Saturday, August 24, 2013

ምርጫ 2007 ያስፈልጋል?”


 አዲስጉዳይ በዛሬ ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 
 2005 ዕትሙ
 የአዲስጉዳይ መጽሔት ዝግጅት ክፍል 
 ለመላው አንባቢያን መልካም ቅዳሜ  ይመኛል።
 በዛሬ የዐብይጉዳይ አምድ “ምርጫ 2007 
 ያስፈልጋል?” በሚል ርዕስ ስር በኢትዮጵያ 
 እስካሁን በተካሄዱት ምርጫዎች ዓላማ 
 መሳትና ወደፊት ሊኖሩ በሚችሉ ምርጫዎች 
 ውጤት አልባነት ዙሪያ የሚያጠነጥን ጽሑፍ 
 ለንባብ አብቅቷል። በኢትዮጵያ ኢህአዴግ 
 ሥልጣን ከያዘ በኋላ የተካሄዱ ምርጫዎች 
 ሁሉ የይስሙላና የሕዝብን የሥልጣን 
 ባለቤትነት ያላረጋገጡ ‘የኮታ በሙያ ናቸው’ 
 ይለናል ጽሑፉ። ኢህአዴግ በምርጫ 97 
 ትክክለኛውና በአንጻራዊነት ሲመዘን 
ዴሞክራሲያዊ የነበረ ነው የተባለ ምርጫ 
ቢያካሂድም ሕዝብ በዚህ ዴሞክራሲ
 ጭላንጭል ተጠቅሞ ምርጫውን ቢያካሂድም 
በውጤቱ ግን ያልተጠበቀና ፍጹም በተቃራኒው የተጓዘ ዴሞክራሲን ማፈን፣ 
ምርጫንም ማጭበርበር ፈጽሞ የሕዝቡን ‘ዴሞክራሲ አለ’ የሚል ተስፋ አዳፍኖታል 
የሚለው ይህ ጽሑፍ እስካሁን ባሉት ዓመታት የተካሄዱት ምርጫዎች ሁሉ ሕዝብ 
የሚፈልገውን አካል በፍቃደኝነት ሥልጣን ላይ ያላስቀመጠበት ከሆነ ወደፊት 
የሚካሄዱት ምርጫዎች ዋጋ ቢስ ናቸው ይላል። እስካሁን በነበሩት ምርጫዎች 
ሂደት፣ ኢህአዴግ ምርጫን አስመልክቶ እየተጫወተ ባለው ጨዋታ ተገቢነትና 
ወደፊት በምርጫ የዚሀች ሀገር ፖለቲካ ሊኖረውና ላይኖረው የሚችለውን ለውጥ 
አስመልክቶ ጽሑፉ ሰፊ ትንታኔ ያስነብባል። በዚህ ስሌት ምርጫ 2007 
ያስፈልገናል? ብሎም ይጠይቃል።

በቃለምልልስ ዓምድ የኦሮሞ ፖለቲካ ጉዳይ ላይ ያተኩራል። ኢትዮጵያዊነትና 
ኦሮሞነት፣ አንድነትና ልዩነታቸው የኦሮሞን የገዳ ባህላዊ አስተዳደርና የኦሮሞ ሀገር 
በቀል ዕውቀት ላይ ጥናትና ምርምር ያደረጉትና አራት መጽሐፍት ያሳተሙት 
የዶክትሬት እጩው አቶ ተፈሪ ንጉሴ “ፖለቲካችን ፍርሃትና መጠቃት ይገልጸዋል” 
ይላሉ። በኦሮሞ ፖለቲካና ተያያዥ ጉዳዮቹ ላይ ያተኮረው ይህ ቃለምልልስ 
በወቅታዊው የኦሮሞ ጥያቄና በታሪካዊ ዳራው ላይ የሚያተኩሩ ዋና ሃሳቦችን 
ይዟል።
የዛሬ የታፈኑ ዕውነቶች አምድ “የተጣሉ ነፍሶች፣ ህግና ኅሊና የሚያሳድዳቸው 
እናቶች” በሚል ርዕስ ተወልደው ስለሚጣሉ ኢትዮጵያውያን ህጻናት የሚያወሳ 
ሰፋ 
ያለ ዘገባ ይዟል። በዚህ ጽሑፍ አዳዲስና ጆሮ ያልሰማቸው አሳዛኝ የህጻናት 
ጉዳት ታሪኮች ለንባብ በቅተዋል።
አዲስጉዳይ በዛሬ ወቅታዊ ጉዳይ አምዱ “አብዱልፈታህ አል ሲሲ ዝምተኛው 
ጄኔራል” የሚል የግብጹን የጦር መሪ ማንነት የሚያወሳ ጽሑፍ ሲያትም በስፖርት 
አምዱ ደግሞ “መሃመድ አማን፤ ከምንም— ወርቅ የፈጠረ ጀግና” በሚል ርዕስ 
ስለአትሌት መሃመድ አማን ያስነብበናል።
አምደኛው ሰለሞን ተሰማ ጂ. በታሪክና ፖለቲካ አምድ የታህሳሱ ግርግርና መዘዙን 
የሚያወሳ ታሪክ ይዞ ቀርቧል።
የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ በነጻ መድረክ አምድ ላይ “ሼህ ኑሩን ማን ገደላቸው? 
ለምን?” በሚል ጥያቄ ጉዳዩን በስፋት የገለጹበትን ጽሑፍ ይዘው መጥተዋል።
በወግና መጣጥፍ ዘርፎች የአዲስጉዳይ አምደኞች ሃብታሙ ስዩም “መጽሐፍና 
ሥጋ” ፣አሌክስ አብረሃም አድዋ ዛሬ ናት፣አድዋ ትናንት” ፣ ህይወት እምሻው 
“ትምህርትና ዕውቀት” የሚሉ አዝናኝ ጽሑፎቻቸውን ይዘው ቀርበዋል።
በህግ አምድ አቶ ፊልጶስ አይናለም “ትዳርና ዕዳ” የሚል አስተማሪ ጽሁፍ ይዘው 
ብቅ ብለዋል። የድምጻዊ ኢዮብን አሟሟት ጉዳይ የተመለከተው የዶክተር ብርሃኔ 
ረዳኢ ጽሑፍና የጥበባት ሕይወቱን የሚዳስሰው የጥበባት አምድ ዘገባም 
አንባቢዎቻቸውን ይጠብቃሉ። የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ሰሞነኛ ጉዳዮች ዜናና 
ወቅታዊ መረጃዎችን ይዘው ወደእናንተ ደርሰዋል።
ዝግጅት ክፍሉ ለአንባቢያኑ በድጋሚ ከአዲስጉዳይ ጋር መልካም ቅዳሜ ይመኛል።

No comments: