Tuesday, August 27, 2013

የግዳጅ ሰልፉን ለማምከን ታጥቀን እንነሳ!

የግዳጅ ሰልፉን ለማምከን ታጥቀን እንነሳ!

ማክሰኞ ነሐሴ 21/2005

‹‹የሃሰት ፕሮፖጋንዳ መደጋገም የእምነት መብት ጥያቄን ህገወጥ አያደርገውም!››

(ውድ ኮሚቴዎቻችን ለሚኒስትር
መስሪያ ቤቶች ካስገቡት ደብዳቤ ርእስ የተወሰደ)

ለአመታት የህዝቡን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ህገወጥ በሆኑ ተግባራት ላይ መሰማራት የመረጠው መንግስት በግትርነት አቋሙ መግፋትና ከህዝብ ጋር መጋጨቱን ቀጥሎበታል፡፡ ትናንት በህዝብ ዘንድ የሀሰት ቋት ተደርጎ የሚቆጠረው ኢቲቪ እንደዘገበው የፊታችን እሁድ ነሐሴ 26/2005 ‹‹አክራሪነትን›› ለማውገዝ ሰልፍ ይደረጋል ተብሏል፡፡ የሰልፉ አዘጋጅ ተብሎ የተገለጸው ‹‹የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ›› ተብሎ የሚጠራው ተቋም ሲሆን ተቋሙ ‹‹ከሁሉም ሃይማኖት ተመርጠዋል›› ተብለው የተሰባሰቡ ግለሰቦች ጥምረት እንደሆነም ይታወቃል፡፡

በመሰረቱ ህዝበ ሙስሊሙ አክራሪነትን በጽኑ እንደሚያወግዝ እና በፀረ አክራሪነት ትግል ስም በእምነቱ ላይ የተቃጣበትን ጥቃት ግን እስከመጨረሻ እንደሚታገለው በተደጋጋሚ በግልጽ አስረድቷል፡፡ ዛሬ በግፍ እስር የሚገኙት ኮሚቴዎቻችንም ለመንግስት ባስገቧቸው ደብዳቤዎች በማያሻማ ቋንቋ ያስቀመጡት የማይቀየር አቋም ይኸው ነው፡፡ እኛ ‹‹አክራሪነትን ለማውገዝ ይካሄዳል›› የተባለለትን ሰልፍ የምንቃወመው መንግስት አክራሪነትን በመዋጋት ሽፋን ሃይማኖታዊ ጭቆና በንጹሀን ላይ እየፈጸመ በመሆኑ እና ለሁለት አመታት ያለከልካይ ሲያደርስ የነበረው እጅግ ከፍተኛ የህግ ጥሰት ዛሬ ወይንም ነገ የሚያስጠይቀው ሆኖ ሳለ ወንጀሉን ለመሸፋፈን የሚያደርገው የሞት ሽረት ትግል በመሆኑ ነው፡፡

የዚሁ ሰልፍ ዜና በይፋ የተገለጸው ገና ዛሬ ቢሆንም በየቀበሌው ያሉ የመንግስት ካድሬዎች ግን ከቀናት ጀምሮ ከየቀበሌው እየተሰባሰቡ ህዝቡን በግዳጅ የሚያስወጡበትን መንገድ ሲመካከሩ ቆይተዋል፡፡ በየቤቱ በመዞርም ከእያንዳንዱ ቤተሰብ ቢያንስ 3 ሰው መገኘት እንዳለበት ሲያስጠነቅቁ እና ሲዝቱ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ በፊት እንደዘገብነውም የግል ድርጅቶች ሳይቀሩ እንዲገኙ በማስጠንቀቂያ መልክ ትእዛዝ ወርዶ የማስገደድ ዘመቻ ተሰርቶባቸዋል፡፡ 

በግዳጅ ሰልፉ ማታለል የሚፈልጉት ማንን እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ የሰልፉ እውነተኛ አዘጋጅና አስገዳጅ ራሱ መንግስትና ካድሬዎቹ ሆነው ሳለ ‹‹የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰልፍ ጠራ›› ተብሎ በኢቲቪ መዘገቡ ለብዙዎች አሳፋሪ የሚሆንባቸውም ለዚሁ ነው፡፡

በመሰረቱ ሰልፉ መንግስት ያለመለትን ግብ ሊመታ እንደማይችል ሊታወቅ ይገባል፡፡ የግዳጅ ሰልፍ እስካሁንም ሲደረግ ቆይቷል፤ አዲስም አይደለም፡፡ የሚደረገው አዲስ አበባ ላይ ከመሆኑ ውጪ የተለየ ነገርም የለውም፤ ያው የተለመደው የቀበሌ ካድሬዎች ማስፈራሪያና ‹‹አይናችሁን ጨፍናችሁ ተታለሉ›› ጉትጎታ ነው፡፡ በህዝበ ሙስሊሙም ሆነ በሌላው ኢትዮጵያዊ ወገናችን ዘንድ ጥያቄያችን በሚገባ ታውቋል፡፡ የመብት ጥያቄ መሆኑን በተደጋጋሚ በሚያደርጉት ልባዊ ድጋፍ እውቅና ሰጥተዋል፡፡ መንግስት እስካሁን ሙስሊሙን ስጋት አድርጎ ለመሳል ሲያደርገው የነበረው ከልክ ያለፈ ጥረት አንዳችም አመኔታ አላስገኘለትም፡፡

‹‹ጦርነቴ ከአክራሪነት ጋር ነው›› ሲል
የቆየው መንግስት እየገደለ እና እደበደበ ያለው ሰላማዊውን ሙስሊም መሆኑን ያላየ ኢትዮጵያዊ የት አለና? ‹‹ጥቂት አሸባሪዎች ጋር ነው ግብግቡ›› ሲል ቢቆይም ዘመቻው ግን ተራው ሰላማዊ ሙስሊም ላይ መሆኑን ያልተረዳ አካል የት አለና? እያስፈራራ፣ እየደበደበ፣ እየዘረፈ፣ እያሰረ፣ እያሰደደ፣ እየገደለ ያለው ራሱ መንግስት መሆኑን የማያውቅ ኢትየጵያዊ የት አለና? ደጋግመን ስንናገር እንደነበርነው የመብት ጥያቄ ያነሳው ህዝብ ነው በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ! ህዝብ ደግሞ ለፕሮፓጋንዳ አይሸነፍም፤ ምክንያቱም ፕሮፓጋንዳ ራሱ የሚያስፈልገው ህዝቡን ለማሳመን ነው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ ደግሞ የሚፈልገውን ያውቃል፡፡ ዘመቻው ማን ላይ እንደሆነ ይረዳልና ሊታለል አይችልም፡፡ ለዘመናት አብረውን የኖሩት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንም ጥያቄያችንን ተረድተዋል፡፡ 

እየደረሰብን ያለውን በደል አይተዋል፡፡ እናም እነሱም ሊታለሉ አይችሉም፡፡ በዳዩ መንግስት፣ ተበዳዮቹ እኛ መሆናችን ሐቅ ነውና ያለሀሰት ፕሮፓጋንዳ ጋጋታ እንደረፋድ ጸሀይ ግልጽ ብሎ መታየቱ አይቀርም፤ ኢንሻአላህ! ቀላል ህዝባዊ ጥያቄዎችን ከመመለስ ይልቅ ተራራ መቧጠጥ የቀለለው መንግስት የግዳጅ ሰልፍ ልክ እንደከዚህ ቀደሞቹ የከሸፉ ሙከራዎች ባለቤቱን ሀፍረት አከናንቦ ማለፉ የሚቀር አይደለም!

