ዝክረ መለስ ሙት ዓመት /እውነት የት ነው ያለችው?/
አይደለም የአንዲት መጠነ ሰፊ ቁጥር ያላቸው ቋንቋዎች የሚነገሩባት፣ ልዩ ልዩ ባህሎችና ወጎች የሚከወኑባት፣ በርካታ የእምነት ስርዓቶች የሚራመዱባት ሰፊ አገር ህዝብ ቀርቶ በአንድ ቤተሰብ ውስጥም ተመሳሳይ የሆነ ፖለቲካዊ አመለካከትና አቋም፣ ማህበራዊ እይታና የርዕዮተ ዓለም /ideology/ መነፅር ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በዓለም ላይ ከሚኖረው ቁጥሩ ከሰባት ቢሊዮን በላይ ህዝብ መካከል ሁለት አንድ አይነት ስብዕና /personality/ ያላቸው ሰዎች አይገኙም፡፡ ይህ ፍፁም አምሳያ የሌለው ስብዕና ዋናው የአስተሳሰብ መሰረትና የአቅጣጫ መዘውር ነው፡፡ በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደነብር ዝንጉርጉር፣ እንደለማኝ እህል በየአይነቱ፣ እንደተነቀሰ ድድ ጉራማይሌ፣ እንደጥንታዊ ባቢሎናዊያን ቋንቋችን ለየቅል፣ የጣቢያ መፈለጊያው እንደተበላሸ አሮጌ ራዲዮ ጣቢያዎች ዝብርቅርቅ፣ እንደቀስተ ደመና ሽብርቅርቅ… ያልን ብንሆን አያስደንቅም፡፡ ነገር ግን ሁላችንንም አንድ በሚያደርግ የጋራ ጥቅም የሆነ አገራዊ ጉዳይ ላይ የወታደር ልብስ ስንሆን፣ እንደሰንደቃችን ቀለም ስንለያይ ከማስገረም አልፎ ግራ የሚያጋባ፣ የሚያምታታ፣ የመዶሻ ያክል ራስ የሚመታና ተስፋ ወደ መቁረጥ ጎዳና የሚመራ ጉዳይ ነው፡፡
ሰዎች በወተት ነጭነት ላይ የተለያዩ አቋሞችን ሊይዙ ይችላሉን?
ይህንን ለማለት ያነሳሱኝ የአምባገነኑን መለስ ዜናዊ ህልፈት ተከትሎ የታዩት ያልተጠበቁ አስደንጋጭ ክስተቶች ናቸው፡፡ የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ አቋሞቻቸውን ማንፀባረቅ የጀመሩት መለስ ሙቷል ተብሎ በዋሽቶ አይደክሜው ኢቲቪ በይፋ ከመነገሩ በፊት የማረፉ ጭምጭምታ በሰፊው በሚናፈስበት ወቅት ነበር፡፡
እናም መለስ ዜናዊ አበበ ገላው የሚባል የነፃነት ቡዳ ዋሽንግትን ዲሲ ውስጥ በልቶት ቤልጀም ብራሰልስ ውስጥ 360,000 ዪሮ ማለትም ወደ 10 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ገደማ ተከፍሎለት በህክምና ላይ መሆኑ በተለያዩ ሚዲያዎች በሚነገርበት ወቅት ህዝቡ አርፏል እያለ በየስራ ቦታው፣ በየካፌው፣ በየመሸታ ቤቱ፣ በየጫት ቤቱ፣ በየታክሲው ውስጥ… ባጠቃላይ በሁሉም ቦታ ወሬውን በሰፊው ያነቡገው ስለነበር ከራሴ ጥቂት የቤተሰብ አባላትና የቅርብ ጓደኞቼ ጀምሮ ብዙ ሰዎች መለስ ከሞተ ኢትዮጵያም አብራ እንደምትሞት ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ሙታ ከተቀበረች 21 ዓመታት እንዳለፏት ዘንግተውት ማለት ነው፡፡
አብዛኞቹ ኢትዮጵያ አብራ ትሞታለች ለማለታቸው የሚያቀርቡት ዋና ምክንያት ወያኔ-ኢህአዴግ ውስጥ የመለስን ያክል ፖለቲካ አዋቂና ብልህ አባል ስለሌለ የሚተካው አይኖርም ከዚያም ኢትዮጵያ ከዘመነ መሳፍንት ጊዜው በከፋ ሁኔታ ትበታተናለች የሚል ነው፡፡ ይህ እንግዲህ መለስን በአውንታዊ ጎኑ ከማየት በዘለለ፣ በግለሰብነቱ ከመቀበል ባለፈ አምልኮተ ጣኦት የሚንፀባረቅበት አስተያየት ይመስላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጥቂቶቹ መለስን በመጠኑ በአሉታዊ መልኩ ያይውትና የእሱን ቦታ ለመያዝ በወያኔ-ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች መካከል የስልጣን ሽኩቻ ስለሚኖር አገሪቱ ደም በደም ሆና እንደምትበጣጠስ ያስቀምጣሉ፡፡ አያችሁ በሁለቱም ጎራዎች ከተሰለፉት ማለትም ሟቹን አምባገነን ገዥ በአውንታዊም ሆነ በአሉታዊ መነፅር ከሚመለከቱት ሰዎች የፈለቀው አስተያት መደምደሚያ መበታተንና መበጣጠስ መሆኑን? እስኪ ነገሩን ቆም ብላችሁ ባልተበረዘ ንፁህ ህሊና ተመልከቱት?
አምባገነኑ መለስ ነው እንዴ ሙጫ ሆኖ የኢትዮጵያን ብሄርና ብሄረሰቦች እርስበርስ አጣብቆ በማያያዝ እስካሁን ያቆያቸው? ፅንፈኛ ዘረኛው መለስ ነው እንዴ ኢተዮጵያ የተባለችውን የሳር ክዳን ጎጆ ዋልታና ማገር ሆኖ ዘምሞ በመውደቅ ከመፈራረስ የታደጋት? ፊውዳሉ መለስ ነውን ኢትዮጵያ በተባለችው ቀፎ ውስጥ ያሉትን ከሰማንያ ሚሊዮን በላይ ንቦች አውራ ሆኖ ከመበታተን ያዳናቸው? ትምክህተኛው መለስ ነው እንዴ አውሎ ነፋስና ወጀብ ኃይለኛ ማዕበል አስነስቶ በሚያናውጠው ሰፊና ጥልቅ ውቅያኖስ እየተጓዘች ላለችው ከሰማንያ ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያሳፈረች መርከብ መልህቋ? ደም መጣጩ መለስ ነው እንዴ ከሰማንያ ሚሊዮን በላይ ወፎች መጠለያ በመሆን ተንዘርፍፎ የቆመው ግዙፉ ዋርካ?
እስኪ ይኸው አሁን ሙጫው በዝናብ ታጥቦ ደረቀ፤ ዋልታና ማገሩ ነቅዞ ተሰባብሮ ወደቀ፤ ቀፎው በስብሶ ፈራረሰ፤ መልህቁ እንደበረዶ ቀልጦ ውሃ ሆነ፡፡ ምነው ኢትዮጵያ አልተበታተነችም እሳ? ታሪክ ይፍረድ! ታሪክ ይፍረድ! ከዚህ ሌላ ምን እላለሁ…
እንዴውም እኮ የአንድ ብሄር ፖለቲካ አራማጁ መለስ ነው ብሄርና ብሄረሰቦችን እርስበርሳቸው ያጣበቃቸውን ፍቅር የተባለ ሙጫ ጥላቻ የተባለ መርዝ የረጨበት፤ አንድነት የተባለውን ፍንክች የማይል ሙጫ ዘረኝነት የተባለ አሲድ ያፈሰሰበት፤ ህብረት የተባለውን የማቆራኛ አይላሌ ገመድ በጠባብ ብሄርተኝነት ማጭድ የጎማመደው፡፡ መለስ እኮ ነው ምስጥ ሆኖ ኢትዮጵያ የተባለችውን የሳር ጎጆ ግድግዳ በመብላትና ምሰሶዋን እንደነቀዝ በመቦርቦር ያዘመማት፤ ሻርክ ሆኖ መርከቧን በመገልበጥ ያሰጠማት፤ የኩበት ጭስ ሆኖ ንቦችን የበተናቸው፤ ወፎችን በጅምላ ጎሊያድ አድርጎ ወደ መጠለያቸው ዛፍ በዳዊት ወንጭፍ ድንጋይ እየወረወረ ለሞትና ለስደት የዳረጋቸው፡፡ ለማንኛውም ታሪክ ይፍረድ!
አሁን ደግሞ የኢትዮጵያን ህዝብ ፈረስ አድርጎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የተባለ ኮርቻ ጭኖ፣ ፓርላማ የተባለ ግላስ አልብሶ፣ ካድሬ የተባለውን እርካብ በእግሮቹ ረግጦ እየኮረኮረ፣ ፍርድ ቤት የተባለውን ልጓም እየሳበ፣ ለምዕራባዊያን ፀሃይ መከላከያ ምርጫ ቦርድ የተባለውን የውሸት ዲሞክራሲ ባርኔጣ ከጭንቅላቱ ላይ ደፍቶ፣ ጦር ኃይሎች የተባለውን ረጅም አለንጋ በእጁ ጨብጦ ጆሮ ጆሮውን እየጠበሰ ለ21 ዓመታት የጋለበው አደገኛ የፖለቲካ ፈረስ ጉግስ ተጫዋቹ፣ “ሙጫው፣ ዋልታና ማገሩ፣ የንቦች ቀፎና መልህቁ” ገዥያችን መለስ ዜናዊ ሞተ ተብሎ በይፋ ከታወጀ በኋላ የነበሩትን ያልተጠበቁ ክስተቶችን በጥቂቱ ላንሳ፡፡ እስኪ ከሚዲያዎች አህዱ ብዬ ልጀምር፡፡
የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ ፋና ኤፍ.ኤም ጣቢያዎች የለየላቸው ወናፎች፣ የውሸት ወጀብ አውሎ ነፋሶች፣ የቅጥፈትና የድርቅና ማዕበሎች መሆናቸውን አገር ያወቀው ፀሀይ የሞቀው ዓለምን የሰቀጠጠው ጉዳይ በመሆኑ ስለእነዚህ ዓይን አውጣ ልማታዊ ቀጣፊዎች ማንሳት በከንቱ ጊዜ ማጥፋት ነው፡፡ የግል የተባሉትን ኤፍ.ኤሞችና የህትመት ሚዲያዎች /በተለይም ጋዜጦች/ ጉዳይ ግን ከብዙ በጥቂቱ ልናገር፡፡
ሸገር ኤፍ.ኤም በተለይም ደግሞ ጋዜጠኛ እሸቴ አሰፋ መለስን በሁሉም ነገር የመጀመሪያ የመጀመሪያ፣ ካሁን በፊት ከነበሩት መሪዎች ሁሉ አንደኛ፣ ዕንቁ፣ የነፃነትና የብልፅግና ጮራ ሆኖ በኢትዮጵያ አድማስ ላይ የፈነጠቀ፣ የአዲስ አበባ ህዝብ በጠቅላላ ንቅንቀ ብሎ ወደ ቦሌ አየር ማረፊያና ለረጅም ዘመናት የግፈኞች መመሸጊያ ወደ ሆነው ታላቁ ቤተ መንግስት በመሄድ ከደሙ ከፍሎ ከውስጡ ፈልቅቆ ያለቀሰለት እንደሆነ በተባው ብዕሩና በሰለለ አንደበቱ በተደጋጋሚ ሲያሞካሸው ነበር፡፡ አይ እሸቴ አሰፋ! በቅዳሜው የመቆያ ፕሮግራሙ በዓለም በተለይም በአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ላይ ዘወትር በሚመዝዘው የሰላ የብዕር ሰይፍ እውነተኛ ጋዜጠኛ፣ እውነተኛ ፀሃፊ፣ ሰባዊነት የሚሰማው እውነተኛ የአገርና የሰው ዘር ተቆርቋሪ መስሎኝ ነበር፡፡ ለካስ ውሸታምና ፈሪ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ምን አለ እንደሞያ አጋሮቹ እስክንድር ነጋና እርዕዮት አለሙ እውነቱን ተናግሮ ከመሸበት ቢያድር፡፡ መታሰር እንደጨው አያሟሟ፡፡ ልክ እንደተመስገን ደሳለኝ እውነት እውነቱን ፅፎ ስራ ፈትቶ ነጋ ጠባ በመመላለስ “ፍርድ ቤት” ቢገተር፡፡ ሌላው ይቅርና ለእውነት ሲባልም እኮ ህይወትን የሚያክል ታላቅ ዋጋ ይከፈላል፡፡
ሌላው የኤፍ.ኤም ጣቢያ ደግሞ “የጋዜጠኛ” ሚሚ ስብሃቱው ዛሚ ነው በእርግጥ ሚሚ ስብሃቱ አንዳንዴ ልብ ብሎ ላዳመጣት በህዝብ እየተሰማ ያለ ሚዲያ ላይ ሆና የምትናገር ጋዜጠኛ ሳትሆን ፓርላማ ውስጥ ሆኖ ሲናገር እሱን ራሱን ሟቹን ሰውዬ ነው የምትመስለው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ እንደተቃዋሚም ያደርጋትና በዚህ የወያኔ-ኢህአዴግ ፈረስ ሆኖ ጀርባው የተገጠበ ህዝብ ላይ ታላግጥበታለች፡፡ እናም ድሮውንም ቢሆን ከዝንብ ማር አንጠብቅም፡፡ ኧረ ዛሬ ዛሬማ እንዴውም እንኳን ዝንቦች ወያኔ-ኢህአዴግ ንብ ነኝ ካለ ወዲህ ንቦችም ማር መስራት አቁመው በቀፏቸው ውስጥ ሬት ማከማቸት ጀምረዋል አሉ፡፡
“ለጋዜጠኛ” ሚሚ ስብሃቱ አንዲት ጠቃሚ ምክር ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡ እግረ መንገዴን ሳልረሳ “ለጋዜጠኛ” ሳምሶን ማሞም ጭምር፡፡
ሚሚ ስብሃቱና ሳምሶን ማሞ! ለሞያችሁ ተገዥ ሆናችሁ እውነቱን በመናገር እንዳትመሰክሩና ለደሃው ጭቁን ወገናችሁ ሳይሆን ለአምባገነን ገዥዎች ጥብቅና እንድትቆሙ ያደረጋችሁ በጭንቅላታችሁ ውስጥ ከመጠን በላይ የተከማቸው ጮማ ነው፡፡ ስለሆነም እባካችሁን ወገኖቼ አዲስ ዘመን ጋዜጣን ትታችሁ የተለያዩ መፅሀፍትን በማንበብ የጭንቅላታችሁን ጮማ አቅልጡት፡፡ ይህን ካደረጋችሁ በኋላ ምናልባት ለሞያችሁ ስነ-ምግባር በጥቂቱም ቢሆን ትገዙ ይሆናል የሚል ተስፋ በትንሹም ቢሆን አለኝ፡፡
እነ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ደግሞ የግል የሚል ሀሰተኛ ጭምብል ያጠለቁ፣ ለምድ ደርበው ከበጎች መሃል የቆሙ የቀበሮ ባህታዊያን መሆናቸው ያኔ በአምባገነኑ መለስ ዜና እረፍት ሰሞን በውል ተለይቶ ታወቀ፡፡ ሁሉም የህትመት ሚዲያዎች ለማለት በሚያስችል ሁኔታ በእያንዳንዱ ገፃቸው የመለስን ልዩ ልዩ ምስሎች ይዘው ከጋዜጣነት ወደ ፎቶ አልበምነት የተቀየሩ ሲሆን መለስ በህይወት እያለ ለፈፀመው ጥቁር ታሪክ ቅንጣት ታክል እውነት አልፃፉም፡፡ በተለይ አዲስ አድማስ ከተቃውሞው እጅግ በጣም እየተለሳለሰ መጥቶ በአዲስ ዘመን ሳንባ ለመተንፈስ ተቃርቦ ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ የእኔ ትዝብት ብቻ አይደለም ብዙዎቹ የሚጋሩት እንጂ፡፡ እንዴውም ስለ ዚያን ሰሞኑ የግል የተባሉትን የህትመት ሚዲያዎች ሁኔታ ለአንድ ጓደኛዬ በስልክ ሳጫውተው “አንተ አጉል የዋህ አትሁን የግል ጋዜጦችማ እኮ ከመለስ ጋር አብረው ሞተው ተቀበሩ፡፡” ብሎኛል፡፡
ፈረስ ሆኖ ለ21 ዓመታት ጀርባው ተገጣጥቦ እስኪተላ ሲጋለብ ከኖረውና አሁንም እየተጋለበ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ጥቂቱ ማቅ አጥልቆ ደረቱን እየደቃ ሲያለቅስ ታይቷል፡፡ ታድያ ወያኔ-ኢህአዴግ ይህንን ጥቂት የማህበረሰብ ክፍል የኢትዮጵያ ህዝብ በጠቅላላ እያለ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለራሱ ለህዝቡ ከመግለፁ ባሻገር ለ21 ዓመታት አፉን ከፍቶ ባዶውን የቆየውን የፖለቲካ ጎተራ በመጠኑም ቢሆን ሞልቶበታል፡፡ ግድግዳውን ምስጥ በልቶት ወደ ጎን የዘመመውን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አገዳ ጎጆ እንደባላ ተጠቅሞ በማስደገፍ ለጊዜውም ቢሆን አቃንቶበታል፡፡ ነገር ግን እርግጠኛ ነኝ የሰውዬው ሞት ያለስቆጨው ሰልፍ እንዲወጣ ቢፈቀድ አዲስ አበባ በደራሽ የህዝብ ማዕበል እንደምትጥለቀለቅ አያጠራጥርም፡፡ ለዚህ ደግሞ የ1997 ዓ.ምን በተከታታይ የተደረጉትን የወያኔ-ኢህአዴግንና የቅንጅትን የሚያዚያ ሰልፎች በነቃሽነት ይጠቅሷል፡፡
ለማንኛውም በጥቂት ሰዎች ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን በጅምላ ለጨቋኝና አምባገነን ገዥያቸው ያለቀሱ የመጀመሪያዎቹ ቂል ህዝቦች ተብለን የዓለም ሁሉ መሳቂያና መሳለቂያ ሆነናል፡፡ ደግሞ እኮ አንዳንዶቻችንማ ስናለቅስ ወላጅ እናታችን የሞተችብን አሊያም የምናፌዝ ነው የምንመስለው፡፡ ከቤተ መንግስቱ አጥር አካባቢ በሰዎች ተደግፋ ቁማ “ሰው እንደዚህ አንጀቱ በእጥፉ ይቆረጣል!” እያለች ስትነፋረቅ እንደታየችው አንዲት ልጅ እግር ወጣት ሴት፡፡
ጭቆና እና ረገጣ ናፍቆን የምናለቅስ የምንመስልም ነበርን፡፡
ግን እኛ እስከ መቼ ነው ከነፈሰው ጋር አብረን ስንነፍስ የምንኖረው? መቼ ነው በራሳችን እምነት ፀንተን የምነቆመው? መቼ ነው እሳትን ከውሃ በትክክል ለይተን ማወቅ የምንጀምረው? መቼ ነው ያጠለቅነውን የፍርሃት ሸማ አውልቀን ጥለን ሃሳባችንን ሳንሸማቀቅ የምንገልፀውና በውስጣችን የተቀበረውን እውነት በድፍረት ፈንቅለን የምናወጣው?
በ1997 ዓ.ም እኮ ነው አደባባይ ወጥተን “መለስ ሌባ!” ባልንበት አንደበታችን ተመልሰን “ጀግና አይሞትም!” ስንል የተደመጥንበት፡፡ ድንጋይ በወረወሩ እጆቻችን እኮ ነው ሻማ ጨብጠን ያበራንባቸው፡፡ የህፃናትና ወጣቶቻችን ደም ሲፈስስ በተመለከትንባቸው እይኖቻችን እኮ ነው ያነባንባቸው፡፡ ይህን ስል በመለስ ሞት ተደስተን ከበሮ እንደልቅ ማለቴ አይደለም፡፡ ይህን ባህላችንም አይፈቅደውም፡፡ ከቤታችን አርፈን በተቀመጥን ብዬ እንጂ፡፡ እንዴውም እኔ 21 አመት ሙሉ ሲፈፅመው በኖረው ግፍ ንስሃ ሳይገባ በመሞቱ በእጅጉ አዝኘለታለሁ፡፡ ነገር ግን ከለቅሶው አልሄድኩም፡፡ በወቅቱ በእሱ መሞት ኢትዮጵያ ምንም ያጣችው ነገር አንደሌላትም ተሰምቶኛል፡፡ አሁንም አንዲሁ፡፡ ይህንን ፅሁፍ ስታነብቡ የሞተ ሰው እንዴት ትወቅሳለህ ልትሉኝ የምትችሉ ትኖራላችሁ፡፡ እንደእኔ እንደእኔ ግን አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ገና አልሞተም፡፡ እሱ ሞተ የሚባለው በደም እያቆረበ ያቋቋመው ስርወ-መንግስቱ ወድቆ እንደሸክላ እምሽክ ድቅቅ ሲል ነው፡፡ ወያኔ-ኢህአዴግ የጥንብ አንሳዎችና የቁራዎች መስፈሪያ የሆነ ግዙፍ ዛፍ ነው አሁን ዛፉ ከአድማስ በወረደ ያልታሰበ መብረቅ ተመትቶ በመንደድ በቁሙ ደረቀ እንጂ ከስሩ ተገርስሶ ከአፈሩ አልተደባለቀም፡፡ ደግሞ አይደለም አሁን ገና ከእኔ በኋላ በሚመጡት ህልቆ መሳፍርት ትውልዶች ለዘመናት ሲወቀስና ሲነቀስ ይኖራሉ፡፡ /በተለይ ያች አገር የመገንጠሏ ነገር፣ የባህር በሯ ጉዳይ… መች ትረሳና፡፡/ እንዲህ እንዲሆን ያደረገው ደግሞ ራሱ መለስ ነው፡፡ እሱስ ቢሆን ያለፉ ነገስታትን አፅም እየፈነቀለ በእግሮቹ ይረግጥ አልነበረም እንዴ፡፡ የኋላ ኋላ የእጅ አይቀር፡፡
የህብረተሰቡ ዋና መነጋገሪያ አጀንዳ ሆነው የከረሙት ደግሞ “አርቲስቶች” ናቸው፡፡ በእኔ በኩል ምንም የተመለከትኩት አዲስ ነገር የለም፡፡ ሰራዊት ፍቅሬና ተከታዮቹ የጥበብን የሐሰት ካባ የደረቡ ለጥቅም ያደሩ ሆዳም ነጋዴዎች እንጂ ትክክለኛ አርቲስቶች አለመሆናቸውን ከተረዳሁ አያሌ ዘመናት ነጉደዋልና፡፡ ምክንያቱም እውነተኛ የኪነ-ጥበብ ሰው ማለት ራሱን ሻማ አድርጎ በጥበብ እሳት በመለኮስ በአምባገነኖች የግፍ አገዛዝ ጥቅጥቅ ጨለማ ውስጥ ላለ ሰፊ ህዝብ ብርሃን የሚፈነጥቅና ፈረስ አድርገው እንዳሻቸው እየጋለቡት የሚገኙትን አደገኛ የሆነ የዘር ፖለቲካ ጉግስ የሚጫወቱትን የብዕር ሰይፍ አንስቶ የሚፋለም እንጂ ተገባብጦ ከተላው የፈረሱ ጀርባ ላይ ተፈናጥጦ ተጨማሪ ሸክም የሚሆን አይደለም፡፡ ትክክለኛ የጥበብ ሰው በአፉ ጨው አይሟሟም፡፡ እውነቱን እውነት ሀሰቱን ሀሰት ይላል እንጂ ፈርቶ ሃሰቱን እውነት በማለት አይናገረም፡፡ ብቻ ግን አሁንም ታሪክ ይፍረድ!
የእውነት ከሆነ አትሌቶችም በመለስ ሞት ልባቸው እንደተሰበረ ሲናገሩና ፊታቸው በእምባ ሲታጠብ ታይተዋል፡፡ ማዘንም፣ ማልቀስም መብታቸው ነው፡፡ ነገር ግን በ80 ሚሊዮን ህዝብ ላይ ጊዜ ተመቸን ብለው አፋቸውን አንዳሻቸው የመክፈት ቅንጣት ታክል መብት የላቸውም፡፡ መለስን የሚተካው መሪ ለዘላለሙ እንደማይኖርና ይህንን ፍካሬ ኢየሱሳዊ ንግግሩን ፍፃሜ ወደ ፊት በዓይኖቻችን እንደምናየው አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ ትንሽ እንኳን ቅር ሳይለው አፉን ሞልቶ ተናግሯል፡፡ ኃይሌ ህፃናትን ንቋል! ኃይሌ እኛን ወጣቶችን አጣጥሏል! ኃይሌ ጎልማሶችን /ፖለቲከኞችን፣ ምሁራንን…/ አበሻቅጧል! ኃይሌ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ አንኳስሷል! በእውነት ይህንን ህሊና የሚያደማ ንግግር ከኃይሌ አንደበት አልጠብቅም ነበር፡፡ ለካስ ሟቹ ሰውዬ ራሱ እንደተናገረው እውነትም እግር ጭንቅላት አይሆንም፡፡
በተጨማሪም አትሌት ኃይሌ ጎዳና ላይ በክላሽን ኮቭ ተጨፍጭፈው ለተረፈረፉት ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ ለምንስ ልክ እንደአሁኑ ባደባባይ ሲያለቅስ አልታየም፡፡ ለኃይሌ ታላቅ ክብርና የጀግና ሞገስን በመሸለም ያጎናፀፈው እኮ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ የህወሓት ስርወ መንግስት አይደለም፡፡ እነኛ በአዲስ አበባ ስቴዲዬም የተደረጉ የህዝብ ማዕበሎች ከመቸው ተረሱና ነው ወደ ዘለፋ የተገባው፡፡ አይ ኃይሌ! ደግሞ እኮ ይህንን የድንጋይ ዘመን አስተሳሰቡን ሳይቀይር የኢትዮጵያ ህዝብ መሪ የመሆን ምኞት አንዳለው ሲናገር መደመጡ ነው እጅግ የሚገርመው፡፡ ኃይሌ ልክ እንደሰራዊት ፍቅሬ ታዋቂነት አዋቂነት ማለት አንደሆነ ደምድሟል ማለት ነው፡፡
ሌላው አዲስ ክስተት ደግሞ አዲስ አበባ በመለስ ፎቶግራፎች፣ ባነሮችና ቲሸርቶች ደራሽ ጎርፍ መጥለቅለቋ ነው፡፡ ይህ ለነጋዴዎች አጋጣሚ የፈጠረው ጥሩ የገቢ ምንጭ ቢሆንም ለሟቹ መለስ ምን ዓይነት ጥቅም እንደሚሰጠው ምስጢሩ እስካሁን ድረስ አልተገለፀልኝም፡፡ ይልቅስ እሱን ከምስሉ በበለጠ በአምባገነንነቱና በዘረኝነቱ ድፍን የአዲስ አበባ ህዝብ ከህፃን እስከ አዋቂ ግጥም አድርጎ ስለሚያውቀው ለዚያ የወጣው በርካታ የደሃይቱ ኢትዮጵያ ገንዘብ ዳቦ ተገዝቶበት ቁራሽ አጥተው በየጎዳናው ለወደቁት ጎስቋላ ኢትዮጵያዊያን በስሙ ቢዘከር ሰውዬው በሚከተለው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ህግ መሰረት በሰማይ ደጅ ዋጋ ያሰጠው ነበር፡፡
ደግሞ የወያኔ-ኢህአዴግ አባላት ቲሸርቱን ገዝተው እንዲለብሱ መገደዳቸውን አንዲት ግዳጁ አባል በሆነችው እናቷ ላይ የተጣለ የእህቴ ጓደኛ የሆነች ወጣት ሴት ስታወራ ባጋጣሚ ሰምቻታለሁ፡፡ ልክ የኮሚኩ መሪያችን በረከት ስምኦን “የሁለት ምርጫዎች ወግ” መፅሃፍን እያንዳንዱ ካድሬ ሳይወድ በግድ እንዲገዛ እንደተደረገው አስቂኝ ሁኔታ ማለት ነው፡፡
በተጨማሪም እስከ ቀብር ስነ-ስርዓቱ በነበረው የአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በየቀበሌው በተተከሉት ድንኳኖች ላይ ተገኝቶ በሬዲዮ የሚለቀቀውን ዋሽንት እያዳመጠ ሲያለቅስ ሲያስለቅስ የዋለና ያልዋል የቀበሌ ሰራተኛ ምዝገባ ይካሄድ ነበር አሉ፡፡
በመለስ ሞት ማግስት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የሰጡትን መግለጫ በየጋዜጦች የመጀመሪያ ዓምድ ላይ አንብቤ ነበር፡፡ የአብዛኞቹ ዙሪያውን በስጋት የታጠረና በፍርሃት የተሸበበ ንግግር ነበር፡፡ ምነው እውነትን ሁሉም ፈራት! ምነው ሀቅን ሁሉም ሸሻት! እውነት ግን የታለች? እስኪ አመላክቱኝ የት ቦታ ነው የማገኛት? እውነት! እውነት! እውነት…
ምንም እንኳን ወያኔ-ኢህአዴግ የተቃዋሚ ፓርቲ ድርጅቶችን ለማዳከምና ከነጭራሹ ከስመው ከኢትዮጵያ አፈር እንዲጠፉ ለማድረግ ለ21 ዓመታት ሲተጋበት የቆየበት ግንባር ቀደም ዓላማና ተግባሩ ቢሆንም ለኢትዮጵያ ህዝብ የግፍ አገዛዝ ዓመታት፣ ፈረስ ሆኖ የመጋለብ ጊዚያት መራዘም በተቃዋሚው ጎራ የተሰለፉት ፖለቲከኞችም በተወሰነ መልኩ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ ታግሎ የሚያታግል የተደራጀ ኃይል ካገኘ ካመረቀዘ ጀርባው ላይ የተጫነውን የአምባገነኖች መቀመጫ ኮርቻ አውልቆ ጥሎ ከፈረስነት እንደሰው ልጅ ለመኖር ያለውን ቁርጠኛ አቋምና ፍላጎት በ1997 ዓ.ም አይተውታል፡፡ ነገር ግን ሌላው ቢቀር በመካከላቸው ያለውን ልዩነት አጥብቦ አንድ በመሆን የጋራ ጠላታቸውን በሰላማዊ ሜዳ መፋለም አልቻሉም፡፡ ወያኔ-ኢህአዴግ በበረሃ በጠመንጃ ተዋግቶ ደርግን አሸንፎ ከነቁምጣው በባዶ እግሩ ቤተ መንግስት ገብቶ ለ22 ዓመታት ሲነግስ እነሱ በሰላም ወረዳ ከተማ ውስጥ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ህዝቡን ጋሻ ደጀናቸው አድርገው ማሸነፍ አቃታቸው፡፡ በምርጫ ማሸነፍ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ እስከ መጨረሻው አልህ አስጨራሽ ትግልም ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ዝምብሎ በከንቱ በእስር በስብሶ መበታትን አይደለም፡፡
እንደእኔ እምነት ተቃዋሚዎች በ1997 ዓ.ም ያገኙትን ውጤት ይዘው አንድነታቸውን እንደጠበቁ ፓርላማ ቢገቡና ከመቸውም ጊዜ በላይ ከህዝቡ ጋር እጅና ጓንት ሆነው ተግተው ቢንቀሳቀሱ ኖሮ በ2002 ዓ.ም መርጫም በድጋሜ በዝረራ ማሸነፋቸው አይቀሬ ነበር፡፡ ወያኔ-ኢህአዴግ ያኔም “በማንደም ማን ይነጋሳል” ማለቱ ሳይታለም የተፈታ ቢሆንም ህዝቡ ለሁለተኛ ጊዜ ድምፁን ሲነጠቅ ዝምብሎ ቆሞ ያያል ብየ በጭራሽ አላስብም፡፡ ደግሞ ከዚህ በፊት አስቀምጨዋለሁ ዋናው ቁምነገር በምርጫ ማሸነፍ አይደለም በባሌም በቦሌም ብሎ የምርጫውን ውጤት ማስጠበቁ ነው፡፡ ከፍተኛ ዝግጅት መደረግና ስትራቴጅ መነደፍ ያለበት ለዚህ ነው፡፡ ፈረስ ሆኖ እየተጋለበ የሚገኝ ህዝብ ጋላቢውን እንደማይመርጥማ እኮ አስቀድሞ የታወቀ ነገር ነው፡፡
ያለፈው አልፏል ለወደፊቱ እኛ ኢትዮጵያዊያን በተለይም ደግሞ እኛ በአፍላ የወጣትነት ዘመን የምንገኝ የህብረተሰብ ክፍሎች አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ስልት በወለደው የሰላም አየር በሚነፍስበት የፖለቲካ ጃንጥላ ስር ልንሰባሰብና አንድ ሆነን በመመካከርና በመተባበር ለ22 ዓመታት ከጀርባችን ላይ የተጫነውን የአምባገነኖች ኮርቻ አውልቀን ልንጥለው ይገባናል፡፡ ማንም ሰው የማይጎዳበት ሰላማዊ ትግል /civic disobedience/ ያስፈልጋል፡፡ የጠመንጃ ትግል፣ እርስበርስ መጠፋፋትና ደም መፋሰስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከአምባገነኑ መሪ ጋር ወደ ከርሰ መቃብር መውረድ አለበት፡፡
የአገራችን ኢትዮጵያ ግፍ የተሞላበት አገዛዝ የወለደው ድህነት፣ ኋላ ቀርነትና ውርደት የሚያንገበግበን ከሆንን ካሁኗ ሰዓት ጀምሮ ለእኛ ለጭቁኖች ሳይሆን ለአምባገነኖች ጥብቅና የቆሙ ሬዲዮ ጣቢያዎችን ማድመጥና ጋዜጦችን ማንበብ እናቁም!? ሀሰተኛ የጥበብ ካባ የደረቡ አድር ባይ ሆዳም ነጋዴዎች የሚያወጡዋቸውን ፊልሞችና ሙዚቃዎች ከመግዛት እንቆጠብ!? ወደ ፊልም ቤታቸውም ከመሄድ እንገታ!? ምክንያቱም ዓላማቸው ከእኛ በሚሰበስቡት ገንዘብ እጆቻችንንና እግሮቻችንን ተጠፍረን የምንታሰርባቸውን የባርነት ሰንሰለቶች ለአምባገነኖች ገዝተው መስጠት ነውና፡፡ ብዕርን በጨለማ ክፍል ውስጥ በማሰር የመፃፍ ነፃነትን ለገደበ አምባገነን ገዥ “እሰዬው አበጀህ” ብሎ የወርቅ በዕር የሸለመን የኪነ-ጥበብ ማህበር ውግዝ ከማሪዮስ እንበለው!? ሰላማዊ ትግል ከዚህ ይጀምራል፡፡
ደግነቱ ዘውዱ
ኢትዮጵያ የመፃፍና የመናገር ነፃነት የተንሰራፋባት ታላቅ አገር ትሆናለች!
No comments:
Post a Comment