Saturday, August 24, 2013

አንድነት በፍቼ ከተማ አባላቱ መደብደባቸውን አወገዘ

አንድነት በፍቼ ከተማ አባላቱ መደብደባቸውን አወገዘ


“ወደ ስፍራው ከመድረሳቸው በፊት ጥበቃ እንዲደረግላቸው አላሳወቁም”
- (የዞኑ ኦህዴድ ጽ/ቤት)
አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) ነገ በፍቼ ከተማ የሚካሄደውን ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ለማስተባበር በስፍራው የተገኙት ሁለት አባላቱ መደብደባቸውን አወገዘ፡፡ የፓርቲው የህግ ክፍል ድርጊቱን በፈፀሙ አካላት ላይ ክስ ለመመስረት ወደ ስፍራው እንደሚጓዝ ተገልጿል፡፡ 
የአንድነት ፓርቲ የአዲስ አበባ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ነብዩ ባዘዘው እና ባልደረባቸው አቶ መሳይ ትኩ፤ ነገ የሚካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ለማስተባበርና አንዳንድ ዝግጅቶችን ለማድረግ ረቡዕ አስር ሰዓት ተኩል አካባቢ ፍቼ ከተማ መድረሳቸውን የገለፁት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ፤ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ ባረፉበት ሆቴል በከተማው የፀጥታ ዘርፍ ምክትል ሃላፊና ሌሎች ፊታቸውን በሸፈኑ 11 ሰዎች ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸውና ራሳቸውን ሲስቱ ጥለዋቸው መሄዳቸውን ገልፀዋል፡፡ “በስፍራው የደረሰው ፖሊስ ህገ ወጥ ድርጊት የፈፀሙትን ይዞ ወደ ህግ ማቅረብ ሲገባው፣ ዱላቸውን ቀምቶ ወደቤታቸው መሸኘቱ አይን ያወጣ የህግ ጥሰት ነው” ያሉት አቶ ዳንኤል፤ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀስ ህጋዊ ፓርቲ አባላትን በዚህ መልኩ ማሰቃየቱ የህግ የበላይነት እየተጣሰ መሆኑን ያመላክታል ብለዋል፡፡ 
ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድና ክስ ለመመስረት የፓርቲው የህግ ክፍል ወደዞኑ እንደሚያመራም አቶ ዳንኤል በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡ http://andenatethiopia2012.blogspot.no/2013_08_01_archive.html
አንድነት የጀመረው የሶስት ወር የህዝብ ንቅናቄ አካል የሆነውን ሰላማዊ ሰልፍ ነገ በባሌ ሮቤ፣ በአዳማና በፍቼ ለማከናወን እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ዳንኤል፤ ይህን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ የፍቼ ከተማ የፀጥታ ዘርፍ ሃላፊዎችና ግብረ አበሮቻቸው ያደረሱትን ህገ-ወጥ ድርጊት ፓርቲው በቸልታ እንደማያልፈው ጨምረው ገልፀዋል፡፡ 
ድብደባ ተፈፀመባቸው ወደተባሉት አቶ ነብዩ ባዘዘው ደውለን በሰጡን መረጃ፤ የከተማው የፀጥታ ዘርፍ ም/ሃላፊ የሆኑት አቶ ሃይለየሱስ በየነና ሌሎች 11 ሰዎች እንደደበደቧቸው ገልፀው፤ “በመጀመሪያ እኛ የያዝነውን አልጋ ካልያዝኩ የሚል አንድ ሰው ልከው ነገር ፈለጉን፤ ግን እኛ ዝም አልን” ብለዋል፡፡ 
የሆቴሉ ባለቤቶች “መጀመሪያ አከራይተነዋል፤ አሁን ለመጣ ሰው እንዴት እንሰጣለን” በሚል በተነሳ ክርክር፣ የፀጥታ ዘርፍ ሃላፊው እና ግብረ አበሮቻቸው ከፍተኛ ድብደባ እንዳደረሱባቸው የተናገሩት አቶ ነብዩ፤ እነዚህ ሰዎች ደብድበዋቸው ከሄዱ በኋላ ፖሊሶች ወደመኝታቸው ገብተው የፓርቲውን የፍቃድ ወረቀት፣ መታወቂያቸውን፣ ቃለ ጉባኤና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመውሰዳቸው ምንም አይነት ስራ ለመስራት መቸገራቸውን ጠቁመዋል፡፡ በድብደባው እሳቸውም ሆኑ ባልደረባቸው ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቁመው፤ ባልደረባቸው አቶ መሳይ ትኩ በግራ እጃቸው ላይ ስብራት እንደደረሰባቸው ሀኪሞች መናገራቸውን ገልፀዋል፡፡ 
የሰሜን ሸዋ ዞን የኦህዴድ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሰለሞን መኮንን ጋር ቀርበው ልብሳቸውን በማውለቅ የደረሰባቸውን ጉዳት ማሳየታቸውን የተናገሩት አቶ ነብዩ፤ ሃላፊው ይህ ህገ ወጥ ድርጊት ነው፤ ፓርቲያችንም ሆነ መንግስታችን አይቀበለውም፤ በአስቸኳይ ኮሚቴ አቋቁመን ድርጊቱን የፈፀሙ ግለሰቦች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንወስዳለን፤ እናንተም ክስ መስርቱ ብለውን ይህን እያደረግን ነው ብለዋል፡፡ 
“ፖሊሶችም፤ ደብዳቤዎቹን ወደ ህግ ሳያቀርቡ በሰላም መሸኘታቸው በፓርቲያችን ላይ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ሴራ እየተፈፀመ መሆኑን ማሳያ ነው፤ እኛ ግን ሰላማዊ ትግላችንን እንቀጥላለን” ብለዋል አቶ ነብዩ፡፡ 
በሰሜን ሸዋ ዞን የኦህዴድ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሰለሞን መኮንን በበኩላቸው፤ ጉዳቱ የደረሰባቸው የአንድነት ፓርቲ ሰዎች ቀደም ብለው ወደ ከተማው ስለመምጣታቸው ለኦህዴድ ጽ/ቤትም ሆነ ለፀጥታ አካሉ አለማሳወቃቸውን ገልፀው፤ ይህን ቢያደርጉ ኖሮ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይችል እንደነበር አብራርተዋል፡፡ 
“በተፈፀመው ድርጊት እንደግለሰብም እንደ መንግስት አመራርም በጣም አዝኛለሁ” ያሉት የጽ/ቤት ሀላፊው፤ ጉዳቱን ያደረሰባቸው አንድ ግለሰብና የባጃጅ ሹፌር እንደሆነ መስማታቸውንና ይህም ግለሰብ በሀገሪቱ ህግ መሰረት ተጠያቂ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡ 
የፀጥታ ዘርፍ ም/ሀላፊውና ሌሎች የፖሊስ አካላት የፓርቲውን አባላት ደበደቡ የተባለውን ግን አቶ ሰለሞን አስተባብለዋል፡፡ የማሳወቂያ ደብዳቤውን በተመለከተ፤ ሰዎቹ ለከተማው ከንቲባ ጽ/ቤት ያስገቡት ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ መሆኑን ከከንቲባው ጽ/ቤት መስማታቸውንም ሀላፊው አብራርተዋል፡፡ 
“ያስገቡት ደብዳቤ ፎርማሊቲውን ያሟላ አያሟላ ባላውቅም ደብዳቤው መስፈርቱን አሟልቶ ሰልፉ ከተፈቀደ የፀጥታ አካሉ ጥበቃ ያደርግላቸዋል” በማለት አረጋግጠዋል፡፡ መደብደባቸውን ከተናገሩ በኋላ ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ 
ጉዳት የደረሰባቸው የፓርቲው አባላት ድብደባውን በፈፀሙ ግለሰቦች ላይ መረጃ አሰባስበው ክስ መመስረት እንደሚችሉም አቶ ሰለሞን ገልፀዋል፡፡

No comments: