የአቶ መለስ ገፅታዎች - ከደደቢት እስከ ካምፕዴቪድ ፩
የጉብዝና ወራታቸውን እና የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ለትግሉ የሰውት አቶ መለስ ዜናዊ በአፀደ ስጋ ከተለዩን ድፍን አንድ አመት ሆነ፡፡ አቶ መለስ በህይዎት ዘመናቸው የመሰላቸውን አድርገው ለማንም ወደ ማይቀረው በጊዜ ሄደዋል፡፡ አቶ መለስ የመንግስቱ ሃይለማርያምን ወንበር ተረክበው ከፊተኛቸው ሶስት አመት ዘለግ አድርገው ታላቋን ሃገር ሲያስተዳድሩ እንዳልክ ተብለው፣ የወደዱትን አድርገው፣ በሁሉን አወቅ ልዕለ-ሰብ ተመስለው ነበር፡፡ በኋለኞቹ የመሪነት ዘመናቸው በተለይ የህወሃት/ኢህአዴግ እስትንፋስ፣ የሀገሪቱ ብቸኛ አድራጊ ፈጣሪ፣ ፖሊሲ ቀራጭ፣ ስለሁሉ ተጠያቂ፣የሁሉ ፈቃጂ ከልካይ፣ ከተሜ ገጠሬውን፣ልጅ አዋቂውን፣ሴት ወንዱን፣ ሊጉንም ክንፉንም ሰብሳቢ፣አወያይ፣ መካሪ ዘካሪ ሆነው ነበር፡፡ ከምርጫ 1997 በኋላ ለትንሹም ለትልቁም በየመድረኩ መታየታቸው ስልጣን ጠቅላይነታቸውን ያሳብቅ ነበር፡፡ ሁሉን ጠቅልሎ የመያዙ ነገር አቶመለስን ከሊጡም ከወጡም እንዲሉ በማድረጉ እረፍት ማጣቱ ከህመማቸው ጋር ተደምሮ ሲቀራቸው ወደሞት ሳያጣድፋቸው አልቀረም፡፡
የመለስ ውበቶች!
ተማሪውን መለስ ጠቅላይሚኒስተር መለስ ያደረጋቸው ተምሮ ዶክተር ከመሆን የተለምዶ ጉጉት እና ምኞት አለፍ ብለው ማሰባቸው ነው፡፡ አቶ መለስ በጉብልነት እድሜያቸው እጃቸው የገባውን “ንወር ክበር” የሚያስብለውን የዶክተርነት ሙያ እንደምንም ነገር ቆጥረው ደደቢትን መመኘታቸው ሁሉም ሰው የማያስበው ልዩነታቸው ነው፡፡
ደደቢት ከገቡ በኋላም መልካም የሆነውን የማንበብን እጣፋንታ መምረጣቸው ተናግረው እንዲያምርባቸው ረድቷቸዋል፡፡አንባቢነታቸው በነጮች ሳይቀር የሚመሰከርላቸው አቶ መለስ ይበጃል ያሉት ሃሳባቸው ሶስተኛ ወገንን አሳመነም አላሳመነ፣ አስከፋም አስደሰተም፣ ከመርህ ጋር ተጋጨም አልተጋጨም፣ ትናንት ራሳቸው በአንደበታቸው ከተናገሩት ጋር ገጠመም አልገጠመ ዛሬ ያመኑበትን ብቸኛው መንገድ አድርገው ለማስረዳት አይሰንፉም፡፡ ይሄ ማንነታቸው ጥሩ ነው መጥፎ ወደ ሚለው ዝርዝር ሳይገባ ላመኑበት ነገር ያላቸው ፅናት ግን ውበታቸው ነበር፡፡
ክፉም ይሁን በጎ ላመነበት ነገር እስከመጨረሻው የሚፀና ሰው እንደሚያደንቁ የሚናገሩት የአቶ መለስ ይህ ንግግራቸው ከላይ የተገለፀውን ማንነታቸውን ያመላክታል፡፡ በህልፈታቸው ሰሞን አንድ የቢቢሲ ጋዜጠኛ “ያመኑበትን የሚናገሩ የሚናገሩትን የሚያደርጉ” ሲል ነበር የገለፃቸው፡፡ “የሚናገሩትን የሚያደርጉ” የሚለው ቢያጠያይቅም የሚያምኑበትን የሚናገሩ የሚለው ይገልፃቸዋል፡፡ ለወትሮው ሲያንቆለጳጵሳቸው የነበረው ዘ-ኢኮኖሚስት መፅሄትም በሞቱ ሰሞን “አምባገነንነትን በአለማቀፍ መድረክ ተቀባይ ለማድረግ ሲለፉ የኖሩ መሪ” ሲል ገልጿቸዋል፡፡ ይህ አባባል የመጣው ልማታዊው መንግስቴ በስልጣን ላይ መሰንበትን የሚፈልገው ለልማት ሲል ነው፤ስለዚህ ልማትን እስካመጣ ድረስ ፓርቲየ ስልጣን ላይ ቢባጅም በልማታዊነቱ ህዝቡ ፈልጎ መርጦት በመሆኑ ዲሞክራሲዊ ከመሆን የሚያግደው የለም ብለው ሲሞግቱ በመኖራቸው ነው፡፡ የፈለገ ተአምር ቢሰራም መንግስት ስልጣን ላይ ከሰነበተ አምባገነንነት እንደማያጣው የሚያውቁት ነጮች ደግሞ ለአምባገነን አገዛዛቸው የልማታዊነት ገበር ያለው የይስሙላ ዲሞክራሲ ካባ የሚሰፉ ከንቱ ደካሚ ሙግተኛ ያደርጋጓቸዋል፡፡
መንግስታዊ መንበሩን ከመዘወሩ ጎን ለጎን መማርን መሻታቸውም መልካም ገፅታቸው ነው፡፡ ትምርቱን ቢማሩም ባይማሩም የሰራዊታቸው ክንድ እስካልሰነፈ ድረስ በስልጣን ላይ መቆየት እንደሚችሉ እያወቁ መማር መፈለጋቸው ለእውቀት ያላቸውን ቦታ ያመላክታል፡፡
ፋኖው መለስ
አቶ መለስ በጫካ ትግል ቆይታቸው በጦር ሜዳ ጀብዱ በመሰራት ብዙ አይታወቁም፡፡ እንደውም የጫካው ህወሃት ሂሳብ ሹም የነበሩት አቶ እየሩሳሌም ጌታቸው “ነፍሱን በጨርቅ መቋጠር የሚቀረው” ሲሉ ከመሞት መሰንበት ባይ፣ ነፍሳቸውን ወዳድ እንደ ነበሩ “የሀገር ልጅ” ለተሰኘው የኢሳት ፕሮግራም በአንድ ወቅት ገልፀዋል፡፡ አቶ ኢየሩሳሌም በተቃራኒው ወ/ሮ አዜብን “በተፋፋመ ጦርነት ለመማገድ የማትፈራ ጀግና ነበረች፣ ዘወትር በጦርነቱ ለመሳተፍ ስትፈልግ እሱ ነበር እየለመነ የሚያስቀራት አንዳንዴ ግን እምቢ እያለችው ትሄድ ነበር” ይላሉ፡፡ አቶ መለስ ራሳቸውም በትግሉ መጀመሪያ አመታት በተወሰኑ ግንባሮች ተሳትፌያለሁ ይሉነበር እንጂ በትግሉ ዘመን ሁሉ ከጠላት ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቄ ተዋግቻለሁ፣ በጥይት በሳንጃ ጠላት አርበደብድ ነበር ብለው አያውቁም፡፡
አቶ መለስ ብዙውን የጫካ ህይወታቸውን በፖለቲካው ኮሚሳርያት ክፍል ነበር ያገለገሉት፡፡ ሁሉም ሰው ጦር ሜዳ ወርዶ መዋጋት ላይኖርባቸው ይችላልና አቶ መለስ መድፍ ማገላበጡ ባይሳካላቸው መፅሃፍ አገላብጠው፣ሀልዮት ባይፈጥሩም የነማርክስን ሃልዮት እንደሚመች ደውረው ሰራዊቱን ለአላማ በመፅናት ስም ነፍስን ከምንም እስካለመቁጠር በዘለቀ መሰጠት ህወሃት/ኢህአዴግን አዲስ አበባ እንዲያደርስ አድርገዋል፡፡ ይህ ለህወሃት ትልቅ አበርክቶት ነው፡፡
መትረይስ ከማናገር መውዜር ከመታጠቁ ሰራዊቱን በምስራቃዊ ርእዮት አለም ወደ ማስታጠቁ መዞራቸው ለአቶ መለስ በግልም ብዙ ጠቅሟቸዋል፡፡ ብዙጊዜያቸውን በማንበብ እንዲሳልፉ አድርጓቸዋል፡፡ ማንበባቸው የርእዮት አለም ትጥቃቸውን ከማጥበቁ ባሻገር ማለት የፈለጉትን ንባብ በሳለው ርቱዕ አንደበት አሳምረው እንዲናገሩ፣ ተናግረውም እንዲሰሙ፣በሰራዊቱ ዘንድም ወደር የለሽ ምጡቅ አዋቂ ተደርገው እንዲታሰቡ ረድቷቸዋል፡፡ በሰራዊቱ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት እያደር እያደገ መምጣቱ በእድሜም፣ በችሎታም ላቅ የሚሉዋቸውን እንደነ አረጋይ በርሄ እና ግደይ ዘርአፅዮን አይነት ቀደምት ታጋዮችን አስወግዶ ፊት ለመሆን ትግላቸው ክንዳቸውን አበርቶላቸዋል፡፡
በጫካ ትግሉ ወቅት የወታደሩ ክንፍ በፖለቲካ ኮሚሳሪያቱ ስር ስለነበር የፖለቲካ ኮሚሳርያቱን ቁንጮነት የተቆናጠጡት መለስ በተለይ በኋለኞቹ የትግል ዘመናት የህወሃት ዋና ሰው እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡በጦር ሜዳ ከጦሩ ጋር ወድቀው ተነስተ ከታገሉት የጦሩ ፊትአውራሪዎች በላይ በስልጠና፣ፕሮፖጋንዳ እና ርእዮ-ተአለም ስርፀት ስራ የተካኑት ተናጋሪው መለስ ተፅእኖ መፍጠር ችለው እንደነበር የህወሃትን ትግል የሚዘክሩ ከቅርብ አመታት ወዲህ በብዛት እየታተሙ ያሉ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡
በምስራቅ ምዕራብ መስህብ መዋተት
እንደሃገራችን አቆጣጠር በ 1960ዎቹ መጨረሻ አካባቢ በሃገራችን የነበረው የፖለቲካ ንፋስ በማርክሲስት ሌኒኒዝም ርዕዮት የተቃኘ ስለነበር በዚሁ ዘመን ትግል የጀመረው ህወሃትም ማርክሲዝም ሌኒኒዝምን መመሪያው እንዳደረገ በ1968ቱ ማኒፌስቶው ላይ እንዲህ ሰፍሯል፡ “ማርክሳዊ ሌኒናዊ ሳይንስ የላብ አደር ርዕዮተ-አለም መሆኑን በማመን በአሁኑ ጊዜ የሚካሄደውን አብዮት ከግቡ ሊደርስ የሚችለው ይህንን መመሪያ በማድረግ ብቻ መሆኑን በመገንዘብ .....ወዝ አደሩንና ደሃ ገበሬውን ለማደራጀት በቅድሚያ ማርክሳዊ ሌኒናዊ የሆነ የፖለቲካ ማህበር ያስፈልጋል፡፡”(ገፅ. IX-X) ወደ ሰባዎቹ ሁለተኛ አጋማሽ አካባቢ ደግሞ ትግራይን ነፃ ካወጣሁ በኋላ የአልባኒን አይነት ሶሻሊዝም በነፃይት ትግራይ እመሰርታለሁ ሲል ማሌሊት መመሪያየ ነው እንዳለ እና ማሌሊትን በማቀንቀኑ በኩል ደግሞ አቶ መለስ ቀዳሚ እንደነበሩ “ከሃገር በስተጀርባ” የሚለው የአስራት አብርሃም መፅሃፍ ያነብስባል፡፡
በዚህ ሁኔታ አብዛኛውን የጫካ ቆይታቸውን በምስራቃዊ ፖለቲካ ዘይቤ አድርገው የቆዩት አቶ መለስ አዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ሲታያቸው እና የምስራቃዊው ርዕዮት ሲነኮታኮት አንድ ሆነ፡፡ አዋጭው መንገድ እየነጋለት ካለው ምዕራባዊነት ጋር መመሳሰል መሆኑ የተከሰተላቸው አቶ መለስ እንደፈረጆቹ አቆጣጠር በ1990 ወደ ምእራባዊኑ አውራ ሃገር አሜሪካ ገሰገሱ፡፡ የጉዞዋቸው ዋና አላማ ደርግን ጥለው ለሚመሰርቱት መንግስት ግልፅ የሆነ የአሜሪካ እዳታ ስለሚያስፈልጋቸውና ያንን ለማስተማመን መሆኑን በወቅቱ የአሜሪካ ፀጥታ ምክርቤት ባልደረባ ለነበሩት እና በቅርቡ በሞት የተለዩት ወዳጃቸው ፖል ሄንዝ ባደረጉላቸው ቃለ ምልልስ ገልፀዋል፡፡
በቃለ-ምልልሱ ሄንዝ ለአቶ መለስ በወሳኝ ጥያቄዎችን አቅርቦ ነበር፡፡ የቃለ-ምልልሱ ሙሉቃልም ስለኢትዮጵያ ፖለቲካ ትኩረት በሚያደርጉ ድህረገፆች ላይ ይገኛል፡፡ በሶስት ዙር በተደረው ቃለምልልስ ሄንዝ የአቶ መለስን እና የድርጅታቸው ህወሃትን ምስራቃዊ የፖለቲካ ማንነት ሲጠይቃቸው ድርጅታችን ምስራቃዊነትን አያውቅም፣ ማርክሲስት ሌኒኒስትነትን የሚገልፅ አንዳችም ቅጥያ በድርጅታችን ስም ላይ የለም፤ ምናልባት እኛ በግል ማርክሲዝምን እናምን ይሆናል እንጂ ሲሉ ነበር እንመሰርተዋለን ሲሉት የኖሩትን ማሌሊትን ዶሮ ሳይጮህ እንደ ጴጥሮስ ደጋግመው የካዱት፡፡ ነገሩ ያልጣመው ሄንዝ ደጋግማችሁ ማርክሲስት ነን ትሉ ነበር፣ እንደውም የአልባኒያን ሶሻሊዝም አርአያ ትግራይ ላይ እንደግማለን ትሉ ነበር ሲል ሲሞግታቸው አቶ መለስ እኛ የቻይናንም ሆነ የራሽያን አለያም የአልባኒያን ሶሻሊዝም በህዝባችን ላይ የመጫን እቅድ የለንም ብለው ከእውነታው የማይገጥመውን የበፊቱን ሶሻሊስት አይደለንም ሚለውን አቋማቸውን አጠናክረዋል፡፡
ቃለምልልሱ ከተደረገ ከአንድ አመት በኋላ አዲስ አበባ የገባው ኢህአዴግ ልማታዊ መንግስት ሆንኩ እስካለበት ድህረ ምርጫ 1997 ድረስ ነጭ ካፒታሊዝምን እንደሚከተል አቶ መለስ ደጋግመው ይናገሩ እንደነበር ዳንዲ በሚለው መፅሃፍ ላይ ዶ/ር ነጋሶ ገልፀዋል፡፡ ካፒታዝምን መከተሉ የምእራባዊያንን ዲሞክራሲ ማስፈንን፣ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በመንግስት መዳፍ ከመዘወር ለገበያው ሁኔታ መተውን ስለሚጠይቅ እና ይሄ ደግሞ ውስጠ ማርክሲስት ለሆነው ኢህአዴግ በቀላሉ የማይለመድ መሆኑ ኢህአዴግ አይኑን ሙሉ በሙሉ ከምእራባዊያን ላይ ባያነሳም ቀደምት ምስራቃዊነቱ ከልጓም ስቦት በቅርቡ ወደ ቻይና ጠጋጠጋ ማለት ጀመረ፡፡ መሪው አቶ መለስም ቻይናን ከኢትዮጵያ አልፋ ከአፍሪካ ጋር ወዳጅነቷን እንድታጠብቅ በአፍሪካ መድረክ ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም አፍሪካ-ቻይና ወዳጅነትን እውን አደረጉ፡፡ የወዳጅነቱ ሁኔታ ቻይናን አንዷን ሀገር አግዝፎ አህጉር ከሆነው ከአፍሪካ ጋር መሳ ያደረገ ያጋደለ ወዳጅነት ነው፡፡
የጫካው እና ከተሜው መለስ
አስራ ሰባት አመታትን በጫካ ትግል ያሳለፈው ህወሃት/ኢህአዴግ አዲስ አበባ ከገባ በኋላም የሚያሳየው የአመራር ዘይቤ ከጫካው አመራር ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ አቶ አስገደን ጨምሮ ከድል በኋላ ኢህአዴግን የተለዩ የቀድሞ ታጋዮች በፅሁፍም ሆነ በሚሰጧቸው ቃለ-ምልልሶች ይገልፃሉ፡፡ ይህ መመሳሰል በትጥቅ ትግሉ ወቅት በተለይ በመጨረሻዎቹ ዘመናት የፖለቲካው ክንፍ ዘዋሪ የነበሩት አቶ መለስ ከድል በኋላም በመሪነቱ በመሰንበታቸው ይሆናል፡፡
የጫካው መለስ ሁልጊዜ አሸናፊነትን ብቻ ሰንቀው የሚነሱ፣ ከእሳቸው ሃሳብ በተቀራኒ የቆመን ሁሉ ተጨባጭ በሆነም ባልሆነም ፍረጃ ከጨዋታ ውጭ እንደሚያደርጉ፣ የተቀናቃኛቸውን ግብአተመሬት ለመፋጠን ዋና ዋና መርሆችን እንኳን ከመጣስ እንደማይመለሱ የቀድሞ የትግል አጋራቸው እና የዚህኛው የአቶ መለስ ስብእና ሰለባ የሆኑት አቶ አረጋይ በርሄ አቶ መለስ ባረፉ ሰሞን ለቪኦኤ በሰጡት ሰፊ ቃለምልልስ ገልፀዋል፡፡አቶ ግደይ ዘርአፅዮንንም አቶ መለስ ህወሃት ገላ ላይ የበቀለ ጋንግሪን ስለሆነ እሱ ካልተቆረጠ ህወሃት በህይወት አትኖርም ብለው እንዳሰናበቷቸው በትግሉ ዙሪያ የተፃፉ መዛግብት ያትታሉ፡፡ ይሄ የአቶ ግደይ እና የአቶ አረጋይ እጣ በብዙ ለምን ባይ ታጋዮች ላይም ወድቆ እንደ እስራኤሉ ሙሴ የመሩት ትግል ወደተስፋ ምድራቸው አዲስ አበባ ሳይደርስ ከመሃል መንገድ እንዲቀሩ አድርጓቸዋል፡፡
የትግሉ ዘመን ገንዘብ ቤት የነበሩት አቶ እየሩስአሌም ጌታቸውም በተመሳሳይ አቶ መለስን ጠላታቸውን ለመወንጀል ራሳቸው ሚያደርጉትን ሳይቀር እንደወንጀል ጠቅሰው የሚከሱ ሲሉ የሃገር ልጅ ለተሰኘው የኢሳት ፕሮግራም ገልፀዋል፡፡ በራሳቸው ላይ የደረሰውን እንደማስረጃ ሲገልፁም “ከ1977 በፊት በነበረው የትግሉ ወቅት ከተቃራኒ ጾታ ጋር የፍቅር ግንኙነት መጀመር ክልክል ቢሆንም እኔ በስህተት የጀመርኩትን ግንኙነት ደርሶበት ከሶ አስቀጥቶኝ ነበር፡፡ ይህንን ያደረገው ከእኔ ጋር አለመግባባቶች ስለነበሩ እንጂ ህጉን ለማስከበር አልነበረም ምክንያቱም በኋላ አዜብ ራሷ እንደነገረቸኝ መለስ እና እሷ ከ1971 ጀምሮ ድብቅ የፍቅር ግንኙነት ነበራቸው” ይላሉ፡፡
ከላይ ስለአቶመለስ የጫካ ስብእና አፈንግጠው ከወጡት የቀድሞ የትግል አጋሮቻቸው ከሚሰማው በተቃራኒ ስለጫካው መለስ ትህትና፣ ጉራማይሌ ሃሳብ አስተናጋጅነት፣ የሁሉን ሃሳብ አድማጭነት፣ ሃሳብን እንጂ ሰውን በክፉ የማያዩ እና ሚዛናዊ ውሳኔ ሰጭ መሪነት የሚመሰክሩ ፀሀፍትም ሆኑ የአይን ምስክሮች ሞልተዋል፡፡ የአቶ መለስን ፖለቲካዊ ስብእና በተመለከተ በሁለት ተቃራኒ ጫፍ ላይ የቆሙ መረዳቶችን ለማመሳከር የከተሜውን መለስ አመራር ማጤኑ አማራጭ መንገድ ነው፡፡
በግሌ የአቶ መለስን ጉራማይሌ ሃሳብ አስተናጋጅነት ትእግስት እጠራጠራለሁ፡፡ ምናልባት እስከተወሰነ፣ ለክፉ እስካልሰጠ ድረስ የተለየ ሃሳብን የሚቀበሉ ዲሞክራት መሪ ለመምሰል ይሞክሩ ይሆናል እንጂ ለሃሳብ የበላይነት እጃቸውን ሲሰጡ አልተስተዋለም፡፡ ይሄን ለማረጋገጥ ደግሞ በራሳቸው አንደበት ስለተቃዋሚ ፓርቲዎች “ማሰሪያቸው ሲረዝም የተፈቱ ይመስላቸዋል” ሲሉ የገለጹትን እንደአስረጂ ማንሳት ይቻላል፡፡
ጠቅለል ብሎ ሲታይ አቶ መለስን በተመለከተ ዘላቂ ወዳጆቻቸው ከሚያነሱት ፖለቲካዊ ማንነታቸው ይልቅ በነ አቶ አረጋይ የተገለፀው የጫካ ማንነታቸው በከተሜው መለስ ላይ ጎልቶ ይታያል፡፡ ምናልባት በተቃራኒው የሚያስረዳኝ ካለ ለመማር ዝግጁ ነኝ፡፡ ወደ ግላዊ መረዳቴ ስመለስ አቶ አረጋይ አቶ መለስ ባለጋራውን ለማጥቃት ንኛውንም መርህ ሊጥስ ይችላል ያሉት ነገር በ1997 አቶ መለስ ስልጣናቸውን ለማትረፍ ሲያደርጉት የነበረው ዲሞክራሲያዊ መርሆችን የመጣስ የደመነፍስ ጉዞ ምስክር ነው፡፡
በወቅቱ የተቃውሞው ጎራ መሪዎችን ከያሉበት እየለቀመ ሲስፈልግም ቦክስ እየሰነዘረ እስርቤት የሚያጉረው ፖሊስ በቀጥታ የሚታዘዘው በእሳቸው ነበር፡፡ የመንግስታቸው አካሄድ የህዝብ ቁጣ ሊቀሰቅስ እንደሚችል የተረዱት ነገር አዋቂው መለስ የዲሞክራሲ መርሆዎች አንዱ የሆነውን የመሰብሰብ መብት በገዛ አንደበታቸው ላልተወሰነ ጊዜ ብለው ለስምንት አመት እንደ እናት ጡት እንድንረሳው አደረጉ፡፡ ጋዜጠኞችን ለቃቅመው ሲያስሩም ከዲሞክራሲያዊ መርሆዎች አንዱ የሆነው ሚዛናዊ መረጃ የማግኘት መብት እየተጣሰነበር፡፡
ከዘጠና ሰባት አለፍ እንበል ከተባለ ደግሞ ለኢህአዴግ ጆሮ የማይመቹ መረጃዎችን የሚያቀርቡ መገናኛ ብዙሃንን ስንት ሃብት አፍስሶ በሞገድ ከማፈን ጀምሮ እስከ ማተሚያ ቤት ድረስ ገስግሶ የውሃሽታ የማድረጉ እርምጃ ዲሞክራሲያዊ መርህ መጣሱ እንደ ቀጠለ ያመላክታል፡፡ ህገመንግስታዊ መርሆች ሳይቀሩ ነገሬ የማይባሉበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ሽብርተኝነትን ለመቆጣጠር ወጣ የተባለው አዋጅ፣ የመገናኛብዙሃን እና የሲቪክ ማሀበራት ህጎች ለዚህ ምስክሮች ናቸው፡፡ ህገ መንግስት ተርጓሚ ተብሎ የተቀመጠው አካልም የአቶ መለስን አመራር የመሞገት ሞገስ ያለው አይመስልም፤ አይን በአይን ህገመንግስቱን የሚጥሱ ህጎች ሲወጡ በአንዱም ላይ ተቃውሞ ሲሰማ አልተደመጠምና፡፡
አቶ እየሩሳሌም የጫካው መለስ ራሳቸው የሚያደርጉትን ነገር ሳይቀር እንደ ወንጀል ጠቅሰው ተቀነቃኛቸውን ይከሱ ይወቅሱበት ነበር ያሉት የአቶ መለስ ስብእና በከተሜው መለስ ውስጥም በጉልህ ይስተዋላል፡፡ ራሳቸው አቶ መለስ ይመሩት የነበረው ህወሃት ትግራይን ነፃ ለማውጣት ብረት አንስቶ አስራ ሰባት አመት መዋጋቱ እውነት ቢሆንም እሳቸው መንግስት ከሆኑ በኋላ የወጡበትን ብሄር ነፃ እናወጣለን የሚሉ ድርጅቶችን በጠባብነት ይፈርጁ ነበር አቶ መለስ፡፡ ነፃ አውጭ ነን ባዮቹ ብረት ያነሱ ከሆኑ ደግሞ የስድብ እርግማኑ መጠን ይጨምርና ጠባብ በሚለው ላይ የእንትን ተላላኪ፣ ሃገር አፍራሽ፣ ፀረ-ልማት፣ ፀረ-ሰላም፣ፀረ-ህዝብ የመሳሰሉ አጠልሽ ቅጥያወች ይጨመሩላቸዋል፡፡
የአቶ መለስ ህወሃት እዚህ የደረሰው ለሻብዕያ አቤት ወዴት ብሎ ቢሆንም አሁን ወደሻዕብያ ጠጋ ጠጋ የሚሉ የኢህአዴግ ባላንጣ ፓርቲዎች ስማቸው ሀገር ከዳተኛ ነው፡፡ በጫካ ሳሉ ኢትጵያን ሸራርፎ “ታላቋ ሶማሌ”ን ለመገንባት ደፋቀና ሲል የነበረው ዚያድባሬ በሰጣቸው የሱማሌ ፓስፖርት ሲንቀሳቀሱ እንደነበረ በገዛ አንደበታቸው የተናገሩት አቶ መለስ በተመሳሳይ መንገድ የሚሄዱ የዘመኑ ብረት አንጋች ተቃዋሚዎችን ሲየብጠለጥሉ ጊዜ አይበቃቸውም ነበር፡፡
ተፈጥሯዊው የወጣትነት እድሜ የሚያመጣው ለውጥ መሻት ከዩኒቨርሲቲ ደደቢት ያበረራቸው አቶ መለስ የአሁን ወጣት ስለለውጥ እንዲያስብ አይፈልጉም ነበር፡፡ የሚፈልጉት በጥቃቅን እና አነስተኛ ተደራጅቶ የእሳቸው መንግስት ባሰበለት መጠን እንዲኖር ነው፡፡ እሳቸው እንዳደረጉት ለለውጥ እነሳለሁ ካለ ስሙ አደገኛ ቦዘኔ፣ የሆነ ሰው ተላላኪ (እንጂ በራሱ አስቦ ለውጥ የማይፈልግ)፣ የጎዳና ላይ ነውጠኛ ወዘተ ነው፡፡(ይጥላል)

No comments:
Post a Comment