እንደህዝብ የሚፈጸምብንን ከፍተኛ በደል ተቋቁመን በትእግስታችንና ሰለማዊነታችን ጸንተናል፡፡ እንደህዝብም ንጽህናችንን አስመስክረናል፡፡ መንግስት ግን በሚሰራው ወንጀል ከማንም በላይ ራሱን እያጋለጠና ተቀባይነቱን እየሸረሸረ ነው፡፡ በተጨማሪም ህዝበ ሙስሊሙ የጁምአ ተቃውሞውን ላልተወሰነ ጊዜ በማቆም የእፎይታ ጊዜ መስጠቱ ለመንግስት የማሰቢያና የጥሞና እድል ለመስጠት መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ይህ የእፎይታ ግዜ አሁን ከሚታዩ ሁኔታዎች በመነሳት መከለሱ ግዴታ እየሆነ ይመስላል፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ በማንኛውም ወቅት አስፈላጊውን መስዋእትነት እየከፈለና የሰላማዊ ትግል ስልቶችን እየለዋወጠ ለመብቱ የሚያደርገውን ትግል መቀጠል የሚችል ህዝብ ነው፡፡

አዎን! እንደህዝብ ሚሊዮኖች ሆነንና ተባብረን የሀሰት ፕሮፓጋንዳውን በአላህ ፍቃድ ድባቅ እንመታለን! የእሁዱ የመንግስት የግዳጅ ሰልፍ ፕሮፓጋንዳ ያለጥርጥር ይከሽፋል! በጭራሽ አላማውን ሊያሳካም አይችልም! ህዝቡ በዚህ የሀሰት ድግስ ላይ እንዳይካፈል የማድረጉ ርብርብ እንደተጠበቀ ሆኖ ሰልፉ ቢካሄድ እንኳን በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የመዲናይቱን ከተማዎች የሚያጥለቀልቀው የዒድ ህዝባዊ ማእበል በአንድነት ወጥቶና ተቀላቅሎ ትክክለኛ ድምጹን ሊያሰማና በደሉን ሊያሳውቅ የሚችልባቸው ስልቶች ከሌሎች በርካታ አማራጮች ጋር ቀርበው ምክክር እየተደረገባቸው ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ‹‹የሃሰት ፕሮፖጋንዳ መደጋገም የእምነት መብት ጥያቄን ህገወጥ አያደርገውም!›› በሚል ርዕስ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የመንግስትን እኩይ አላማ የማሰናከል ዘመቻ ይካሄዳል፡፡ 

መንግስት የጠራው ሰልፍ በሃገራችን ሰምተን የማናውቀው አዲስ የመጥፎ ታሪክ ጅማሮ በመሆኑ ስለነገዋ ኢትዮጵያ እና ስለነገው ትውልድ ሁሉ የሚጨነቅ ኢትዮጶያዊ ይህንን ጥፋት በመከላከል የበኩሉን ድርሻ የመወጣት ግዴታ እንዳለበትም ማሳሰብ እንወዳለን፡፡ በዘመቻው ላይ መላው ኢትዮጵያዊ እንዲሳተፍ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

በተጨማሪም እያንዳንዱ ሙስሊም በየመንደሩ ሰልፉን አስመልክቶ እየተሰራ ያለውን ህገወጥ ተግባር በማጋለጥና መረጃውን በማዳረስ ከፍተኛ ርብርብ የማድረግ ስራ ላይ መሰማራት በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ሁላችንም እንበርታ!

መረጃዎችን ትንሽ ትልቅ ሳንል እያጣራን ማሰራጨቱ ለትግላችን ከፍተኛ ድጋፍ የሚያደርግ ተግባር ነውና አንዘናጋ! ጊዜው እየሄደ ነው! ጨለማው ጥቅጥቅ ባለ ቁጥር ንጋቱ እየተቃረበ መሆኑን እያሰብን በትግላችን እንበራታ፤ ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለምና!

አላሁ አክበር!

ድምፃችን ይሰማ

No comments: