መለስን ከቀዳሚዎቻቸው’ጋ የማወዳደር ሽቀላ
አቶ መለስ መሞታቸው በኢቴቪ ከተነገረ አንድ ዓመት ነገ ይሞላዋል፡፡ መንግሥት እንደስትራቴጂ በስማቸው (‹‹በሙት መንፈሳቸው››) ማስተዳደር ከጀመረም እንዲሁ አንድ ዓመት፡፡ ይህንን አጋጣሚ በመከተልም ስማቸውን ለማግዘፍ የሚደረገውን ፕሮፓጋንዳ ለመቋቋም የራሴን ድርሻ በዚህ ሳምንት በአጫጭር ማስታወሻዎች ለመወጣት እሞክራለሁ፡፡
የመለስን ‹‹ታላቅነት›› ለማግዘፍ ከሚደረግባቸው ሙከራዎች አንዱ ካለፉ አምባገነኖችጋ ማወዳደር አንዱ ነው፡፡ ይህንን ዘዴ መለስ ራሳቸው በሕይወት እያሉ ጀምረውት ነበር፡፡ ለምሳሌ በጥር ወር 2003 ኮሎምቢያ ዩንቨርስቲ ውስጥ ከተማሪዎችጋ ባደረጉት ቃለምልልስ በአስተዳደራቸው ያመጡትን ዴሞክራሲ ለመግለጽ የተናገሩት ‹ዜጎች ለተገደሉበት ጥይት ወላጆች የጥይት ሒሳብ እንዲከፍሉ የሚጠየቁባት አገር ነበር የተረከብነው› በማለት ነበር፡፡ ይህ በመለስ ይሁንታ 193 ሰዎች በአደባባይ በተገደሉበት አገር የተሳሳተ ምሳሌ ነበር፡፡ ያለፉት ገዢዎች አምባገነንነትም ቢሆን ለመለስ ለዘብተኛ አምባገነንነት መመዘኛ ሊሆን አይችልም፡፡
የሚያሳዝነው… የመለስን አስተዳደር በአምባገነንነቱ ወደር ካልተገኘለት ከደርግጋ በማወዳደር ለማግዘፍ የሚሞክሩት ወደኋላ ርቀው ከንጉሡ ጋር ለማወዳደር ግን አይሞክሩም፡፡ በንጉሡ ጊዜ ተማሪዎች ሲያምፁ የሞተው ሰው ቁጥር 12 ሰው ብቻ ነበር፤ አሁንስ? በንጉሡ ግዜ የነበሩት ትላልቅ ምሁራንን የሚያክሉ ባለሥልጣናት ቦታ አሁን በካድሬዎች ተሞልቷል፡፡ ካድሬዎቹም ከዚያ ዘመን መጥፎውን ብቻ እየመዘዙ የመለስ ማግዘፊያ የማድረግ ሽቀላውን አጧጡፈውታል፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ‹እያንዳንዱ አስተዳደር በራሱ ዘመን መመዘኛ ይመዘናል እንጂ ካለፈው አንፃር መመዘኑ ትክክለኛ አካሄድ አይደለም› ይላሉ፡፡ አዎ፤ ከንቱ ሽቀላ ነው፡፡ የመለስ አስተዳደር ስር የሰደደ፣ ዘመናዊ አምባገነናዊ አስተዳደር ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ የፓርቲው አባላት ሳይቀሩ በአንድ ሰው የሚገዙበት የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት የገነነበት ክፉ አስተዳደር ነበር፡፡
No comments:
Post a Comment