንቀጽ 14 መሰረት ‘በተለያዬ ድረገፆች የኢትዬጲያን ገጽታ ለሚያበላሹ ሃሳቦችን በመሰንዘር እና በኢትዬጲያ ውስጥ የሽብር ተግባር የመፈጸም አንቅስቃሴ ላይ ናቸው ያላቸው ተከሳሾች ላይ የላከው ማስረጃ ነው፡፡ በአጭሩ ተጠናቀረ የተባለው ማስረጃ የተከሳሾቹን ሽብርተኛነት ድርጊት ያሳያል ተብሎ የቀረበ ሲሆን ሰነዱ ከግል ቤተሰባዊ ስልክ ልውውጦች እስከ የጓደኝነት ቀልዶች ድረስ ይዟል፡፡ በትንሹ ብንጠቅስ
“በ10/09/2005 አም የቃሊቲ ትዊተር ቻት ( Kality twitter chat ) አምስት ሰአት አንደሚጀመር እና አራት ኪሎ ካፌ ውስጥ እንዳለ የቡድኑ ጸሃፊ በፍቃዱ ሃይሉ ለዘላለም ክብረት ገልጾለት ዘላለምም ወደአራት ኪሎ ለመሄድ ተስማምቷል”
“በ01/05.2006 ሰሞኑን የማህበራዊ ድህረ ገጾች ላይረ ሲወጡ የነበሩ ጽሁፎች በጣም አከራካሪ ስለሆኑ በዚህ ዙሪያ ፎርቹን ጋዜጣ ላይ የሚወጣ ጽሁፍ እያዘጋጀ ስለሆነቃለ መጠይቅ ሊያደርገው ስለፈለገ ይመቸው አንደሆነ ተስፋለም ወልደየስ የቡድኑ አባል ለነፍቃዱ ሃይሉ የቡድኑ ጸሃፊ ገልጾለት በፍቃዱ ሃይሉም ቀደም ብለው በ6 ሰአት መገናኘት አንደሚችሉ ገልጾለታል”
እነዚህና መሰል የተከሳሾቹን የስልክ ንግግሮች ያለ ፍርድ ቤት ፍቃድ ከተጠለፈው ስልካቸው ጋር እነደማስረጃ በመሆን ተከሳሾቹ ላይ ቀርቧል ይህንንም ፍርድ ቤቱ መርምሮ ብይን ይሰጣል ማለት ነው ፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ በሌሎች ሰዎች የተጻፉ እና ኮምፒውተር ላይ የተቀመጡ ጽሁፎች ተከሳሾች በልጅነታቸው የጻፉት የትምህርት ቤት ግጥሞች አለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ የጻፏቸው ፕሮፓዛሎች ሰነዶችም ማስረጃ ተብለው ለፍርድ ቤቱ ቀርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ይህንን መርምሮ ለሰኞ ብይን ይሰጣል፡፡
Source: Zone9

No comments: